Tuesday 31 December 2013

ትንሽ ስለ ሜንጫ ፓለቲካ ባህሪያት (ሳምሶን. ብ. ለንደን )

        ባንዲራ ጨርቅ ነው ፤ የአክሱም
menchaሐውልት ለወላይታው ምኑ ነው ? ኢትዮጵያ ሀገራዊ ህልውና የመቶ አመት ጉዳይ ነው ፤ ያለ ‘ብሄሮች ፈቃድ’ የኢትዮጲያ ነገር አከተመለት ከተባለ 23 አመታት በሁዋላ ሰሞኑን ጎሰኝነትና የከርሞው ‘ ኢትዮጵያ ለምኔ’ ቱማታ እንደገና ‘በህዳሴ’ ብቅ ማለት የጀመረ ይመስላል። ምስጋና ‘ለወጣቱ ምሁር’ ጃዋር መሀመድ ይድረሰውና ! ጃዋር ብቻውን ስላይደለ እንቅስቃሴውም የተደራጀ እንደመምሰሉ ለዚህ ጽሁፍ ይሆን ዘንድ ‘የሜንጫ ፖለቲካ’’ ስል እሰይመዋለሁ። ይህን ስያሜ የመምረጤ አብይ ምክንያት የዚህ ቡድን አባላት ቢሳካላቸው ተፈጸመብን የሚሉትን የፓለቲካ አድልዎና በደል ሊያርሙ የሚመርጡት  መንገድ  ግፍን በግፍ የማረም መሆኑን ለማስገንዘብ ነው። አንባቢዎች በዚህ ምትክ ያሻቸውን ስያሜ ሰጥተው ሊጠቀሙ መብታቸው ነው።
በዚህ ጽሁፍ በኦሮሞ ማህበረሰብ ኢትዮጵያዊነት ላይ በሀገራችን ነገስታት የስልጣንና ሀብት ቅርምት በይበልጥም የግዛት ማስፋፋት ሂደት ውስጥ የተፈጸሙትን ሁነቶች በተመለከተ  የጭብጥ ክርክር ውስጥ ብዙም አልገባም።ለዚህም በርካታ ምክንያቶች አሉኝ፤፡ አንዱና ዋናው ምክንያት አዲሶቹ  ጎሰኞች በመረጃና ታሪክ ጠቀስ ክርክር  እምብዛም ስለሆኑ ነው፡፡ ለምሳሌ የታሪክ ነክ ክርክሮችን በኢትዮጵያውያን አዋቂዎች ድርሳናት ማመሳከር አይቻልም ፤  በእነርሱ የጨዋታ ሕግ መሰረት ኢትዮጵያውያን የታሪክ  አዋቂዎች ሁሉ ‘ደብተራዎች’ ናቸው ፤ ስራቸው ለምስክርነት የማይቀርብ ። የአውሮፓውያኑን  ድርሳናት ማመሳከር ደግሞ ፈረንጆቹን ‘በነጭ ነፍጠኝነት’ ያስከስሳል። ሁለተኛው ምክንያቴ ደግሞ የክርክራቸው አሰልቺነት ነው። የተዛባ ማስረጃና ጩሀት ተደጋግሞ ስለተነገረ እውነት የሚሆን ይመስል ውሃ ወቀጣ ይበዛዋል ፡፤ ኢትዮጵያ ከህወሃት መንግስት በፊት ከኦሮሞዎች  በቀር ለተቀሩት ብሄረሰቦች በተለይም ለአማራው ‘ምድራዊ ገነት’ እንደነበረች ነው ተደጋጋሚው ስብከቱ።  የባሌ ኦሮሞ በቀዳማዊ ሀይለስላሴ ላይ ሲያምጽ የጎጃም ሰው ቤቱ በሰላም ውሎ የገባ  ይመስል አልያም የወሎ ሰው በረሃብ ሲጠቃ ንጉሱ ‘ ወገኔን’ ብለው ያደሉለት ይመስል። እሺ ካለፈው የተማረ ስረአት መመስረት ላይ ለምን አይሆንም ውይይቱ ለሚል መልስ የለም ፤ ዘፈኑ ተመልሶ ወደ ሚኒሊክ ፤ ሲያሻው ወደ ሃይለስላሴ ይሄዳል ፤፡ የፊትን የማየት ነገር የሚባል ልማድ እዚያ አካባቢ የለም ፡ እንዲያውም ‘በትምክተኝነትና ሴረኛ አማራነት’ ያስከስሳል። ከሁሉም ከሁሉም ከእንደዚህ   አይነት ሰዎች ጋር ረብ ያለው ውይይት ማድረግ የማይቻለው የእልህና ቁጣ ፖለቲካ መልመዳቸው ነው። ለምን ማህበራዊ ድረ ገጽ ላይ አይሆንም የሀሳባቸውን ፋይዳ ቢስነት መተቸት ቁጣና ለከት የሌለው ዘለፋ ያስከትላል። እናም ለጊዜው  ይህን ጽሁፍ ሰሞኑን ፈገግ አለያም እንዴ ባሰኙኝ ጉዳዮች እንዲያተኩር አደርጋለሁ።
‘የሜንጫ ፖለቲካ’’ ዋንኛ ባህሪው እንደ አብዛኛው አፍሪካዊ  አፋጣኝ ስልጣን ፈላጊ  የፓለቲካ ልሂቅ የቆየ ብሶትን መቆስቆስ መሰረት ያደረገ ነው ። ፈረንጆች ግሪቫንስ ፓለቲክስ እንዲሉ። የአፍሪካ ፓለቲካ ልሂቃን  በዚህ የተካኑ ናቸው የ እኛዎቹን ጨምሮ : ታሪካዊ ፤ ነባራዊና ማህበራዊ ልዩነቶችን ፣ እነዚህ ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን እንዴት ተጠቅመው ተከታዮቻቸውን ማባዛት በተለይም በምሬት ማነሳሳት ያውቁበታል። በሀገራችን ከድህረ ወያኔ መራሄ መንግስትነት  በሁዋላ ይሄ ስልት የፓለቲካ ወደጅና ጠላትን ከመፈረጅ  ባለፈ የፌዴራል አደረጃጀቱን ፤ የመሬት ስሪቱንን ያልተጻፈውን የኢኮኖሚ ፓሊሲና ከሁሉም ከሁሉም የፓለቲካ ስርአቱን ቅርጽና ይዘት ለማደራጀት ጠቀሜታ ላይ ውሏል። እንደ አብዮታዊ ዲሞክራሲያውያኑ እይታ ትልቁ የፓለቲካ ፋይዳቸው ‘ስልጣን ተመልሶ ነፍጠኞችና ትምክተኞችና ያለፈው ስርአት  ናፋቂዎች እጅ እንዳይገባ ማድረግ ነው። ያ እንዲሆን ደግሞ በየጎጡ የተሰለፈው የፓለቲካ ልሂቅና ጀሌው ትናንት ጡትህን ሲቆርጡህ የነበሩትን ፤ ትናንት እንዲህ ሲሉህ የነበሩትን እያሸንልህ ነው አንተም ክንድ አበድረን ይባላል። በፕሮፓጋንዳ ስሜቱ የተንቦገቦገ  ቆም ብሎም አያስብም  በክንድ ፈንታ የክላሹን ቃታ ነው የሚስበው፡፡
የሚገርመው እነ ጃዋር ይሄንን ለ23 አመታት ስንሰማው  የነበረውን ዜማ ከልሰው ፤ አራዶች እንደሚሉት ‘ሪሚክስ’ አድርገው በአዲስ መልኩ ሊያቀርቡት መፈለጋቸው ነው። ይህ ሕዝብን ከሕዝብ የማባላትና በሂደቱም ስልጣንን የማቆየት ዘዴ የዛሬን አያርገውና ‘ እኒያን ሽርጣም ሲሉዋችሁ የነበሩትን ነፍጠኞች በሉዋቸው ሲባል ተቀኝቶለታል በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ታምራት ላይኔ ። ይህንን ተከትሎ ዘርና ደም እየተቆጠረ ከስራ ማባረር ፤ እስርና ግድያ በብዙዎች ላይ ተፈጽሞአል።  እንዲህ አይነቱ ግፍ በቀደሙት ስርአት ግፉአን ነበሩ የተባሉትን ብሄረሰቦችና የማህበረሰብ ክፍሎች ቁስሎች ያሽሩ ይሆን ? የለም ! ወያኔ ስልጣኑን ለማደላደል በተጠቀመበት በዚህ አይነቱ የመስዋእት በግ አሰሳ ዋና ተሳታፊ የነበሩ እንደ ኦነግ ያሉ ድርጅቶች  ፤ ነፍጠኛው ነው የሚፈጀው እኛ ምን ከዳችን ሲሉ ከዳር ቆመው የነበሩ ኦሮሞዎችም በሁዋላ ላይ የስርአቱ አዶ ከበሬ ደምና የእስር ቤት ግብር ሲሻ ገፈቱን ቀምሰውታል ፤ ዛሬም ድረስ በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን የዝዋይና ሸዋ ሮቢትን እስር ቤቶች ታጉረውም ይገኛሉ።  የሽግግር ( እናታችን የችግር ትለዋለች) ስርአቱ ሲመሰረት ነጻ አውጪ ነን ሲሉ የተሰባሰቡት ፓለቲከኞች ከብሶትና በቀል ፓለቲካ አርቀው አይተው ብሄራዊ መግባባትን ፈጥረው ቢሆን ኖሮ ይሀው ዛሬም እቀድሞ ሲዜም የነበረው  ቢሊሱማና ወልቂጡማ  የሚኒያፓሊስን ተራሮች  አያንቀጠቅጣቸውም ነበር።
ከአስገራሚዎቹ ‘የሜንጫ ፖለቲካ’’ ባህሪያት መሀከል ዋናው ደግሞ ተጋፊነቱና ኢፍትሀዊ አመለካከቱ ነው። ሰሞኑን እንደምናነበውና እንደምንሰማው ከሆን የእነ ጃዋር ‘ኦሮሚያ’ እውን ትሆን ዘንድ የሌሎቻችን መብቶች ሁሉ መታቀብ አለባቸው። አዲሶቹ ነጻ አውጪዎች  ወገኖቻችን ለሚሉዋቸው  የህብረተሰብ ክፍሎችና ብሄረሰቦች ወደፊት ሊቸሩዋቸው ከሚያሰቡአቸው መብቶች ውስጥ የተወሰኑትን ለእኛ ለወደፊቱ ጎረቤቶቻቸው ባይነፍጉን ምናለ? እነ ጃዋር የኢትዮጵያ ሙስሊሞች (ሰሞኑን ወደ ኦሮሞ ሙስሊሞች ወረድ ብሎ ይሆናል ) በሀገሪቱ እኩል የእምነት ነጻነትን በሰበኩበት አንደበታቸው እነርሱ ሰፈር ቤተስኪያን ሊሰራ ላሰበ አማኝ ለምን  ሜንጫ ይመኙለታል ? እነርሱ የራሳቸውን የታሪክ ድርሳናት አማክረው በአደባባይ የሚዘልፉትን ፤ የተቀረው አለም ቢያንስ ቢያንስ ‘’በማያዳግም መልኩ የነጭን ሰራዊት ለመጀመሪያ ጊዜ ድባቅ የመታ  ሕዝብን የመራ ንጉስ’’  ሲል የመሰከረለትን መሪ የለም ስሙን በደግ አታንሱ ይላሉ። የእነርሱ ህልም እውን ይሆን ዘንድ ያለፈ ታሪክን መልካም ገጽ ማንቆላጰስና በሂደቱም ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት መታቀብ አለባቸው ። ለምሳሌ እነርሱ ሚኒሊክ ፈጸሙት የሚሉትን ግፍ ለማስታወስ ሙዙየም ማሰራታቸውን ፤ ሃውልት ማቆማቸውን ሌላው ማህበረሰብ በዝምታ ሲያልፈው ታሪክን በሌላ ገጽ የሚመለከተው  ማህበረሰብ ለምን የእነርሱን ያህል መብት እንዲያጣ ይፈለጋል? ከዚሁ በተጓዳኝ ከሁሉም የሚያሳፍረው ተግባር  ደግሞ የእነርሱን  ጽንፍ የነካ ዘረኝነት የማይጋሩ ኦሮሞዎች ላይ የሚያደርሱት ጫና ነው። ትናንት ከመገንጠል ውጭ አማራጭ የለም ሲሉ ይታገሉ የነበሩ ፤ ዛሬ ደግሞ የለም ከብሄራዊው ዳቦ የድርሻችንን ነው ለማግኘት መታገል  ያለብን የሚሉ ጎምቱ የኦሮሞ ፖለቲከኞች  አይደለም ሀሳባቸው ሊሰማ በመጀመሪያ ከሜንጫ ፓለቲከኞች  የኦሮሞነት መታወቂያ ማግኘት አለባቸው።  እንዲያ በማሰባቸው ብቻ ‘ጎበናዎች’ ይሆናሉ በአንድ ሌሊት ። ይሄ ተዋልጄያለሁ ተዛምጄያለሁ የሚለውን ኦሮሞማ ለጊዜው መተው ነው ፤ ሲጀመርም እንደ ‘አርያን ሜንጪስት’ አይቆጠርም።
ሌላው  ‘ የሜንጫ’ ፖለቲከኞች መለያ ፤ የተከታይን ቀልብ ይስባል ተብሎ የሚታሰበውን ሁሉ ፍለጋ ከዛፍ ዛፍ መዝለል። ባለፈው የስኮትላንዱ ፈረስት ሚኒስትር አሌክስ ሳልመንድ የስኮትላንድን የሪፈረንደም ማኒፌስቶ ባወጀ ሰሞን እነ ኦቦ ጃዋርም የወንድም ሀገር ስኮትላንድ  አርአያነት ለተከታዮቻቸው ይሰብኩ ገቡ። እነርሱ ዘንድ ዩናይትድ  ኪንግደም የአራት ሀገራት ህብረት እንደሆነች ፤ ስኮትላንድ ከሕብረቱ ወጣች አልወጣች የራሳ ብሄራዊ አስተዳደር እንዳላት አይታወቅም።  የትም ይሁን የት ብቻ (ቲቤት ይሁን ፑንትላንድ፤ ኪውቤክ ይሁን ሞኖሶታላንድ ) የብሄራዊ ማንነት ጥያቄ ይነሳ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁናቴ ጋር ይዛመድ አይዛመድ  እነ ሜንጫ በፍጥነት ‘ ላይክ’ ያደርጋሉ። ይሄው ፈገግ አድርጎን ብዙም ሳንቆይ ደግሞ በማንዴላ እልፈተ ሞት ምክንያት  የእነ ጀነራል ታደሰ ብሩና ኮሎኔል ፍቃዱ ዋከኔ  ገድል መነሳት ጀመረ። እንደ ልማዳቸው የእኛዎቹ  ‘ የነጻነት ታጋዮች ’ አጋጣማውን ለግልብ የፓለቲካ ገበያ ሊጠቀሙበት ተንጠለጠሉበት፡፤ ማንዴላ እንደ ሁለተኛ ሐገሬ ነው የማያት ያሏት ኢትዮጵያ ፤ እነ ጀነራል ታደሰ ብሩና ኮሎኔል ፍቃዱ ዋከኔ  የተዋደቁላት ኢትዮጵያ ‘በፎቶ ሾፕ’ ከምስሉ ወጣችና የመኮንኖቹ  ጎሳና ደም ተቆጥሮ   በአንድ ሌሊት ታሪክ ተቀይሮ ማንዴላ ‘ከኦሮሚያ’ የጦር ልምምድ ስልጠና አግኝተው ነበር ተባለ።  የእነ ማንዴላ ቁስል አድራቂነት ፤ አስታራቂነት ፤ ዘርና ማህበራዊ ክፍፍል ያላሸነፈው የፓለቲካ ርእዮትማ  ማን ያስተውለው ? ለስሜትና ብሶት ፖለቲካ አይመችማ !
ዘግየት ብሎ ደግሞ ‘የሜንጫ ፓለቲካ’ የተመልካቾችን ቀልብ ይገዛልኛል ፣ ተከታዮቼንም ያበዛል በሚል  ስልት ታዋቂው አቀንቃኝ ‘ቴዲ አፍሮ’  ላይ እመር ብሎ ሰፍሯል።  እነ ጃዋር ቀድሞውንም ቢራ በአፋቸው  አይዞርም የሚባልላቸውንና  ከአማርኛ ሙዚቃ ከተፋቱ 23 አመት የሞላቸውን ‘ወገኖቻቸውን’ ፤ ቢራ አትጠጡ ሙዚቃም  አታድምጡ  እያሏቸው ነው። ለዚህ ዘመቻቸው ሰበቡ  ያው የፈረደባቸው ምኒሊክ ለምን ተወደሱ ነው። ይሄ እንግዲህ የፓለቲካ ‘ ስትራቴጂስቱ’ ኦቦ ጃዋር እንደ አስማተኛ ሊያጃጅለን እፊታችን  ያቀረበው  ‘ቀይዋን  ያየ’ መሆኑ ነው። በእርሱ ቤት  እኛ ‘የታላቂቷን ኦሮሚያ’  የመመስረት ቅዠት አናውቅም ፣ ይህ ሕልም እውን ይሆን ዘንድ ገና አንድ ሺ አንድ ሰበቦች እንደሚደረደሩም እሚገባን  አይደለንም። ከዚሁ ጋር በተያያዘ አስቂኙ የሜንጫ ፓለቲከኞች ሰሞናዊ ተግባር ደግሞ ይህቺን ጊዜያዊ ትርኢታቸውን ለማሳመር  በአርባና አምሳ ሺ እስር ቤት አጎረን ያሉት ወያኔን ‘አስኮቱ’ ማለታቸው ነው። ቴዲ አፍሮ ‘ በአስራ ሰባት መርፌ’                         ሲል የተዘባበተብህ እኛንም አጥንታችን ድረስ ዘልቆ ይሰማናል አሉታ ክንዱን ሊዋሱት። ህወሃት ምላጭ መሆኑን ከአጎቶቻቸው  ‘የሽግግር’ ጊዜው ታሪክ የተማሩም አይመስሉም ። ወያኔ ዛሬ ቴዲን ቢበላ በአንድ ጎጆ ሁለት አባወራ እንደማይኖር ስለሚያምን  ነገ የእነ ጃዋርን ጆሮ እንደሞቆረጥም ልብ ያሉ አይመስልም።  ለማንኛውም እነ ሜንጫ ፓለቲከኞች እደጃችን የቆመውን  አስቀያሚ  ሁነት እንድናውቀው ስለወተወቱን  እናመሰግናቸዋለን። ሲሆን  በአንድነት ቆመን ‘እምቢ ለዘረኝነት’ ብለን እናቆማቸዋለን ፣ አይሆንም እንደለመድነው እርስ በራሳችን እየተጯጯህን በሩን የምንከፍትም ከሆነ ሜንጫው የት እንደሚያርፍ ማሰቢያ ጊዜ አለንና ተመስገን ነው።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
ሳምሶን. ብ. ለንደን

የጃዋር መሀመድና የአንዳንድ አጨብጫቢዎች አደገኛ መንገድ በአጭሩ

December 31, 2013
ዋቅጅራ ሶሪ
“በእናቴ መንዜና ኦርቶዶክስ ክርስቲያን ነኝ፤ በአባቴ የአርሲ ኦሮሞ እና ሙስሊም ነኝ፤ ከኔ ወዲያ ለኢትዮጵያዊነት ምልክት ሊሆን የሚችል የለም” ጃዋር ይህን ያለው ከዓመት በፊት ወጣቱ ተንታኝ እየተባለ በኢሳት  በተደጋጋሚ ይቀርብ የነበረ ሰሞን ነው።Jawar Mohamed Muslim fundamentalist
የተመቼው እና ፖለቲካዊ ንግዱ የደራለት  ሲመስለው ከኢትዮጵያውያን ጋር ተመሣስሎና አድፍጦ የቆየው ጃዋር  መሀመድ ፤በግብጽ የመንግስት ለውጥ መደረጉን ተከትሎ የሙርሲ ባለስልጣናት በአባይ ግድብ ያደረባቸውን ንዴት በግልጽ በቴሌቪዥን  ተሰባስበው እየፎከሩ በኢትዮጵያ ላይ እርምጃ ለመውሰድ ሲዝ ቱ  ሰማ። የሙርሲ ባለስልጣናት  ከሰነዘሯቸው አማራጮች አንዱ፦” የኦሮሞ ነፃነት ግንባርን የሙስሊም ክንፍ ወይም ኦብነግን ማስታጠቅና መርዳት” የሚል መሆኑን የሰማው ጃዋር ሳይውል ሳያድር በአልጀዚራ ላይ ቀርቦ በግልጽ “ኦሮሞ ፈርስት” በማለት የኢትዮጵያዊነት ቆቡን አሽቀንጥሮ ጣለ። ሜንጫው ተከተለ፤የሙስሊሞችን የመብት ትግል ከኦነግ ጋር እያገናኘ ተናገረ፣ ኢትዮጵያውያን ከኦሮሚያ ይውጡ! እያለ መፈክር ሲያሰማ ተደመጠ…
እባብ ልቡን ዐይቶ እግር ነሳው እንዲሉ፤ አምላክ የሙርሲን መንግስት በአጭሩ ቀጨው እንጂ፤ የሙርሲ ሰዎች በስልጣናቸው ቢቀጥሉ ኖሮ የጃዋር መንገድ ወዴት ወዴት እንደነበር መገመቱ ቀላል ነው።
ከክፉ መንገዱ ሊመለስ ያልቻለው ጃዋር በቅርቡ በሳዑዲ አረቢያ በወገኖቻችን ላይ የደረሰባቸውን መከራ ተከትሎ በኖርዌይ የሚገኙ ተከታዮቹ “እኛ ኢትዮጵያውያን አይደለንም! ወንጀለኞች አይደለንም!” በማለት ስለወጡት እና የበርካቶችን ልብ ስላደማው ሰልፍ “ትክክል ነው” ብሎ ፃፈ። ሌላም ኢትዮጵያዊነትን የሚፃረር በርካታ ነገሮች ፃፈ፣ ተናገረ።
ጃዋር በአጭር ጊዜ እነኚህን ሁሉ ስህተቶች አድርጓል። ፈጽሟል። ኢትዮጵያዊ ነኝ ለሚል እና በትክክል ስለ አገር ምንነት ለገባው ሰው ጃዋርን ለመኮነን እና ለመለየት ከነዚህ ስህተቶች አንድኛው ብቻ በቂ ነበር። ሆኖም ከልጅነት እና ከእልክ የመጣ ስህተት ይሆናል፣ ልጁ ነገ ጧት ከስህተቱ ተጸጽቶ መንገዱን እየመረመረና እያሻሻለ ሊመጣ ይችላል፤ ይህን ልጅ ብናቀርበውና በትክክለኛው መንገድ መሄድ ቢችል በዕውቀቱ አገሩንና ወገኑን ሊያገለግል ይችላል..  በሚል እሳቤ አንዴና ሁለቴ  አልፈነዋል። ይህን ለፍቅርና አብሮ ለመኖር እንደተሰጠ ዕድል ስላየሁት ምንም አልመሰለኝም ነበር። እሱ ግን ከስህተቱ ሊመለስ አልቻለም። በተቃራኒው ጭራሽ እየባሰበት መጣ። ጃዋር  እየሄደበት ያለው መንገድ፤ ከኢትዮጵያዊነት ጋር ያለውን ርቀት አንዴ ብቻ ሳይሆን በተደጋጋሚ ዓየን።  የጃዋር ችግር ከግለሰቦችና ከፓርቲዎች ጋር ቢሆን የፈለገውን ያህል ዘመን ቢወስድ መታገሱና ማባባሉ ሊያስኬድ ይችል ነበር። ጃዋር ደጋግሞ እየወጋ ያለው ግን ኢትዮጵያዊነትን ነው። መንገዱ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ለማፈራረስ ነው። ምንም ለማያውቁ ታዳጊ ህፃናት የፈጠራ ድርሰት እየተረከ ትውልድ እየለያየ ነው። አገር በጥላቻ እንዲናጥ እያደረገ ነው።
ያደቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይመለስም እንዲሉ፤ ጽንፈኛው ጃዋር በአሁኑ ወቅት ከህወሀቶች ጋር በመሆን የዓፄ ምኒልክን ምስል ከሂትለር ጋር መሳ ለመሳ እያደረገ መበተን የደረሰበት ደረጃ ላይ ደርሷል። የማንነታችን (የኢትዮጵያዊነታችን) መሰረት፤ ማላገጫና መቀለጃ  መቀለጃ ሆኗል። በበኩሌ ከዚህ በላይ በኢትዮጵያዊነት ላይ መሳለቅ ያለ አይመስለኝም። ለምን ምኒልክ ተነኩ አይደለም እያልኩ ያለሁት። ህወሀቶችም ምኒልክን ለዓመታት ሲከሱ ሰምተናል። ደግሞም ምኒልክ ይህን ፈፅሟል፣ ይህን አድርጓል.. የሚለው ክስና ወቀሳ አግባብ ያለውና ለውይይት በር የሚከፍት  ስለሆነ ችግር የለውም። ጃዋርና ተከታዮቹ ግን  ወደ አደገኛ ጽንፍ በመሄድ “ምኒልክ ሂትለር ነው” የሚል  ጸያፍ፣ ርካሽና ጨርሶ ለውይይት የማይጋብዝ ቅስቀሳ ነው እያደረጉ ያሉት።  ጃዋር በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ይህን ሲያደርግ ኢትዮጵያዊነትን፣ነፃነትን፣ ማንነትን፣ እየናደና እያፈረሰ ነው ለማለት ነው የፈለግኩት። ስለሆነም ከሰፊውና ኢትዮጵያዊነቱን ለአፍታም ተጠራጥሮ ከማያውቀው ከወንድማችን የአሮሞ ህዝብ ጋር  በፍቅርና በአንድነት መኖራችን ይቀጥላል፡፡ ወይም በግልጽ ለመናገር ያህል እኛ በኢትዮጵያዊነታችን ቅንጣት ጥርጥር የሌለን ኦሮሞዎች ከወንድሞቻችን ጋር በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር በፍቅርና በአንድነት መኖራችንን እንቀጥላለን። አገር ለማፍረስና ለመገንጠል እንዲሁም በብሔረሰቦችና በሀይማኖቶች መካከል ጥላቻና ልዩነትን ለመፍጠር ተግተው እየትቀሳቀሱ ካሉት  ከጽንፈኞቹ ከነ ጃዋር ጋር  ግን ልዩነታችን ሰፍቷልና በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ልንታገላቸው ይገባል። ከወያኔ ጋር የሚደረገው ትግል፤ ልጆቹንና ጉዳይ ፈፃሚዎቹን እነ ጃዋርን ሊያጠቃልል ይገባል። አውቀውም ይሁን ሳያውቁት በወሳኝ ሰዓት የኢትዮጵያውያንን ትግልን በማደናቀፍ የወያኔን ዕድሜ የማስቀጠል ተልዕኮ እየፈጸሙ ያሉትን እነ ጃዋርን በቸልታ ልናያቸው አይገባም።
****
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ከላይ በጠቀስኳቸው ባለፉት  ሂደቶች እኔን ከጃዋር በላይ ሲገርመኝና ሲያበሳጨኝ የቆየው ታዲያ “ኢትዮጵያ አገሬ”  እያሉ ነጋ ጠባ የሚፎክሩ ሰዎች  ተግባር ነው።በተለይ አንዳንድ “አክቲቪስት” ነን የሚሉና ነፋሱ ወደነፈሰብት እየጋለቡ የሚያራግቡ  አጨብጫቢዎች፣ ነፃ ለመውጣት የምናደርገውን ትግል በመጎተትም ሆነ አገርን በማፍረስ እየተደረገ ባለው ሴራ ከጃዋር በላይ ተጠያቂ መሆናቸውን ሊያውቁት ይገባል። (ስማቸውን ያልጠቀስኳቸው ሁላችሁም ታውቋቸዋላችሁ ብዬ ነው HL & BT) ነው። ያልገባኝ ነገር  እነኚህ አክቲቪስት ተብየዎች አገር ለመገንጠል እየተጋ ካለ ጽንፈኛ ጋር የሚታከኩት ምን ትርፍ ለማግኘት ነው የሚለው ነው…  የሀገር ጉዳይ የምንሞዳሞድበት እና የምናመቻምቸው ጉዳይ አይደለም። በኢትዮጵያ ጉዳይ ቁማር መቆመርና እከከኝ-ልከክህ መጫዎት አይቻልም። ከፈለጉ ምርጫቸውን አስተካክለው ከጽንፈኛው ከጃዋር ካምፕ ይቀላቀሉ። ያ ካልተመቻቸው ደግሞ በኢትዮጵያ ባንዲራ ስም መነገዳችውን ያቁሙ።
የሀገር ጉዳይ የዕውቀት ስታንዳርድ እያወጣን  የምንሞጋገስበት፣ የምንኮፋፈስበት እና በፌስ ቡክ የምንጫዎትበት አይደለም።

በ”ዲሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ”ና በሁለት ተጨማሪ መጽሀፎች ላይ የቀረበ አጭር አስተያየት

December 31, 2013
ፋሲል የኔዓለም
በፖለቲካው ዓለም ጉልህ ስፍራ ያላቸው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ “ዲሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ” በሚል ርዕስ የጻፉትን አዲስ መጽሃፍ ያነበብኩት ዘግይቼ ነው ፤ ለመዘግየቴ ሶስት መሰራታዊ ምክንያቶች ነበሩኝ፣ አንዱና ዋናው ዶ/ሩ በተለያዩ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አመለካከት በመገናኛ ብዙሃን በስፋት ስላቀረቡ በመጽሀፉ ውስጥ እምብዛም አዲስ ነገር ያቀርባሉ የሚል እምነት ስላልነበረኝ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ዶ/ሩ ራሳቸው በከፊል የጠቀሱት ነው፣ “ በአገሪቱ ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት የሚደረገው ትግል ውስጥ ጉልህ ሚና እየተጫወተ ያለ የተቃዋሚ ድርጅት አመራር አባል መሆኑን ሲመለከት፣ ከቅንጦትም ባሻገር በተወሰነ ደረጃ “ የስራ ፈትነት” ወይንም የበለጠ ጠርጣራ ( cynic) ለሆነ ሰው “ በተግባር ስራ ለመስራት ካለመቻል “ የመጣ፤ ተግባራዊ ድክመትን ለመሸፈን የሚደረግ ሙከራ ሊመስል ይችላል” የሚለው ነው። ሶስተኛው ምክንያቴ ደግሞ ፣ ፋሽን በሚመስል መልኩ በአገር ቤት የሚኖሩ ፖለቲከኞች በተከታታይ መጽሃፎችን በማሳተማቸው ለእነሱ ቅድሚያ ለመስጠት በመፈለግ ነው።Ethiopian books review
ዶ/ር ብርሃኑን ያነበብኩት ሁለቱ ታዋቂ ፖለቲከኞች፣ ዶ/ር መረራ ጉዲና “የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምስቅልቅል ጉዞና የሕይወቴ ትዝታዎች -ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ እስከ ኢህአዴግ” እንዲሁም ኢ/ር ሃይሉ ሻውል “ ሕይወቴ እና የፖለቲካ እርምጃዬ” በሚሉ ርዕሶች ያሳተሙዋቸውን መጽሃፎች ካነበብኩ በሁዋላ በመሆኑ፣ በሶስቱም ስራዎች ላይ መጠነኛ ንጽጽር ለማድረግ አስችሎኛል።
ዶ/ር መረራ ከተማሪዎች እንቅስቃሴ እስከ ዛሬ ያለውን የአገራችንን ፖለቲካ ግሩም በሆነ መንገድ አቅርበዋል፤ መጽሃፉ ብዙ አስቂኝ ገጠመኞች የተካተቱበት በመሆኑ ፣ በቋንቋና በዓርትዖት በኩል የሚታይበትን ጉልህ ችግር አይተን እንዳላየን እንድናልፈው ያስገድደናል። መጽሀፉ በጥሩ ዓርታዒ እንደገና ቢታረምና ቢታተም “ የተዋጣላቸው” ከሚባሉት የአገራችን መጽሀፎች ተርታ የመመደቡ እድል ከፍተኛ ነው። ዶ/ር መረራ የአገራችንን ህልውና እየተፈታተነ የመጣውን፣ በ1960ዎቹ ተዘርቶ በእነ አቶ መለስ ዜናዊ አገዛዝ ተኮትኮቶ ያደገውን የብሄር ፖለቲካ መነሻ ፣ ያመጣውን ግሳንግስ እና የግሳንግሱን ማራገፊያ መፍትሄ አስቀምጠዋል። መፍትሄ ብለው ያስቀመጡትም በመጽሀፉ የመጨረሻ ገጽ እንደሚከተለው ሰፍሯል፣ “ …ለታሪክም ለህዝብም አስቀምጬ (ማለፍ) የምፈልገው መሰረታዊ ነጥብ ፣ አብዛኛው የትግራይ ሊሂቃን “ ስልጣን ወይም ሞት” ብሎ ስልጣን ላይ የሙጥኝ እስካለ ድረስ ፣ አብዛኛው የአማራ ሊህቃን በአጼዎች ዘመን የነበረውን የበላይነትን መልሼ አገኛለሁ ብሎ የሚገፋውን የሕልም ፖለቲካ እስካልተወ ድረስ፣ ብዙሃኑ የኦሮሞ ሊህቃን ኦሮሚያን ለብቻ የማውጣቱን ሕልም እስካልተወ ድረስ ሀገራችን ከአደጋ ቀጠና የምትወጣ አይመስለኝም። በሌላ ቋንቋ ለነዚህ መሰረታዊ በሽታዎቻችን መድሃኒት እስካላገኘን ድረስ ኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምም ሆነ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደርን ፈጽሞ የምታገኝ አይመስለኝም።” ( ገጽ 264)። ምንም እንኳ “አብዛኛው” የሚለው ቃል አወዛጋቢ ሊሆን እንደሚችል ቢሰማኝም ፣ ዶ/ሩ ያቀረቡት የመፍትሄ ሃሳብ በትኩረት ሊታይ እንደሚገባው ሳላስታውስ አላልፍም፤ በተለይ” እነዚህ የሶስቱ ብሄሮች ሊህቃን ህልማቸውን እንዲተው ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው?” የሚለው ጥያቄ ለእኔ ቁልፍ ይመስለኛል። ዶ/ር መረራ በዚህ ዙሪያ የተብራራ መልስ ቢሰጡ ኖሮ መጽሃፋቸውን የበለጠ ሙሉ ማደረግ ይችሉ ነበር እላለሁ።
የኢንጂነር ሃይሉ መጽሀፍ የአገራችንን የፖለቲካ ችግር ከግለሰቦች ባህሪ ጋይ ያያዘው በመሆኑ ብዙም ክብደት የሚሰጠው ሆኖ አላገኘሁትም፤ ንድፈሃሳባዊ ትንተናዎች ይጎድሉታል፣ የተዓማኒነት ችግሮችም አሉበት( በተለይ ከቅንጅት መሪዎች ጋር ስለነበረው የሽምግልና ሂደትና ከዚያ በሁዋላ ስለተፈጠሩት ኩነቶች) ፤ ለተተኪው ትውልድ የሚሰጠው ትምህርት ስለመኖሩም በእጅጉ እጠራጠራለሁ፤ በእርግጥ ኢ/ር ሃይሉ ብዙ ውጣውረዶችን አልፈው እስካሁን በህይወት ለመቆየት መቻላቸው እድለኛ ሰው እንደሆኑ በመጽሃፋ ለማየት ችለናል፣ አገራቸውን የሚወዱ ሰው መሆናቸውንም አስገንዝቦናል። ኢ/ር ሃይሉ የዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን መንገድ በመከተል መጽሀፉን በሌላ ሰው በማስጻፋቸው ስለጸሃፊነት ችሎታቸው አስተያየት ለመስጠት አያስችልም ።
የዶ/ር ብርሀኑ “ዲሞክራሲና ሁለንተናዊ ልማት በኢትዮጵያ” የሚለው ርዕስ ዘጊ ወይም ለማንበብ የማይጋብዝ ነው፤ በትምህርቱ አለም የዘለቁና የጥናትና ምርምር ወረቀቶችን ለማንበብ ፍላጎት ያላቸው ምሁራን ካልሆኑ በስተቀር፣ እንደ እኔ አይነቱ ተራ አንባቢ በርዕሱ ማልሎ መጽሀፉን ለማንበብ ስለመነሳሳቱ እጠራጠራለሁ። መጽሀፉ ውጫዊ ገጽታው ባያማልልም ውስጣዊ ይዘቱ ግን ድንቅ ነው። እንደምንም የጀመርኩትን መጽሀፍ እየተጨነቁና እየፈራሁ፣ እያዘንኩና ከራሴ ጋር እየተሟገትኩ፣ እግረ-መንገዴንም የጸፊውን እይታ፣ የትንታኔ እና የቋንቋ አጠቃቀም ችሎታ እያደነቁኩ ጨርሸዋለሁ። መጽሀፉን እንደጨረስኩ የተናደድኩበት ነገር ቢኖር ጻሃፊው የኢትዮጵያን ችግሮች እንዲያ አድርገው ካቀረቡ በሁዋላ መፍትሄውን በይደር በመተዋቸው ነው።
ከዚህ ቀደም የአገራችንን ሁለተናዊ ችግሮች ማለትም የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የተፈጥሮና የህዝብ ብዛትን በአንድነት አጣምሮ፣ በአገራችን ህልውና ላይ የደቀኑትን ፈተናዎች ቅልብጭ አድርጎ ያሳየ ከገብረህይወት ባይከዳኝ “መንግስትና የህዝብ አስተዳደር” በሁዋላ የተጻፈ መጽሀፍ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ፤ ይህን ስል ሌሎች ድንቅ የፖለቲካ መጽሃፎች አልተጻፉም እያልኩ አይደለም፤ የዶ/ር ብርሃኑን መጽሀፍ ለየት የሚያደርገው የተለያዩ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ችግሮችን ለይተው በማውጣት እርስበርስ ያላቸውን ትስስር ከግሩም ትንተና ጋር ሁሉም ሊረዳውና ሊጠቀምበት በሚችለው መንገድ ማቅረባቸው ነው ። (የምጣኔ ሀብት ትምህርት ( economics) የማይገባው ሰው እንኳ ቢሆን፣ መጽሀፉን አንብቦ ስለአገራችን ኢኮኖሚ ለመረዳት አይሳነውም።) መጽሃፉ የባራክ ኦባማን The Audacity of Hope እንዳስታወሰኝ ብገልጽ ያጋነንኩ አይመስለኝም፣ አጋነኸዋል የምትሉኝ ካላችሁም ” አንብቡትና ሞግቱኝ።
የዚህ መጽሀፍ ትልቁ መልእክት፣ ለእኔ እንደገባኝ፣ “የአገራችን ችግር ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን በመገንባት ይፈታል” የሚለው አስተሳሰብ እንደሚታሰበው ቀላል አለመሆኑንና ከአሁኑ መፍትሄ ካልተበጀለት በሁዋላ ላይ ይዞት የሚመጣው ችግር ቀላል አለመሆኑን ማሳየት ነው ። የብሄር ፖለቲካው በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ላይ የሚኖረው ተጽእኖ፣ በአገራችን ልማትን ለማምጣት የሚገጥሙ ፖለቲካዊና መዋቅራዊ ችግሮች፣ ከአካባቢ ውድመትና ከህዝብ ብዛት ጋር ተያይዞ በመጽሀፉ በዝርዝር ቀርቧል። በአሁኑ ጊዜ በአገራችን እየታየ ያለውን የገቢ አለመመጣጠንም 1500 ብር የሚያወጣውን የአንድ መለኪያ ውስኪ ግብዣ በምሳሌነት በማንሳት በደቡብ አፍሪካ እንደታየው በአገራችንም ለወደፊቱ ይዞ ሊመጣ የሚችለውን ጣጣ ጸሀፊው በደንብ አሳይተውናል።
መጽሀፉ የውጩ ፖለቲካ በአገራችን ፖለቲካ ላይ የሚያሳርፈውን ተጽዕኖ እንዲሁም የአለማቀፉ የንግድ ስርዓት በኢትዮጵያ እድገት ላይ ያለውን ተጽእኖ ቢያካትት ኖሮ የበለጠ ድንቅ ይሆን እንደነበር አስባለሁ ። ከዚያ በተረፈ ግን መፍትሄዎቹ በሌላ ክፍል እንደሚቀርቡ መገለጹ በመጽሀፉ ላይ በቂ ክርክር እንዳይነሳ ያደረገው ይመስለኛል። በመጽሀፉ በቀረቡት ችግሮች እና ትንተናዎች ላይ ተቃውሞ የሚኖረው ሰው ይኖራል ብየ አላስብም፣ ተቃውሞ የሚነሳው ችግሮችን ለመፍታት በሚቀርቡት የመፍትሄ ሀሳቦች ላይ እንደሚሆን በመገመት ቀጣዩ መጽሃፍ አወያይ ( አካራካሪ) ይሆናል እላለሁ።
ስለአገራቸው እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ ሁሉ መጽሀፉን እንዲያነቡት እመክራለሁ ( የዶ/ር መረራንም ጨምሮ)። በተለይ በሰላማዊው የትግል ሜዳ ለመፋለም የሚያስቡ ጀማሪም ሆኑ ነባር ፖለቲከኞች የብርሀኑን መጽሀፍ በማንበብና በምርጫ ክርክር ወቅት ይዞ በመቅረብ ( የመፍትሄው መጽሀፍ ቶሎ እንደሚደረስ በመገመት) ምርጫውን ሊያሸንፉ እንደሚችሉ አልጠራጠርም፤ ስልጣኑን ይረከባሉ ብዬ ባላስብም።

Sunday 29 December 2013

ዛሬ አረና/መድረክ በሽሬ የሚያደርገው ስብሰባ ጉዳይ… (ከትግራይ)

(ኢ.ኤም.ኤፍ) በዛሬው እለት የአረና/መድረክ ፓርቲ በሽሬ እንዳስላሴ ከተማ ስብሰባ ለማድረግ ፈቃድ አግኝቶ፤ ይህንኑ ህዝባዊ ስብሰባ ያደርጋል ተብሎ እየተጠበቀ ነው። ሆኖም በስፍራው የሚገኘው የድርጅቱ ህዝብ ግንኙነት፤ አብርሃ ደስታ እንደዘገበው… ስብሰባው ከመጀመሩ በፊት የህወሃት አባላት መግቢያው በር ላይ ግርግር እየፈጠሩ ናቸው። እንዲህ በማለት ይቀጥላል። “ህዝባዊ ስብሰባውን ለመጀመር አዳራሹ ሲከፈት ህዝብ በስብሰባው ለመሳተፍ መግባት ሲጀምር አስተዳዳሪዎቹ ደንግጠው ‘በስብሰባው መሳተፍ የሚችለው የቀበሌ መታወቅያ ያለው ሰው’ ብቻ መሆን እንዳለበት አወጁ። ይህ ብቻም አይደለም፤ መታወቂያውን እየመዘገቡ ለማስገባት ወሰኑ። ህዝቡ ተቃወመ። የዓረና አመራር አባላትም ድርጊቱ ተቃወሙ። መታወቂያ የሌለው እንዳይገባ ስለተወሰነ ብዙ ሰው ተቃውሞ ስላነሳና መግባት ስለፈለገ የአዳራሹ መግብያ በር ተዘጋ። አሁን የተፈቀደልን አዳራሽ ዝግ ነው። ዓረና ስብሰባው በአዳራሹ በር ባለው ሜዳ ለማካሄድ ወስኗል። ባደራሹ በር አከባቢ ብዙ ህዝብ አለ። ካድሬዎቹ ህዝቡን ለመበተን እየፈተኑ ነው። (ኢ.ኤም.ኤፍ ሁኔታውን እየተከታተለ ማቅረቡን ይቀጥላል)

እኔ ኣላውቅም ፈራሁ ጁሃር (ሄኖክ የሺጥላ )

የበደሌ ቢራ ፋብሪካ ከ ኣዲስ ኣበባ 483 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ኢሉ-ኣባ-ቦራ ( Eloo The father of Holstein Friesian) ኢልባቡር ከተማ በሁለት መቶ ሃምሳ ሺ ስኩውር ሜትር ይዞታ ላይ ስራውን እንደ ኣውሮጳውያን ኣቆጣጠር በ 1993 ማከናወን የጀመረ ትልቅ የቢራ ማምረቻ ድርጅት ነው።
ኢሊባቡር መልካም ምድራዊ ኣቀማመጡም ሆነ ምድራዊ ልምላሜው፥ እንደ በቆሎ ፤ ገብስ፤ ጤፍ፤ የቅባት እሎች፤ ማር፤ ከነ ቦራ ደሞ ወተት፤ ቅቤ እና ወዘተ የሚዘራባት፤ የሚታጨድባት፤ የሚቆረጥባት፤ የሚታለብባት ሃገር እንድትሆን ኣድርጉዋታል።
ኢሊባቡርን የጽሁፌ መንደርደሪያ ኣደረኩ እንጂ ዋናው ነጥቤ እሱ ኣይደለም። ዛሬ መናገ ወይም መጻፍ የፈለኩት ቴዲ ኣፍሮ በቅርቡ በመላው ኢትዮጵያ የሙዚቃ ዝግጅቱን እንዲያሳይ ወኪል የሆነውን የበደሌ ቢራን ያለመጠጣት ኣድማ ( boycotting) በመላው ኢትዮጵያ ይደረግ ዘንድ ኣንዳንድ ግለሰቦች የጀመሩትን ነገር ሰምቼ፤ ለምን በደሌን፤ ለምን ቴድን የሚል ጥያቄ ለሚጠይቁ፤ መልስ የሚመስለኝን ለመተየብ፤ ከተቻለም ለማሳየት መመኮር በመሻቴ ነው ።
ቴዲ ኣፍሮ በቅርቡ በ ጋዜጣ ላይ ስለ ኣድዋ ድል በሰጠው ኣስተያየት የተቆጡ፤ የተቀየሙ ግለሰቦች፤ ቴዲ ኣፍሮ ጥቁር ሰው ብሎ ንጉስ ሚኒሊክን፤ ከዛም በላይ የኣድዋ ድልን በመዘከሩ የተበሳጩ የህብረተሰብ ኣካሎች፤ ቴዲ ኣፍሮ ከዚህ ቀደም ጃ ያስተሰርያል ብሎ በመዝፈኑ ቂም የቁዋጠሩ ሰዎች፤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በሊግ ኦፍ ኔሽን በ 1936 የኢጣልያንን የተለከለ የኬሚካል መሳሪያ መጠቀምን በመቃወማቸው፤ ኢትዮጵያን የ ዩናትድ ኔሽን ኣባል በማድረጋቸው፤ ቅራኔዎችን ኣብርደው ያፍሪካን ህብረት በመመስረታቸው፤ ለነዚህ ጉልህ ኣስተዋጾዎቻቸው በመዝፈኑ፤ ለነዚህ ለተጠቀሱት መልካም ስራቸው መታሰቢያ የጭንቅላቱ ውጤት የሆነውን ምዚቃ በማበርከቱ፤ ቴዲ ኣፍሮ ፤ ኣቀንቃኝ ና ኣዝማሪ ፤ ገጣሚና ሰኣሊ፤ ሃያሲና ደራሲ፤ ጸሃፊ ተውኔቱና ብላታው፤ ኣፉን በለጎመበት ዘመን፤ በብእሩ የታሪክ ጋሻ፤ በግጥሙ ለቆሰለ ታሪክ ማገገሚያ፤ በዘፈኖቹ ( ከ ማሊ ሱፊዎች ባልተናነሰ መልኩ) የነብስን ክር እየተጫነ ያላስለቀሰው፤ ያላስተከዘው፤ ሰው እንደሌለ የገባቸው ሰዎች፤ በይበልጥም የኣድዋ ድል፤ የጥቁር ኣንበሳዎች ድል መሆኑን ያሳየበት በመሆኑ እና ይህም የሚያማቸው ሰዎች፤ ዛሬ በደሌ ቢራ ቴዲ ኣፍሮን ስፖንሰር ስላደረገ፤ በደሌ ቢራን ያለመጠጣት ኣድማ ጠርተዋል። ኣሁን ቴዲ ኣፍሮን ኣብዶ በረንዳ ( የጫት ማከፋፈያ በረንዳ ነው) ቢሆን ስፖንሰር ያረገው ምን ሊሉ ነበር።። ባረገው እና የተከታዮቻቸውን መልስ ባየን። ኣንድ ጊዜ ቆይ ጠብቁኝ ሳቄ መጣብኝ ያለው ተናጋሪ ማን ነበር።
ኣዲሱ የቴዲ ኣፍሮ ኣልበም ( ጥቁር ሰው) የብዙዎቹን እትዮጵያዊያኖች ድምጽ ያስገኘለትን ያህል፤ ንጉስ ሚኒሊክ በድሎናል፤ ጡታችንን ቆርጦዋል፤ ወዘተ ወዘተርፈ ለሚሉት ደሞ፤ ከሚኒሊክ መፈጠር፤ ከታሪክ ኣንቅጽነቱና ኣኩሪ ገድሉ ጋር የጀመሩትን እጹብ ጸብ ውሃ የሚደፋበት በመሆኑ፤ ጠላት ሊያፈራበት እንደሚችል መገመት ብዙም ኣይዳግትም። እናም ‘ነዚህ ሰዎች ቀደም ብዬ እንደ ጠቀስኩት፤ በደሌ ቢራን ያለመጠጣት ኣድማ እናድርግ እያሉ ነው። ልክ ናቸው፤ ህዝብ በጥላቻም በቢራም ሰክሮ እንዴት ይሆናል፤ ባንዱ ብቻ ይበቃልና።
በነገራችን ላይ ይህንን ኣድማ ለማስመታት ከሚራወጡት እና ከሚሯሯጡት ሰዎች መሃከል ኣንዱ ጁሃር መሀመድ መሆኑን ሰምቼ ኣፍሬ ጥፍሬ ውስጥ ልገባ ነበር። ባንድ ወቅት ይሄ ወጣት ፖለቲከኛ ስለ ራሱ ሲናገር “እኔ እናቴ መንዜና የኦርቶዶክስ ክርስቲያን ነች ኣባቴ ደሞ ኦሮሞና ሙስሊም ነው ፤ ታዲያ ከኔ በላይ ኢትፖጵያዊነትን የሚወክል ምንነት ኣለ ወይ” ብሎ ነበር። መልሱ ሊሆን ይሚችለው ጁሃርዬ በውነትም የለም፤ እንዳንተው ኣቶ መለስም እኮ የተላቀቀ ነገርን ማጣበቅ የሚችል (ኡሁ የሆነ) (UHU…glue) ደም ነበራቸው፤ ግን ደሙ ሳይሆን የደሙ ባህሪ ነው ወሳኙ ነገር። የተሸከምነው ደም ሳይሆን በውስጣችን ያፋፋነው ስብዕና ነው ማንነት ፤ ማንነት ስራ ነው እንጂ ኣንተ እንዳልከው የ-ኢ-ተጎራባች ዘር ደም ውህደት (ኬሚስትሪ ውጤት ኣይደለም)፤ ክርስቶስ ( ኤሳው… ኣለይሁ ሰላም) በ-በረት ተወለደ ብለን እናምናለን፤ ግን እንደ ሰብኣዊ ፍጡር በ-በረት መወለዱ ሳይሆን ሰው ሆኖ ሲኖር ያደረገውን ነገር ነው የምናስበው፤ ስለ ነብዩ ሙሃመድ (ሰ.አ.ወ) ኣንድ ሙስሊም ሲያስብ ስለ ዘራቸው ሳይሆን ስለ ስራቸው ነው የሚያስበው ብዬ ኣስባለሁ ። ባንድ ወቅት ይሄው ሰው፤ ፹ ከ ፻ የሚሆነው የሃገሬ እስላም ኦሮሞ ነው፤ እናም የእሮሞ ህዝብን ኢምፓወር ማድረግ፤ እስልምናን ኢምፓወር እንደማረግ ነው ኣለን፤ ለመስማት ኣይደል የተፈጠርነው እናም ሰማነው፤ ባሜጃ ኣለን ዝም ብለን ሰማነው፤ ቀጥሎም ኢትዮጵያ ኣውቶ ኦፍ ኦሮሚያ ኣለን እሱንም ሰማነው። በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ኣውት ኣፍ ኦሮሚያን ወደ ፈርንጅኛ ስቀዳው ( the child give birth of her mother) ኣይመስላችሁም ? ለመተርጎም የተገደድኩት የመጀመሪያው ራሱ እንግሊዘኛ መሆኑን ስለ- ተጠራጠርኩ ነው። ለነገሩ ስታንፈርድና ኮሎምቢያ ዩንቨርስቲ እኮ መፈክር ኣያስተምሩም።
እና ዛሬ በደሌ መጣ እና ወንድሜ ጁሃር ሰማኒያ ከመቶ ካለው ሃሳብ ጋ ግንባር ለግንባር ተጋጨ ( head on collusion) እናም ሁለት የሚጋጩ ነገሮችን እንግዲህ እናስተውላልን።
፩) መቼም ፹ ከመቶው እስላም ኦሮሞ ነው ብለኽን፤ ኣንተም በዘር ብቻ ሳይሆን በእምነትም ጭምር ጠበኽ፤ ኣልገባኝም ታዲያ እንዴት ነው፤ እነማን ቦይ ኮት እንዲያረጉልኽ ነው ጥሪውን ያቀረብከው፤ ፳ ፐርሰንቱ እስላም ያልሆነው ኦሮሞ ? ደሞ ከ ፹ ከመቶ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ውስጥም ቢሆን ኣዲስ የበደሌ ኣድመናኛ ማግኘት ይቸግራል ብዬ ኣስባለሁ፤ ምክኒያቱም እነሱ ላንተ ሲሉ ሳይሆኑ ለዲናቸው ሲሉ ድሮም እንዲህ ኣይነቱን ነገር ይነኩት ነበር ብዬ ኣላስብም፤ በፍጽም ኣያደርጉትም፤ ታዲያ የማይጠጡ ሰዎችን ነው ኣድማ የጠራነው፤ ወይስ ሙሉ የኢትዮጵያዊነት ማሳያ ምሳሌ እንድትሆን ያደረገችህ የመንዜዋ እናትህን ዘመዶች፤ እኔ ኣላውቅም ፈራሁ ሄኖክ ነው ያለኝ የልጅነት ጉዋደኛዬ፤ ባንድ ትልቅ የውሃ ጉድጉዋድ ውስጥ እንሹለክ ስለው። እኔ ኣላውቅም ፈራሁ ጁሃር።
ዛሬ ጀርመን ያላትን ቅርጽ እንድትጠብቅ ወይም እንዲኖራት ያደረገው ኦቶ ቮን ቢስ ማርክ፤ የደም ትግል ውጤት ነው። ታዲያ ጀርመኖች በ ቢስ ማርክ ተናደው ፒሊሲነርን ( የጀርመን ታዋቂ ቢራ ነው) ቦይ ኮት እናርግ ኣላሉሉም። በፈረንሳይ እንዲህ የሚባል ታሪክ ኣለ፤ በኣሜሪካም፤ ኣረ ሆመር በጥንታዊያኖቹ የግሪክ ዘመን ስለነበረው ጦርነትም ጽፎዋል፤ ስለ ስርኣቱ፤ ስለ ኣገማምኖን እና የወንድሙ መንግስት፤ ስለ ሄለናዊው ስርኣት፤ ከዚያም በሁዋላ እነ ዳንቴ ስለ ጻፉት ስለ ዲቫይን ኮሜዲ፤ ፍሬድሪክ ዊልሃልም ኒቺ ስለተራቀቀበት የማህበረሰብ ስነ ልቦና፤ እነ ኣልበርት ካሙ ስለጻፉለት የፈረንሳይ ማህበረስብ እና በየስራቶቹ ውስጥ ስለ ነበርው ፍዳ፤ እነ ልዮ ቶሎስቶይ በሰላ ብእራቸው ስለዘገቡት የሩሲያ የጭቆና ቦለቲካ፤ እነ ፓብሎ ፒካሶ ጉሬንሽያ ብለው ስለገለጹት የስፔን ከተማ ስለ ስንቱ ለዚህ ለወጣቱ ፖለቲከኛ እንንገረው እስኪ ባክህ ጁሃርዬ ገረፍ ገረፍ ኣርጋቸው (በቃ እንደውም ለዚህ ክረምት ለፐርሰናል ዲቨሎፕመንት…ትመለከታቸው ዘንድ እጠይቅ፤ሃለሁ (ማሳሰቢያ በኣብዛኛው በኣማራ ጻሀፊ ኣይደልም የተጻፉት ቢሆኑም ደሞ ኣነተ ኣምሳ ፐርሰንት ኣማራ ኣይደለህ እንዴ፤ የምሬን እኮ ነው)
በታሪክ ላይ ጥላሸት መቀባት በፍጹም ለማንም ኣይሳካም፤ ወደድንም ጠላንም፤ ጠቅልለን የምንጎርሰውን እንጀራ የፈጠሩት ኣባቶቻችን ናቸው፤ ለሆዳችን ያለን ቅርበት ለታሪካችንም ይኑረን። ቴዲ እንዳለው ክፉውን በክፉ ለመመለስ ማሰብ ሌላ ክፉነት ነው። ሁለቱ ደሞች እንደ ደም ይሰሩ፤ ያስቡ ዘንድ ሰው እንሁን።

በደቡብ ሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን መንግስት እንዲታደጋቸው እየተማጸኑ ነው

ዩኒቲ በሚባለው ግዛት ውስጥ የሚገኙ ኢትዮጵያን በጦርነት አጣብቂኝ ውስጥ መገኘታቸውንና ህይወታቸው አደጋ ውስጥ መውደቁን ተናግረዋል።
በግዛቱ ውስጥ በአንድ የመንገድ ስራ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው የሚሰሩ 6 ኢትዮጵያውያን እንደተናገሩት በሁለቱ ተፋላሚ ሀይሎች መካከል የሚደረገውን የተኩስ ልውውጥ ለማምለጥ ያለፉትን ሁለት ቀናት በከባድ ማሽነሪዎች ውስጥ በመደበቅ ለማሳለፍ ተገደዋል። በአካባቢያቸው 2 ኢትዮጵያውያን መገደላቸውንና 3ቱ ደግሞ መቁሰላቸውን ተናግረዋል።
እስካሁን ድረስ ምን ያክል ኢትዮጵያውያን እንደሞቱ ባይታወቅም፣ የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ በአገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማነጋገር እንደዘገበው የሞቱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እስከ ታህሳስ 17፣ 2006 ዓም ድረስ ቢያንስ 30 ይደርሳል።
ኢሳት ያነጋገራቸው ኢትዮጵያውያን እንደሚሉት መንግስት እስካሁን ድረስ ዜጎቹን ለመሰብሰብ ጥረት እያደረገ አይደለም። ጎረቤት አገሮች ኬንያና ኡጋንዳ ዜጎቻቸውን ሲያስወጡ የኢትዮጵያ መንግስት ምንም አይነት እርምጃ ለመውሰድ አለመፈለጉ ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኗል። ኢትዮጵያውያን አሁንም መንግስት እንዲደርስላቸው ጥሪ አቅርበዋል
በጆንግሌ ግዛት የተደፈሩ 4 ኢትዮጵያውያን ጁባ ውስጥ በሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሆስፒታል ውስጥ ህክምና እንዲያገኙ ተድርጓል።x
ይህ በእንዲህ እንዳለ የምስራቅ አፍሪካ መንግስታት በናይሮቢ ኬንያ ያደረጉትን ስብሰባ ተከትሎ የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር በግላቸው ተኩስ እንደሚያቆሙ አስታውቀዋል። አገራቱ የመንግስትን እርምጃ የደገፉ ሲሆን፣ የኬንያው መሪ ኡሁሩ ኬንያታ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን መሪ በሀይል ለማውረድ የሚደረገውን እንቅስቃሴ እንደማይደግፉ ገልጸዋል።
የተቃዋሚዎች መሪ የሆኑት ሪክ ማቻርም በተመሳሳይ መንገድ ተኩስ እንዲያቆሙ የምስራቅ አፍሪካ መሪዎች ተማጽኖ አሰምተዋል። መሪዎቹ በሚቀጥሉት 4 ቀናት ፊት ለፊት ተገናኝተው እንዲወያዩ ኢጋድ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።እስካሁን በተካሄደው የእርስ በርስ ጦርነት ከ1 ሺ በላይ ሰዎች መገደላቸውን አለማቀፍ የመገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል;፡

በሳውድ አረቢያ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ውስጥ ዘረኝነትና ሙስና ተስፋፍቷል ተባለ

-ኢሳት ከቆንስላው ባገኘው የውስጥ መረጃ በሃላፊነት ላይ የተመደቡት አምስቱ ዲፕሎማቶች በዘረኝነትና በሙስና ከመዘፈቃቸው ም በተጨማሪ ሊሴ ፓሴ ለማውጣት ወደ ቆንስላው የሚደውሉትን ስደተኞች በስብሰባ ሰበብ የሉም በማስባል ጉዳያቸውን እያስፈጸሙ እንደልሆነ ተመልክቷል። ከአንድ ወር በፊት ከ160 ሺ በላይ ህዝብ የተፈናቀለበትን ችግር ለማወቅ በቆንስላው የተገኙትና ከዲፕሎማቶች ውጭ ያሉ ሰራተኞችን ብቻ በመሰብሰብ ” የችግሩ ምንጭ ምንድነው በማለት?” የተወያዩት የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፣ ለዚህ ሁሉ ችግር መፈጠር መንስኤ በሆኑት ዲፕሎማቶች ላይ አፋጣኝ እርምጃ እንደሚወስዱ ተናግረው የነበረ ቢሆንም እስካሁን የወሰዱት እርምጃ አለመኖሩ ታውቋል።
“የመኖሪያ ፈቃድ የላችሁም” በሚል ምክንያት ኢትዮጵያውያን ከሳውድ አረቢያ እንዲወጡ ሲታዘዙ፣ ከዚህ ቀደም በቋሚነት ተቀጥረው ይሰሩ የነበሩ 24 የቆንስላው ሰራተኞችን የሚያግዙ በአገሪቱ የሚኖሩ 40 ድጋፍ ሰጪ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ህዳር 12 ቀን 2006 ዓም ለ3 ወራት በሚቆይ የኮንትራት ጊዜ ተቀጥረዋል። ከተቀጠሩት 40 ሰራተኞች መካከል 30 ዎቹ  ሰራተኞች የተቀጠሩት የዲፕሎማቶች የቅርብ ቤተሰቦችና ዘመዶች ናቸው። አብዛኞቹ ሰራተኞችም የተቀጠሩት የዘር ማንነታቸው እየታየ ሲሆን ከተቀጣሪዎቹ መካከል እንግሊዝኛ፣ አማርኛና አርበኛ ከማይናገሩት ጀምሮ ማስተርስ እና የመጀመሪያ ዲግሪ ያላቸው ይገኙበታል።
ከተቀጣሪዎቹ መካከል የተሻለ የትምህርት ደረጃና ብቃት ያላቸው 10 ሰዎች ከአንድ ወር በሁዋላ ታህሳስ 14 ቀን  ተመርጠው እንዲባረሩ ሲደረግ 30 ዎቹ የዲፕሎማቶች ቤተሰቦች እንዲቆዩ ተደርጓል። አስሩ ሰዎች እንዲባረሩ የተደረጉት ከመባረራቸው ከአንድ ሳምንት በፊት  ከውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ሰባቱበቋሚነት እንዲቀጠሩ ደብዳቤ መላኩን ተከትሎ ፣ በትምህርት ደረጃና በችሎታቸው የተቀጠሩትን አስቀድሞ በማባረር እና ውድድር ውስጥ እንዳይገቡ በማድረግ የዲፕሎማቶችን ቤተሰቦች  እድሉን እንዲያገኙ ለማድረግ መሆኑ ታውቋል። በቆንስላው ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ከ1 ሺ 300 እስከ 1 ሺ 500 ሪያድ የሚከፈላቸው ሲሆን፣ ለአዲሶቹ የሚከፈላቸው 2000 ሪያድ ነው።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ የቆንስላውን ዲፕሎማቶች በማግለል ሰራተኞችን በዝግ ስብሰባ ያነጋገሩ ሲሆን፣ ሰራተኞችም የሳውድ አረቢያ ችግር ከመፈጠሩ በፊት የነበረውን ችግር አንድ ባንድ ዘርዝረው በድፍረት ተናግረዋል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አፋጣኝ እርምጃ እንደሚወስዱ ለሰራተኞች ቃል ገብተው የሄዱ ቢሆንም እስካሁን ምንም እርምጃ ባለመውሰዳቸው ችግሩ ተባብሶ መቀጠሉ ታውቋል።
አንደኛው ዲፕሎማት 9 ዘመዶቹን ሲያስቀጥር፣ ሌላዋ ደግሞ 8 ቤተሰቦቿንና የብሄሩዋን ልጆች ብቻ በመምረጥ አስቀጥራለች። ቀሪዎቹ 13 ሰዎች ደግሞ የሌሎች ዲፕሎማቶች ዘመዶችና ወዳጆች ናቸው።
ዲፕሎማቶቹ በሳውድ አረቢያ የሚኖራቸው ቆይታ ከ4 አመት የማይዘል በመሆኑንም ጊዜያቸውን ሀብት በማከማቸት እንደሚያጠፉ ታውቋል። ምንም እንኳ መንግስት ወደ ሳውድ አረቢያ የሚደረገው ህገወጥ ጉዞ እንዲቆም ቀደም ብሎ መመሪያ ቢያስተላልፍም፣ በሳውዲ በሚገኘው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ሊቀመንበር አማካኝነት የህገወጥ የሰዎች ዝውውር በዲፐሎማቶች አማካኝነት ሲካሄድ መቆየቱን መረጃው ያሳያል።
በእስር ቤት ውስጥ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሊሴ ፓሴ እንዲሰራላቸው በተደጋጋሚ ሲጠይቁ፣ ዲፕሎማቶቹ ” ስብሰባ ላይ ናቸው” በሚል ለጥያቄያቸው መልስ እንደማይሰጡ መረጃው ያመለክታል።  የሳውዲው ችግር እንደተፈጠረ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለዲፕሎማቶቹ በሰጡት ጥብቅ ትእዛዝ ለአንድ ወር ያክል ፈጣን አገልግሎት በመስጠት ከ130 ሺ በላይ ሰዎች ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ቢችሉም፣ በአሁኑ ጊዜ ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው መመለሳቸው ታውቋል። በእስር ቤቶች ውስጥ የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን አሁንም ሊሴ ፓሴ እንዲሰራላቸው በተደጋጋሚ ወደ ቆንስላው ስልክ እንደሚደውሉ ቢታወቅም፣ አገልግሎት እያገኙ አለመሆኑ ግን ታውቋል።

Thursday 26 December 2013

የፍርሃት ባህልን እያነገሰ ያለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት ወደ ኋላ

ክፍል አንድ
ፍርሃት የግለሰቦች ባህሪ መገለጫ ስለሆነ በማኅበረሰብ ደረጃ የሚኖረውን ገጽታ እና ትርጓሜ ማስቀመጥ ያስቸግራል። አንዱ ሰው የሚፈራውን ነገር ሌላው ላይፈራው ስለሚችል ፍርሃት እንደ የግለሰቡ ባህሪ እና ጥንካሬ ወይም ስነ-ልቦናዊ ሁኔታ የተለያየ መልክ ይኖረዋል። ይሁንና በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች የሚጋሩት ባህልና ስነ-ልቦናዊ ሁኔታ እንደመኖሩ ሁሉ የሚጋሩትም ፍርሃት ወይም ደስታ ወይም ሃዘን ወይም ድፍረት ወይም ሌሎች ባህሪያት ይኖራል። በዚህም ምክንያት አንዳንድ ሰዋዊ ባህሪያት ለአንድ ማህበረሰብ ወይም ለበርካታ ሰዎች የወል መገለጫ ተደርጎ ሲገለጽ ይስተዋላል። ‘የዚህ አካባቢ ሰዎች ጀግኖች ወይም ጸብ ፈሪዎች ወይም እሩህ ሩህዎች ወይም ጨካኞች ወይም ቂመኞች ወይም ገራገሮች ወይም ተንኮለኖች ወይም ጎጠኞች ወይም ሌላ ባህሪ ያላቸው ናቸው’ የሚል አገላለጽ የተለመደ ነው። ይህ አይነቱ አነጋገር ሳይንሳዊ መሰረት ያለው ባይሆንም በአካባቢው ላይ ጎላ ብለው በሚታዩ ሰዎች ላይ ተደጋግሞና ተዘውትረው የሚታዩ ተመሳሳይ ባህሪያት የአካባቢው ሰው ሁሉ መገለጫ ተደርገው ስለሚወሰዱ ድምዳሜው ለስህተት የተጋለጠ ሊሆን እንደሚችል ከወዲሁ ለመግለጽ እወዳለሁ። ከዚህ መንደርደሪያ በመነሳት በዚህ ጥልቅ ጥናት ባላካሄድኩበት ነገር ግን ደጋግሜ ሳብሰለስለው በቆየሁት የፍርሃት ባህል እና በኢትዮጵያ የፖለቲካ ድባብ ዙሪያ ያለኝን ምልከታ ለአንባቢያን ለማካፈልና በጉዳዩም ላይ ለመወያየት ወሰንኩ።
በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ የፍርሃት ድባብ እንዲሰፍን እና ከዚያም አልፎ ባህል እንዲሆን ምክንያት ከሆኑት በርካታ ነገሮች መካከል የተወሰኑትን ልጥቀስና በእኛ ማኅበረሰብ ውስጥ ያላቸውን ገጽታ በመጠኑ ለመዳሰስ እሞክራለሁ። በስነ-ልቦና ጠበብቶች ከሚጠቀሱት ዋና ዋና የፍርሃት ምንጮች መካከል፤ ነፃነትን ማጣት፣ ነገ የሚሆነውን ማወቅ አለመቻል፣ የህሊና እና የአካል ቁስልን ባስከተሉ ትላንቶች ውስጥ ማለፍ፣ የማያቋርጥ ብስጭት ወይም ንዴት፣ ድህነት በሚያስከትለው ስቃይ ውስጥ መማቀቅ፣ አጋር እና አለኝታ ማጣት፣ በሌሎች ክፉኛ መነቀፍ፣ መንጓጠጥ፣ መጠላት እና መገለል፣ በሚኖሩበት ማኅበረሰብ ዘንድ ተቀባይነትን ማጣት፣ የሞት አደጋን ማሰብ፣ ሽንፈት ወይም ስኬት አልባ ሆኖ መቆየት፣ እና ሌሎችም ይገኙበታል። ከእነኝህ መክንያቶች ውስጥ የአንዱ መከሰት አንድን ሰው ወደ ፍርሃት ውስጥ ሊከት እንደሚችል ጥናቶች ይጠቁማሉ። እነኝህ ምክንያቶች ተደራርበውና በአንድ ጊዜ በአንድ ሰው ወይም በአንድ ማኅበረሰብ አባላት ላይ ሲከሰቱና ዕልባት ሳያገኙ እረዘም ላለ ጊዜ ሲቆዩ ደግሞ አደጋቸው የከፋ ነው የሚሆነው። ከዚህም በመነሳት ወደ እኛ ማህበረሰ ስንመለስ በግላችንም ሆነ በጋራ ህይወታችን ከላይ ከተጠቀሱት የፍርሃት መንሰዔዎች መካከል ስንቶቹ በህይወታችን ውስጥ ተከስተዋል፣ ስንቶቹን በአሸናፊነት አለፍናቸዋል፣ ስንቶቹስ ዛሬም ድረስ አብረውን ይኖራሉ፤ የሚሊቱን ጥያቄዎች እያንዳንዱ ሰው እራሱን እንዲጠይቅ እየተውኩ በወል በምንጋራቸው ጥቂት የፍርሃት መንሰዔዎች ላይ ላተኩር።
የነፃነት ማጣት
ሰብአዊ መብቶች በገፍ በሚጣሱበት እና ዜጎች የሰውነት ክብራቸው ተገፎ፣ ተዋርደውና ነፃነታቸውን ተነጥቀው በሚኖሩበት አገር ሁሉ ፍርሃት ትልቁ ገዢ ኃይል ነው። በእንዲህ ያለው ማህበረሰብ ውስጥ የፍርሃት ሰለባ የሆኑት እና ነፃነት አልባ ሕይወትን የሚገፉት ተጨቋኞቹ ብቻ ሳይሆኑ ጨቋኞቹም ጭምር ናቸው። ተጨቋኖቹ በግፍ ልንገደል፣ ልንታሰር፣ የስቃይ ሰለባ ልንሆን፣ ታፍነን ልንሰወር፣ ከሃገር ልንሰደድ፣ ከሥራ ልንባረር፣ ንብረታችን ሊወረስ፣ በግዞት ከቦታ ቦታ ልንዛወር፣ ከቅያችን ልንፈናቀል፣ በሃሰት ክስ ልንወነጀል፣ ደሞዛችንን ልንነጠቅ፣ ከሥራ ደረጃችን ልንቀነስ፣ ወዘት … እያሉ አደጋዎችን እያሰቡ በሽብርና በፍርሃት ቆፈን ተይዘው ‘ጎመን በጤና’ በሚል የማፈግፈጊያ ስልት መብቶቻቸውን አሳልፈው በመስጠት የግፍ እንቆቋቸውን እየተጎነጩ መራራ ሕይወታቸውን ይመራሉ። ጨቋኞቹም ይህን በነፍጥ እና በሕግ አንበርክከው ነፃነቱን የነጠቁትና ለስቃይ የዳረጉት ሕዝብ በአንድ አይነት ተአምር በቁጣ ገንፍሎ ከተነሳ አንድም ቀን እንደማያሳድራቸው ጠንቅቀው ስለሚያውቁ እያንዳንዱን ደቂቃና ሰዓታት ልክ እንደ ተጨቋኙ በፍርሃት እና በሽብር ነው የሚያሳልፉት። ከቦታ ቦታ ሲንቀሳቀሱም፣ የእለት ሥራቸውንም ሲያከናውኑ፣ ሲተኙም ሆነ ሲዝናኑ በሠራዊትና በመሣሪያዎች ጋጋታ ታጅበው ነው። ምናልባትም ከተጨቋኞቹም በባሰ ፍርሃት ውስጥ ነው የሚኖሩት።
ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሁኔታ በቅጡ ያጤንን እንደሆነ ገዢና ተገዢ እርስ በእርስ የሚፈራሩበት፤ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ ተቃዋሚዎች መንግሥትን የሚፈሩበትና አንዱ ሌላውን የማያምንበት ሁኔታ ነው የተፈጠረው። የመንግሥት ፍርሃት ከተቀናቃኝ የፖለቲካ ኃይሎች አልፎ የሲቪክ ማኅበረሰቡን፣ የሙያ ማኅበራትን፣ ነጋዴውን፣ ምሁራኑን፣ ገበሬውን፣ ወጣቱን እና ሌላውንም የኅብረተሰብ ክፍል ክፉኛ የሚፈራበትና በቁራኛ የሚከታተልበት፤ እነሱም መንግስትን እንደ ተናካሽ አውሬ የሚፈሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በመንግሥትና በሕዝቡ፣ በተቃዋሚ ፓርቲዎችና በመንግሥት፣ በሕዝቡና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ካለመተማመን የመነጨው ይህ ጥልቅ ፍርሃት በአገሪቱ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ጥቁር ደመናን ጋርዷል። በገዢው ኃይል በኩል ያለውን የፍርሃት ድባብ ለመመልከት በየጊዜው መንግሥት የሚወስዳቸውን የኃይል እርምጃዎች፣ የሚያወጣቸውን የማፈኛ ሕጎች፣ እያጠናከረ የሄደውን የሥለላና የአፈና መዋቅር፣ በመገናኛ ብዙሃን የሚያሰራጫቸውን ሕግን ያልተከተሉ እና በሽብር መንፈስ የተዋጡ መግለጫና ዘገባዎችን መመልከት በቂ ነው። በተለይም የ1997ቱን ምርጫ ተከትሎ የተቀሰቀሰው የሕዝብ ቁጣ ያስደነበረው የወያኔ መንግሥት ከላይ የጠቀስኳቸውን እና አጥብቆ የሚፈራቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች ቀፍድዶ ለመያዝና እንቅስቃሴዎቻቸውን ለመገደብ ባወጣቸው የጸረ-ሽብር፣ የሲቪክ እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መተዳደሪያ፣ የፕሬስ እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ምዝገባ፣ የፀረ-ሙስና እና ሌሎች አዋጆች ሥርዓቱ የአፈና  እና የመብት እረገጣ ተግባሩን ሕጋዊ ወደማድረግ ሂደት የተሸጋገረ መሆኑን ያሳያሉ። ፍጹም ሰላማዊ እና ሕጋዊ በሆነ መልኩ የመብት ጥያቄዎችን ባነሱ ዜጎች ላይ፤ አቅመ ደካሞችን እንኳን ሳይለይ ‘የፈሪ በትሩን’ ሲያሳርፍ በተደጋጋሚ ተስተውሏል።
ባለፉት ሃያ አመታት የአገዛዝ ሥርዓቱ የፈሪ በትሩን በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ አሳርፏል። ብዕርና ወረቀት በያዙ ከከፍተኛ ደረጃ ተማሪዎች እስከ አንደኛ ደረጃ ትመህርት ቤት ሕፃናት ጋር ሳይቀር በተደጋጋሚ ጊዜያት ተላትሟል። በርካቶችን ገድሏል፣ አስሮ አሰቃይቷል፣ ደብድቧል፣ ከትምህርት ገበታቸው ላይ አፈናቅሏል፣ ከአገር አሰድዷል፣ በሃሰት ወንጅሎ አስፈርዷል። በእምነት ቤቶች ውስጥ ገብቶ ከአማኞች፣ ከመንፈሳዊ አባቶች እና ይህን አለም ሸሽተው በገዳም ከከተሙ መነኮሳት ጋር ሳይቀር ተላትሟል። የኃይማኖት ተቋማት እንዲከፋፈሉና በገዢው ፓርቲ የፖለቲካ ተሿሚዎች ቁጥጥር ስር እንዲወድቁ ተደርገዋል። ምእመናን በመስጊዶችና በቤተክርስቲያን ውስጥ እያሉ በታጠቁ ኃይሎች ተገድለዋል፣ ተደብድበዋል፣ ተዋርደዋል። ቀሳውስት ጥምጥማቸውን እንዲያወልቁ እና መስቀላቸውን እንዲጥሉ ተደርጎ በማጎሪያ ካምፖች ውስጥ የማሰቃየት ተግባር ተፈጽሞቻቸውል። ኢማሞች ጺማቸው እየተጎተተ ተወስደው ተደብድበዋል፣ ታስረዋል። ይህ ሕዝብን የማዋረድ እና የማሸበር ተግባር የመነጨው እንደ እኔ እምነት የገዢው ኃይል እየተባባሰበት ከመጣው የፍርሃት እና የመሸበር ስሜት የተነሳ በራስ የመተማመን ስሜቱ እየተቦረቦረ በመሄዱ ነው። ዛሬ ሥርዓቱ የገዛ ጥላውንም የሚፈራበት፣ አባላቱ ላይ እንኳን እምነት ያጣበት ደረጃ ላይ ደርሷል። ለእዚህም አንዱ ማሳያው በነጋ በጠባ ቁጥር ማቆሚያ በሌለው የግምገማ ስብሰባ አባላቱን ሲያስጨንቅ መታየቱ እና ለዚሁ የሚያባክነው ጌዜ እና የሕዝብ ገንዘብ፣ የባለሥልጣናት ተደጋጋሚ  ሹም ሽር እና ከአገር ከድተው የሚወጡ ባለሥልጣናት እና የወያኔ አባላት ቁጥር መጨመሩ ነው።
ይህ የገዢው ኃይል የሕግን ልጓም በመበጣጠስ የፈረጠመ ክንዱን ይቀናቀኑኛል ባላቸው ግለሰቦች፣ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ ኃይሎችና የሙያ ማኅበራትና አባላቶቻቸው ላይ ሁሉ ማሳረፉ ቀሪውን የኅብረተሰብ ክፍል ክፉኛ እንዲደነብርና በፍርሃት ቆፈን እንዲሸማቀቅ አድርጎታል። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ መብቶች መከበር፣ የዴሞክራሲ ጥያቄዎች እና የሕግ የበላይነት መረጋገጥ የሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል የዕለት ተዕለት ሕይወት የሚነካ ቢሆንም የጥቂቶች ጉዳይ ተደርጎ ተወስዷል። በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ጥቂት የሲቪክ ማኅበራት፣ ጥቂት ጋዜጠኞች፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እና በጠአት የሚቆጠሩ ግለሰቦ ብቻ ናቸው ባላቸው ውሱን ጉልበት እና አቅም ሲወያዩ፣ የምንግሥትን መጥፎ ተግባራት ሲቃወሙ፣ ለዜጎች መብት ሲሟገቱ እና ባደባባይ ሲጮሁ የሚስተዋለው።
በድህነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቆ መቆየት
ሌላው እና ትልቁ የፍርሃት ምንጭ በከፋ ድህነት ውስጥ ለረዥም ጊዜ እየማቀቁ መቆየት እና ድህነቱ ባስከተለው የስቃይ ህይወት አካላዊና መንፈሳው አቅም ተሸርሽሮ ክፉኛ መጎዳት እና መዳከም ነው። ሕዝብን በድህነት ውስጥ አምቆ በማቆየት ለሰው ልጅ ከሚገባው ክብር ወርዶና ከእንስሳ ያልተሻለ ሕይወት እንዲኖር በማድረግ ቅስሙን መስበር የአምባገነኖች አንዱ የሥልጣን እድሜአቸውን ማራዘሚያ ሥልት ነው። የድህነት ክፋቱ ኪስን ብቻ ሳይሆን የሚያራቁተው ክብርንም ጭምር ነው። አንድ ሰው በመንገድ ላይ ቆሞና እራሱን ከመጽዋቾቹ ሥር ዝቅ አድርጎ ቁራሽ ምግብ ወይም ቤሳ ሲለምንና ሲማጸን በኩራትና በደስታ ስሜት ውስጥ ሆኖ አይደለም። እያፈረ እና እየተሸማቀቀ በተሸናፊነትና በዝቅተኝነት ስሜት ውስጥ ሆኖ ነው። ይህ ክስተት በሙሉ ጤንነት እና በወጣትነት ወይም በጉልምስና እድሜ ላይ ባሉ ሰዎች ውስጥ ሲሆን ደግሞ ያለው የውስጥ ሕመም እና የሕሊና ቁስል እጅግ የከፋ ነው። የድህነት ክፋቱ ያፈሩትን ቅሪት ብቻ ሳይሆን የሚያሳጣው ወይም ኑሮን ለማሸነፍ የሚያስችል አቅምን ብቻ ሳይሆን የሚሸረሽረው መንፋሳዊ ወኔንም ጭምር ነው ከላያችን ገፎ የሚወስደው። ከሰውነት ደረጃ ላይ የሚያቆመንን መንፈሳዊ ልዕልና ካጣን በኋላ ቁሳዊ ድህነቱን ብናሸንፈው እንኳን መንፈሳዊ ድህነቱ ይከተለናል። እዚህ ላይ ለማሳሰብ የምወደው ነገር ድሃ ሁሉ ፈሪ ነው ወይም በፍርሃት ቆፈን የተተበተበ ነው የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ እንዳይወሰድ ነው። በከፋ የኢኮኖሚ ድህነት ውስጥ እየኖሩ ክብራቸውን አስጠብቀውና እና በላቀ የመንፈሳዊ ወኔያቸው እራሳቸውንና አገራቸውን አስከብረው ያለፉ ድሃ አያት ቅድመ አያቶቻችንን ማሰብ የግድ ይላል። ዛሬም የገንዘብ እጦትና ድህነት ያላላሸዋቸውና መንፈሳዊ ልዕልናቸውን አስጠብቀው በክብር የሚሞቱ ወገኖች አሉን፤ ትቂቶች ቢሆኑም።
የዚህ ጽሁፍ ትኩረት ግን በቁሳዊውም ሆነ በመንፈሳዊ  ማንነታቸው ውስጥ ድህነትና ፍርሃት ተረባርበው ወይም ከሁለቱ በአንዱ ተጠልፈው ስብእናቸው ፈተና ውስጥ የወደቀባቸውን ሰዎች የሚመለከት ነው። በተለይም በዚህ ግለኝነት በነገሠበት እና ገንዘብ በሚመለክበት የአለም ወቅታዊ  ሁኔታ ውስጥ መናጢ ድሃ ሆኖ ለዘመናት መቆየት መዘዙ ብዙ ነው። ብዙዎች ከዚህ መቋጫው ከጠፋው የድህነት አረንቋ ለማምለጥ ስደትን አማራጭ አድርገው በተለያዩ አቅጣጫዎች አገሪቷን ለቀው ለአረብ አገራት ባርነት ተሰደዋል። ቀሪዎች ደግሞ የአገዛዝ ሥርዓቱ ሎሌ በመሆን ነፃነታቸው በቤሳ መሸቀጥን ቀጥለዋል። ለሁለቱም እድሉን ያጡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ድሆች ደግሞ በየጎዳናው ላይ ተበትነው ዝናብ፣ ውርጭና ፀሃይ እየተፈራረቁባቸው የመጽዋቾቻቸው ደጅ ጠኞች ሆነዋል።
ከተወሰኑ አሥርት አመታት በፊት አንድ ሰው በድህነቱ ምክንያት እራሱንና ልጆቹ የትምህርት፣ የጤና አገልግሎት፣ መሰረታዊ የሆን አልባሳትና መጠለያ ጎጆ ባለቤት ለማድረግ የሚገጥመው ፈተና ቢኖርም ይህን ያህል የመረረ አልነበረም። ዜጎች በወር ከሁለት ብር አንስቶ እንደ የአቅማቸው የቀበሌ እና የኪራይ ቤቶችን ቤቶች ተከራይተው የመጠለያ ችግራቸውን ይቀርፉ ነበር። በአገሪቷ ውስጥ የነበሩ በርካታ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ከመመዝገቢያ ያልዘለለ አነስተኛ ገንዘብ እየተቀበሉ ተማሪዎችን በነጻ ያስተናግዱ ነበር። ብዙ ምሁራንንም አፍርተዋል። በየቀበሌው ከተደራጁ ጤና ጣቢያዎች አንስቶ በተለያዩ የመንግሥት ሆስፒታሎች ዜጎች በነፃና እጅግ ተመጣታኝ በሆነ ክፍያ ጥሩ ሕክምና የማግኘት እድል ነበራቸው። በአንድ ብር በሚገዛው አስር ትንንሽ ዳቦ ወላጆች ልጆቻቸውን አብልተው ያሳድሩ ነበር። ዛሬ አገሪቱ በልማት እየገስገሰች እንደሆነ በሚነገርበት በዚህ ወቅት ዜጎች በኑሮ ውድነትና ዋስትና ማጣት በጨለማ  ህይወት ውስጥ እየተደናበሩ ይገኛሉ።
መንግሥት በኢኮኖሚውም፣ በፖለቲካውም ሆነ በሌሎች ኃይማኖታዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ያሻውን ቢያደርግ  በሕዝብ በኩል መላሹ ዝምታ ሆኗል። አብዛኛው ሕዝብ ከተዘፈቀበት የድህነት አረንቋ ሳይወጣ በርካታ ነገሮች ተቀይረዋል። በመቶና በሁለት መቶ ይገዛ የነበር ጤፍ በሺዎች ሲያወጣ ምላሹ ዝምታ ሆኗል። ቲማቲም እንኳን ባቅሟ በኪሎ ከሁለት ብር ወደ ሃያ ብር ስትጠጋ አንዳንዴም ስትዘል ዝምታ፣ የቤት ኪራይ ከመቶዎች ወደ ሺዎች ሲንር ዝምታ፣ የነዳጅ ዋጋ በየጊዜው ሲያሻቅብ ዝምታ፣ የመብራት፣ የውሃ፣ የስልክ እና የኢንተርኔት አገልግሎቶች በሰአታት፣ ከዚያም ለቀናት አንዳንዴም በተወሰኑ ቦታዎች ለሳምንታት ሲጠፉ ዝምታ፣ መነኮሳት እና አድባራት ሲዘረፉና ሲዋረዱ ዝምታ፣ መስጊዶች እና ኢማሞች ሲዋክቡና ሲታሰሩ ዝምታ፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ሲደበደቡ፣ ሲታሰሩና ሲሳደዱ ዝምታ፣ የንግዱ ማኅበረሰቡ ሲዋክብና ሲጉላላ ዝምታ፣ ገበሬዎች በማዳበሪያ እዳ ንብረታቸውን ሲነጠቁና ከዛም አልፎ ከትውልድ ትውልድ ያቆዩትን ይዞታቸውን እየተነጠቀ ለውጪ ቱጃሮች ሲቸበቸብ ዝምታ፣ ወንዶች ሚስቶቻቸውና ሴት ልጆቻቸው እፊታቸው ሲደፈሩና ሲጠቁ እያዩ ዝምታ፣ እናቶች ልጆቻቸውና ባሎቻቸው በየወጡበት ሲቀሩ እያዩ ዝምታ፣ በየከተማው የሚገኙ ነዋሪዎች ቤታቸ በላያቸው ላይ እንዲፈርስ እየተደረገ ከነልጆቻቸ በየሜዳው ተበትነው ይዞታቸው ለስግብግብ ባለሃብቶች ሲሰጥ ዝምታ፣ የሙያ ማኅበራት ሲጠቁ ዝምታ፣ መምህራኖች ሲዋከቡ ዝምታ፣ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው ‘በድህነት ቅነሳ እስትራቴጂ’ ስም ሲፈናቀሉና ለርሃብ ሲዳረጉ ዝምታ፣ ባለሥልጣናት የከፋ ሙስና ውስጥ ተዘፍቀው ሲንቦጫረቁ ዝምታ፣ ሕፃናት ሳይቀሩ በየአደባባዩ ግንባራቸው በጥይት እየተቦደሰ ሲረሸኑ ዝምታ፣ የአገሪቷ የትምህርት ሥርዓት ክፉኛ አቆልቁሎ ትውልድን ወደማክሰም ደረጃ ላይ ሲደርስ እየተመለከትን ዝምታ፣ መንግሥት ድህነትን ሸሽተው ከሃገር የሚሰደዱ ወጣቶችን መንገዱን ጨርቅ ያድርግላችው እያለና ገንዘብ እየቃረመ ለዘመናዊው ባርነት እያዘጋጀ ፓስፖርት ሰጥቶ ሲያሰድድ ዝምታ፣ በየጎዳናው የወደቁ  ሕፃናቶችን በጉዲፈቻ ስም መንግስት ለውጪ ዜጎች በብዙ ሺ ዶላር ሲቸበችብ እያየን ዝም፣ መንግስት የራሱን ሕገ-መንግስት እየናደ የፈቀደውን ሁሉ በዜጎች ላይ ሲፈጽም የህዝብ ምላሽ ዝምታ፣ ዝምታ፣ ዝምታ…..። ስንቱ ተጠቅሶ ይቻላል?
አንድ ሕዝብ ይህ ሁሉ ውርጅብኝ ያለፋታ ሲዥጎደጎድበት እና መገለጫ የሌልውን ግፍ እና ጭቆና በጫንቃው ላይ ሲጫንበት ውስጥ ውስጡን እያጉረመረመ፣ እያለቀሰና ልቡ እየደማ እንዴት ነህ ሲሉት ደህንነቱን ለመግለጽ ‘እግዚያብሄር/ አላህ ይመስገን’ እያለ የውሸት ሳቅ እየሳቀ እንዲኖር ያስገደደው ምንድን ነው? መንፈሱና አካሉ በቁሙ ተሸርሽረው እያለቁ ባልሞትኩም ባይነት የአያቶቹን ገድል በህሊናው እያመነዥከ በዘመኑ ለተጋረጡበት ፈተናዎች፤ በተለይም ድህነት፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጭቆዎችና በገዛ አገሩ ተዋርዶ መኖርን ለመሸሽ ስደትን ወይም ልመናን ወይም ሕሊናን ቀብሮ ለሥርዓቱ አገልጋይ መሆንን ከማን ተማረ? ይህ ጥልቅ የሆነው ዝምታችን የፍርሃት? ወይስ የትእግስት? ወይስ በፍርሃትና በትእግስተኛነት መካከል ሌላ ደሴት ወይም መንጠልጠያ ስፍራ አለ? እራሳችንን እንጠይቅ!
(ክፍል ሁለት)onetwo
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት በኢትዮጵያዊያን ላይ እያሰፈነ ስላለው የፍርሃት ባህል ቀደም ሲል ባሰራጨሁት የዚህ ጽሑፍ የመጀመሪያ ክፍል ውስጥ ባለሙያዎች በአንድ ማኅበረሰብ ውስጥ ለፍርሃት ባህል መስፈን መንሰዔዎች ያሏቸውን ነጥቦች ዘርዝሬ ነበር። በክፍል አንድ ጽሑፌ መግቢያ ላይ እንደገለጽኩት ምንም እንኳን ፍርሃት የግለሰቦች ባህሪ መገለጫዎች መካከል አንዱ ቢሆንም የዚህ ጽሑፍ ትኩረት በወል የምንጋራቸውና በማኅበረሰብ ደረጃም በሚንጸባረቁት የፍርሃት ምልክቶች ላይ ብቻ ያተኮረ ነው። በመሆኑም በዚህ ክፍል ውስጥ የህሊና እና የአካል ቁስልን ባስከተሉ ትላንቶች ውስጥ ማለፍ የሚፈጥረውን የፍርሃት ቆፈንና የሚያስከትለውን መዘዝ በመቃኘት ፅሑፌን ልደምድም።
በአለማችን ታሪክ ከሰው ልጅ አዕምሮ ተፍቀው የማይወጡና እጅግ አሰቃቂ በመሆናቸው ሲታወሱ የሚኖሩ በርካታ ጦርነቶችና የእርስ በርስ እልቂቶች ተከስተዋል። የመጀመሪያውና የሁለተኛው የአለም ጦርነቶች፣ የኦሽዊትዝ ጭፍጨፋ፣ የአፓርታይድ የግፍ አገዛዝ፣ የሩዋንዳው የዘር ማጥፋት እልቂት፣ እንዲሁም በተለያዩ የአፍሪቃ እና የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ውስጥ የተከሰቱትና የሚሊዪኖችን ሕይወት የቀጠፉት እልቂቶች በዋነኝነት ተጠቃሾች ናቸው። እነኚህ በክፉ ክስተትነታቸው በታሪክ የሚወሱት አጋጣሚዎች ካስከተሉት እልቆ መሳፍርት የሌለው ሰብአዊ ቀውስ እና የንብረት ውድመት ባሻገር ከትውልድ ትውልድ የሚወራረስ ትምህርትንም አስተምረው አልፈዋል። በተለይም የምዕራቡ አለም በራሱም ሆነ በርቀት በሌሎች ላይም የተፈጸሙትን እነዚህን መሰል መጥፎ ክስተቶች በአግባቡ በመመርመር፣ መረጃዎችን ሰብስቦና አደራጅቶ በማስቀመጥ፣ በመጽሐፍ ከትቦና እና በፊልም ቀርጾ በማኖር ቀጣዩ ትውልድ እነኚህን መሰል አደጋዎችን ከሚያስከትሉ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊ፣ ኃይማኖታዊና ኢኮኖሚያው ቀውሶችና ቅራኔዎች እራሱን በማራቅ ችግሮችን እጅግ በሰለጠነና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲፈታ ማድረግ ችለዋል። ዛሬ ላይ ያለው ትውልዳቸውም እነ ናዚ እና ሌሎች አንባገነኖች በታሪካቸው ውስጥ ያደረሱትን ሰቆቃና ግፍ እያሰብ የሚሸማቀቅ ወይም በፍርሃት የሚርድ ሳይሆን ታሪክን በታሪክነቱ ትቶ ሙሉ አቅሙንና ጊዜውን ከሳይንስና ተክኖሎጂ ጋር አዋህዶ በዚህ ምድር ላይ ያሻውን ሁሉ ለማድረግ የሚያስችል አቅም በመገንባት ላይ ይገኛል።
ወደ አገራችን ስንመለስ ኢትዮጵያም ዛሬ ያለችበትን ጂዮግራፊያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ሌሎች ገጽታዎች ለመላበስ ያበቋት እጅግ በርካታ ክፉ እና በጎ ተበለው የሚጠቀሱ የታሪክ ክስተቶችን አስተናግዳለች። ምንም እንኳን ከላይ ከተጠቀሱት የአለማችን አሰቃቂ ታሪኮች ጋር ባይወዳደርም አገራችንም ከውጭ ወራሪዎች በተሰነዘረባት ጥቃትም ሆነ በልጆቿ መካከል በተከሰቱ የእርስ በእርስ ግጭቶች በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ውድ ልጆቿን አጥታለች። ድህነትን ጠራርጎ ሊያስወግድ ይችል ከነበረው አቅም በላይ በብዙ እጥፍ የሚገመት አንጡራ ሃብቷን በጦርነቶች፣ በግጭቶችና በዘራፊዎች ተነጥቃለች። ይህ እና ሌሎች በርካታ ምክንያቶችም ተደራርበው አገሪቱን ከድሃም ድሃ ተብለው ከሚጠቀሱት አገሮች ተርታ አሰልፈዋታል። እንግዲህ ትልቁ ጥያቄ እኛስ እንደ ሌላው ዓለም ሕዝብ አገራችን ካለፈችበት የረዥም ዘመን ታሪክ እና በየወቅቱ ከተከሰቱ መጥፎና በጎ የታሪክ ክስተቶች ምን ተማርን? ተምረንስ ለዛሬ እኛነታችን ምን አተረፍን? በአያቶቻችን እና በእኛ መካከል በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እና በፖለቲካ ተክለ አቋማችንም ሆነ አመለካከታችን ዙሪያ ለውጦች አሉ ወይ? ለውጣችን ቁልቁል ወይስ ካለፉት ወገኖቻችን የህይወት ተመክሮ ትምህርት ወስደን የደረስንበት የላቀ የአስተሳሰብና የኑሮ ደረጃ አለ? የታሪክ መዛግብቶቻችንስ ያለፉ ነገስታቶችን እና የጦር አበጋዞቻቸውን ከማወደስና ገድላቸውን ከመተረክ ባለፈ በቀጣዩ ትውልድ ሕይወት የጎላ ሚና ሊኖራቸ በሚችል መልኩ ተዘጋጅተዋል ወይ? ወይስ ‘እኔ የገሌ ዘር’ እያለ እንዲያዜምና በአያቶቹ ገድል እንዲያቅራራ ብቻ ተደርገው ነው የተዘከሩት? እንደ እኔ እምነት ከምዕራቡ አለም እኛንና ብዙዎች የአፍሪቃ አገራትን ከሚለዩን ነገሮች መካከል ጥቂቶቹ ከነዚህ ጥያቄዎች ምላሽ የሚመነጩ ይመስለኛል።
የዛሬ መቶ እና ሁለት መቶ አመት በፊት የተፈጠሩ የታሪክ ክስተቶችን ፍጹም በተዛባ መልኩ እያጣቀስን ልክ የእኛ የልፋት ውጤት አስመስለን እስኪያልበን የምንፎክርና የምንጨፍር እኛ ነን። ታሪክን እና ጀግኖችን ማወደስ ተገቢ ቢሆንም የኛን ድርሻ እነሱን በማወደስ ብቻ ስንገታው አደጋ ላይ ይጥለናል። እንደ አያቶቻችን ታሪክን መስራት ሲያቅተን ታሪክ ሰሪዎችን በማውሳትና በዜማና በግጥም ማወደስ ብቻ ብንኮፈስ የዛሬውን ማንነታችንን አይሸፍነውም። ይህ በአያቶቻችን ታሪክ ውስጥ ተደብቀን ‘በኢትዮጵያዊነቴ እኮራለሁ’ እያሉ ማዜም፣ መፎከር፣ ማቅራራትና ያዙኝ ልቀቁኝ ማለት ዛሬ ከተጣቡን የድህነት፣ የፖለቲካ ጭቆና እና ማኅበራዊ ቀውስ የማያስጥለን እና ነፃ የማያወጣን እሰከ ሆነ ድረስ ኩራታችን ከድንፋታ አያልፍም። አገሬን እወዳልሁ፣ በኢትዮጵያዊነቴ እኮራለሁ እያሉ ባንዲራ ለብሶ ማቅራራት በተግባር ካልታገዘ የውሸት ወይም ባዶ ኩራት (false pride) ነው የሚሆነው። እውነተኛ ኩራት የሚመነጨው ከራስ ነው፤ የራስን ማንነትን በማወቅና በመቀበል ላይ የሚመሰረት ነው። ማንነትን አምኖ መቀበል አቅማችንንም አብረን እንድፈትሽ ይረዳል። የዛሬ ባዶነታችንን በአያቶቻችን የታሪክ ገድል እንድንሞላ ወደሚያስገድድ የሞራል ክስረት ውስጥም እንዳንገባ ይረዳናል። የዛሬ ውርደታችንን በአድዋ ድል እና በሌሎች የአያቶቻችን ተጋድሎዎች በተገኙ ስኬቶችን ልንሸፍነው ከመጣር ይልቅ ታሪክ እንድንሰራ ብርታት ይሆነናል።
በሌላ በኩል የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ያሳቀፉንን የዘረኝነት መርዝ እያራባን በታሪክ ተፈጽመዋል የተባሉ አንዳንድ ክስተቶችን እየመነዘርን ‘ያንተ ቅም ቅም አያትህ የእኔን ቅም ቅም አይታቶች በድሎ ነበር፤ ስለዚህ በቅም ቅም አያቶቼ ላይ ያንተ ዘሮች ላደረሱት በደል ኃላፊነቱን አንተ ትወስዳለህ እያልን ድርጊቱን ዛሬ ላይ እንደተፈጠረ በመቁጠር የምንጋጭና ለመነጣጠል እንቅልፍ አጥተን የምናድርም አለን። እራስን እንደተበዳይ ሌላውን የኅብረተሰብ ክፍል እንደ በዳይ በመቁጥርና የተዛባን ታሪክ በመተንተን ለዛሬው በዘረኝነት መርዝ ለተለወሰው የፖለቲካ አጀንዳቸው ማሳኪያነት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ካፈር የሚለውሱ ኢትዮጵያዊያኖችም (እነሱ ኢትዮጵያዊ አይደለንም ቢሉም) ልብ ሊገዙ ይገባል። በአገሪቱ ውስጥ ያሉ የተለያዩ ጎሣዎች በገዛ አገራቸው እኩል መብትና ጥቅም እንዲረጋገጥላቸውና የሁሉም አገር እንድትሆን ከመጣር ይልቅ በዘረኝነት ስሜት ውስጥ ተወጥሮ ኢትዮጵያዊነትን መካድና ከራስ ጎሣ ውጭ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል እንደ ጠላት መቁጠር መዘዙ ብዙ ነው። ይህን ለመረዳት ብዙ ምርምር አያስፈልገውም። በቅርባችን ካለችው ከሩዋንዳ ትምህርት መውሰድ ይቻላል። ይህን የዘረኝነት እሳት እየተቀባበሉ የፖለቲካ መታገያቸው ያደረጉ ኃይሎችም ከዚህ እኩይ ተግባራቸው እንዲታቀቡ በስሙ የሚነግዱበት ሕዝብ ሊያወግዛቸው ይገባል።
እርቀን ሳንሄድ የቅርብ ጊዜ ታሪካችንን እንኳን ብንፈትሽ ዛሬ ለምንገኝባቸው እጅግ ውስብስብ እና ፈታኝ ችግሮች መንስዔ የሆኑትን ነገሮች በቀላሉ ልንገነዘብ እንችላለን። የችግሮቻችንን ምንጮች እና ያስከተሉብንን መዘዝ በቅጡ መረዳት ከቻልን ከተዘፈቅንበት አረንቋ ውስጥ ለመውጣት ጊዜ ላይወስድብ ይችላል። መወጣጫውም ላይርቀን ይችላል። ትልቁ ጥያቄ ችግሮቻችንን ከመዘርዘር ባለፈ ምንስዔዎቻቸውንም በቅጡ ተረድተነዋል ወይ? እንደ አንድ አገር ሕዝብ በችግሮቻችን እና በችግሮቹ ምንጭ ዙሪያ የጠራ የጋራ ግንዛቤ አለን ወይ? በፖለቲካ እና በሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ስንደራጅስ ከነዚህ ግንዛቤዎች ተነስተን ነው ወይ? የጋራ የሆኑ ችግሮች ሰዎችን ያስባስባሉ፣ ለድርጅቶች መፈጠርም መንስዔ ይሆናሉ፣ ችግሮቹንም ለመቋቋም እና ለማስወገድ “ከአንድ ብርቱ …” እንደሚባለው ኃይልን ይፈጥራሉ። ይሁንና ስብስቡ ወይም የተደራጀው ኃይል ፊት ለፊት ከተጋረጡት ችግሮች ጋር ከመፋለም ባለፈ በድጋሚ እንዳይከሰቱ ምንጮቻቸውን ለማድረቅ የሚያስችል እይታ ከሌለው እና አቅሙንም በዚያ ደረጃ ካላሳደገ ይህ አይነቱ ማኅበረሰብ ሁሌም ለተመሳሳይ አደጋዎች የተጋለጥ ነው። የችግሩን መንሰዔ አጥንቶ ምንጩን ለማንጠፍ ከሚያወጣው ጉልበት፣ ገንዘብና ጊዜ የበለጠ አዳዲስ ችግሮች በተከሰቱ ቁጥር ከተኛበት እየባነነ ተነስቶ ችግሮቹን ለመቋቋም የሚያስችሉ ድርጅቶችን ለመፍጠርና ለማፍረስ የሚያወጣው ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት እጅግ የላቀ ነው። በእንዲህ አይነት ማኅበረሰብ ውስጥ ጠንካራ የሆኑና ልምድ ያካበቱ ድርጅቶችን መፍጠር አይቻልም። ብዙዎቹ ድርጅቶች ሳይጎረምሱ፣ ሳይጎለምሱ እና ሳያረጁ በጨቅላነታቸው ይሞታሉ ወይም ደንዝዘው ስማቸውን ብቻ ይዘው ይቀራሉ። ይህ አይነቱ ማህበረሰብ አውራ የሚሆኑና በምሳሌነት ሊጠቀሱ የሚችሉም የፖለቲካ፣ የኃይማኖት እና የማኅበራዊ ህይወት መሪዎችን የመፍጠር አቅም የለውም፤ አይፈጥርምም፤ በራሳቸው ጥረት ቢፈጠሩም ጎልተው እንዲታዩ እድሉን አይሰጥም። ትላንት ያነገሳቸውን በማግስቱ አፈር ከድሜ ሲደባልቃቸው ምንም አመክንዮ አይፈልግም። ሲያከብርም፣ ሲሾምም፣ ሲያዋርድም ሆነ ሲኮንን በስሜት ነው። በተለይም እንደኛ በብዙ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ ተተብትቦ ግራ ለተጋባ ማኅበረሰብ ልምድና በእውቀት የጎለበቱና የሕዝብ አመኔታን ያገኙ ባለ ዕራይ ድርጅቶችና ግለሰቦች መኖር እጅግ ወሳኝ ነው።
የፖለቲካም ሆነ ሌሎች ልዩነቶቻችንን የምንይዝበት መንገድ ሊፈተሽ ይገባዋል። የቀዝቃዛው የአለም ጦርነት ማብቂያን ተከትሎ የፈረሰውና ጀርመንን ለሁለት ከፍሏት የነበረው ግንብ ሲናድ ምስራቅና ምዕራቡን ወደ አንድ አገር ከመለወጥ ባለፈ መላው አውሮፓን አንድ ያደረገ ክስተትን ፈጥሯል። የሰብአዊ መብቶች እና የዲሞክራሲ ጽንሰ ሃሳቦች የልዩነት ማጦዣ ምክንያቶች ከመሆን ወጥተው ጀርመንን ብቻ ሳይሆን አውሮፓን ያዋሃዱ ተጨባጭ እውነታዎችን ፈጥረዋል። ይህን ተከትሎም ከታሪክ ለመማር ዝግጁ በሆኑ በበርካታ የአለማችን አገራት በመሬት የተገነቡም ሆነ በሰዎች አዕምሮ ውስጥ የተካቡ የልዩነት ግንቦች ሁሉ ፈርሰው ዜጎች ለጋራ ራዕይ በጋራ የመቆም ጽናትን አሳይተዋል። ሕዝባቸውንም ነጻ አውጥተዋል። ሌሎች እንደ ኢትዮጵያ ያሉ የተለያዩ አገሮች (አብላጫዎቹ የአፍሪቃ አገራት) የልዩነቶቻቸውን ግንቦች አጠንክረውና አዳዲስ ግንቦችን በአይምሯቸው ውስጥም ገንብተው የተሰበጣጠረና የሚፈራራ የኅብረተሰብ ክፍልን በመፍጠር ጉዞዋቸውን ቀጥለዋል። የጎሣ ግንቦች፣ የሥልጣን ግንቦች፣ የኃይማኖት ልዩነት ግንቦች፣ የድሃና የሃብታም ግንቦች፣ የጨቋንና የተጭቋኝ ግንቦች፣ ሌሎች ማኅበረሰቡን በአንድ ላይ እንዳይቆም እና ድህነትና አንባገነንነትን አሽቀንጥሮ እንዳይጥል አቅም የሚያሳጡ በርካታ የልዩነት ግንቦች ተገንብተዋል።
ድርጅቶችን እና መሪ የሚሆኑ ግለሰቦችን እየፈጠርንና መልሰን እየደፈጠጥን የመጣንበትን የ50 ዓመታት የፖለቲካ ጉዞ ወደ ኋላ መለስ ብለን ብንቃኝ ይህንን እውነታ ያረጋግጥልናል። ባለፉት 50 ዓመታት ውስጥ ለቁጥር የሚታክቱ የፖለቲካ፣ የሙያና በማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኮሩ ድርጅቶች ተፈጥረው ብዙዎች ካለሙበት ሳይደርሱ ከስመዋል። ጥቂቶችም ባልሞት ባይ ተጋዳይነት በመኖርና ባለመኖር መካከል ሆነው ቀጥለዋል። በከሰሙትም እግር ሌሎች በርካቶች ተተክተው በተመሳሳይ አዙሪት ውስጥ ወድቀው የኅብረተሰቡን ቀልብ ለመሳብ ደፋ ቀና ሲሉ ይስተዋላል። እዚህ ላይ ልብ ልንለው የሚገባው በዚህ ዘመን ውስጥ ብቅ ብለው በከሰሙትም፣ ተውተርትረው ቆይተው በተዳከሙትም፣ አዳዲስ ስም እየያዙ በተፈጠሩትም ድርጅቶች ውስጥ ዋነኛ ተዋናዮቹና የድርጅቶቹ ፈጣሪዎችም ሆኑ አጥፊዎቹ አንድ አይነት ሰዎች መሆናቸው ነው። ትላንት በአንድ ድርጅት ጥላ ስር ሆነው ሌሎችን እንደ ጠላት ይፈርጁ የነበሩ ሰዎች ዛሬ የብዙ ድርጅቶች ፈጣሪዎች ሆነዋል። ትላንት በጠላትነት የሚፈራረጁ ድርጅቶች አባል የነበሩ ሰዎች ቂማቸውን እንዳረገዙ ዛሬ በአንድ ድርጅት ጥላ ሥር የተሰባሰቡበትንም ሁኔታ እናያለን። በድርጅቶቹ መካከል እጅግ ጠባብ የሆኑ የርዕዮታለም ልዩነቶች ከመኖራቸው ውጭ አብዛኛዎቹ የመጨረሻ ግባቸው አንድ እና አንድ ነው። ዲሞክራሲ የሰፈነባት፣ የሕግ ልዕልና የተረጋገጠባት፣ ሰብአዊ መብቶች የተከበሩባት እና ድህነትን ያሸነፈች ኢትዮጵያን ማየት፣ መፍጠር ነው። በነዚህ መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የሚለያዩ ድርጅቶች ያሉ አይመስለኝም፤ ሊኖርም አይችልም። ልዩነቱ እነዚህ ግቦች ላይ ለመድረስ ድርጅቶቹ በሚከተሉት አቅጣጫና መንገድ ቅየሳ ላይ ነው።
በዚህ የ50 ዓመት ጉዞ ውስጥ በሽብር መንፈስና በነውጥ ተግባራት የተሞላው የኢትዮጵያ ፖለቲካ በድርጅቶች መካከል እርስ በርስ አለመተማመንንና መካካድን ፈጥሯል። ይህም አለመግባባቶቹ ከጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት አልፈው እልቂትን አስከትለዋል። በዚያም የተነሳ አገሪቷ በፍርሃት እንድትዋጥና ሕዝቧም በስጋት እንዲኖር፤ የፍርሃት ባህልም እንዲጎለብት ከፍ ያለ ሚና ተጫውቷል። ዛሬ በእያንዳንዳችን አዕምሮ ውስጥ በርካታ የልዩነት ግንቦች ተፈጥረዋል። በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በሲቪክ ማኅበራት፣ በኃይማኖት ተቋማት፣ በማኅበረሰብ ድርጅቶች መካከልም የበርሊን ግንብ አይነት ግዙፍ የልዩነት ግንቦች ተፈጥረዋል። የዛሬዎቹ ኃይሎች ከገዢው ፓርቲ በስተቀር በትጥቅ የተደራጁ ስላልሆኑ ነው እንጂ ለመጠፋፋት ቅርብ ናቸው። ትልቁና እያንዳንዳችን እራሳችንን ልንጠይቅ የሚገባን፤ እነዚህን ግንቦች ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዴት ንደን እና በላያቸው ላይ ተረማምደን ልብ ለልብ እንዋሃዳልን? እንዴት እንደ አንድ ሕዝብ የጋራ ዕራይ፣ የጋራ መዝሙር፣ የጋራ ህልም፣ የጋራ መፈክር፣ የጋራ መድረክና የጋራ አገር እንፈጥራለን? እንዴት ከቂም፣ ከበቀልና ከቁርሾ ሽረን ከታይታና ከቧልት ፖለቲካ ወደ እውነተኛ የፖለቲካ ሕይወት እንመለሳለን?
ለማጠቃለል ያህል በእኔ እምነት ከተተበተብንበት ውስብስብ ችግሮችና ከተጫነን የፍርሃት ድባብ ለመላቀቅ፤ አልፎም ጤናማ የሆነ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሥርዓት ባለቤት የሆነ ማኅበረሰብ ለመፍጠር የሚከተሉት ተግዳሮቶች ቢቀድሙ ይበጃል እላለሁ::
  • ዛሬ ለፖለቲካ ንትርክና  እርስ በርስ መፈራራት እንደ ምክንያት የሚነሱት የታሪካችን ክፍሎች ከፖለቲካ፣ ከኃይማኖት እና ከሌሎች ወገንተኝነት ነጻ በሆኑ ምሁራን በአግባቡ የሚጠኑበት ማዕከል ቢኖረን። የመወዛገቢያ ነጥብ የሆኑትም ታሪካዊ ኩነቶችን በአግባቡ ቢጠኑ እና በተለያዩ መንገዶችም ተደግፈው ለማስተማሪያነት ቢውሉ በድንቁርና ላይ ከተመሰረቱት ታሪክ ጠቀስ የሆኑና በጥላቻ መንፈስ የተሞሉ ክርክሮች ወጥተን እውቀትን በዋጁ ውይይቶች ላይ እናተኩራልን።
  • የሩቁን ለታሪክ ምሁራን እንተወና ባለፉት አምሣ ዓመታት ከ1960 ዎቹ የተማሪዎች ንቅናቄ ጀምሮ በፖለቲካ ትግል ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑ ኃይሎች ዛሬም በአገሪቷ የለት ተዕለት የፖለቲካ ህይወት ውስጥ በግራና በቀኝ ሆነው እና በመቶ ድርጅቶች ጉያ ውስጥ መሽገው በአገሪቷና በድሃው ሕዝብ እጣፈንታ ላይ ወሳኞች ሆነው ቀጥለዋል። በተለይም ‘ያ ትውልድ’ በሚል የሚታወቀው የኅብረተሰብ ክፍል ከልጅነት እስከ አዋቂነት ክቡር ሕይወቱን፣ ጊዜውን፣ ገንዘቡን እና እውቀቱን ያለምንም ስስት የዛችን አገር እጣ ፈንታ ለማቅናት መስዋዕትነት ሲከፍል ቆይቷል፤ ዛሬም ዋነኛ ተዋናይና አድራጊ ፈጣሪ ሆኖ ቀጥሏል። ይህ ትውልድ ትላንትናም ሆነ ዛሬ በገዢና በነጻ አውጪዎቻች ቡድኖች ተፈራርጆ እርስ በርሱ ተጨራርሷል፣ ቂምና ቁርሾም ተጋብቷል፣ ተሰዷል አሰድዷል። ዛሬም በልቡ ቂም ይዞና በቀልን አርግዞ በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ መሽጎ የጎሪጥ ይተያያል። ባገኘው አጋጣሚም ሆሉ ይናቆራል። ‘ቂም ተይዞ ጉዞ’ እንዲሉ ትላንት በተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ ሆነው በጠላትነት ይፈራረጁና ሊገዳደሉ ይፍላለጉ የነበሩ ሰዎች ይህን ሸክማቸውን በንስሃ እና በይቅር ባይነት ከላያቸው ላይ ሳያራግፉ ውስጥ ውስጡን እየተብሰከሰኩና እየተፈራሩ ገሚሶቹ በልጅነታቸው በቆረቡባቸው ድርጅቶች እየማሉ ቀሪዎቹም ዘመኑ በወለዳቸው አዳዲስ ድርጅቶች ውስጥ ሆነው የለበጣ ውህደት እየመሰረቱ በዋዜማው ይፈረካከሳሉ። እንደ እኔ እምነት ከዚህ የእርስ በርስ መፈራረጅ፣ መፈራራትና የቆየ ቂምና ጥላቻ ሳንሽር የምንክበው ካብ ሁሉ የእምቧ ካብ ነው የሚሆነው። እየሆነ ያለውም ይሄው ነው። ከዚህ አዙሪት ወጥተንና ከቂም ተላቀን የጋራ ራዕይ እንዲኖረን እያንዳንዱ ግለሰብ እራሱን ለይቅርታ ማዘጋጀት አለበት። ከልብ የበደላቸውን ይቅርታ ለመጠየቅና ይቅርታ ለመቀበል። ከድርጅታዊ ወገንተኝነትም እራሱን ነጻ አውጥቶ በሱና በድርጅቱ ላይ የተፈጸመውን በደል ብቻ ሳይሆን እሱም ጠላት ብሎ በፈረጃቸው ሰዎችና ድርጅቶች ላይ ያደረሰውን ግፍና በደል ለመናዘዝና ለደረሰውም ሁሉ አቀፍ ጥፋት ድርሻቸውን በድፍረት በማንሳት የተጠታቂነት ባህልን ‘ሀ’ ብለው ሊጀምር ይገባዋል።
  • ይህ ሁኔታም የደረሰውን የጉዳት መጠን በቅጡ እንድናውቅ ከማድረጉም ባሻገር እርስ በርስ የመወነጃጀሉን ታሪክ እንድንገታውና ልባችንንም በፖለቲካ ንስሃ አንጽተን የሚነገርለትን ያህል የተሳካ ባይሆንም እንኳ ልክ እንደ ደቡብ አፍሪቃው ‘በእውነት’ ላይ ወደ ተመሰረተ የእርቅ እና የሰላም መድረክ እንድቀርብ እድል ይፈጥርልናል።
  • የልጆቹን እርስ በርስ መጨራረስ እየተመለከት ፓለቲካ እንዲህ ከሆነ አርፎ መቀመጥ ይበጃል፤ እርም የፖለቲካ ነገር በሚል አይምሮውን ጥርቅም አድርጎ ዘግቶ የለት ጉርሱን ብቻ እየቃረመ የአገሩን የፖለቲካ እጣፈንታ ለእዝጌሩ ትቶ ደግ ቀንና መልካም አስተዳደርን እንደመና ከሰማይ እንዲወርድለት የሚጠባበቀውም የኅብረተሰብ ክፍል አይኑን ይገልጣል፤ ከመጠፋፋት ወደ ሰለጠነ የውይይት ባህል በሚሻገረው የፓለቲካ ኃይልም ላይ እምነት ያሳድራል፤ እራሱንም ከፍርሃት ነጻ አውጥቶ በሙሉ ልብ በአገሩ ጉዳይ ባለቤት ይሆናል።
  • ስለዚህም የገዢው ኃይል ወያኔ ካለበት ጥልቅ ፍርሃት እና የሥልጣን ጥም የተነሳ ለእንዲህ ያለው ለውጥም ሆነ የሰላምና የእርቅ ጎዳና ገና ዝግጁ ባይሆንም የተቀሩት የፖለቲካ ሃይሎች መንገዱን በመጀመር ለዘመናት በመካከላቸው የቆየውን ቁርሾና ቂም ከአዕምሯቸው በማውጣት ከልብ የመነጨ እርቅ በማድረግ የልዩነት ግንቦችን ማፈራረስ ይጠበቅባቸውል። የሰላም፣ የእርቅ እና የእውነት አፈላላፉ ጉባዔ ያስፈልገናል።
በእውነት ላይ ተመስርተው ተቃዋሚዎች በቅል ልቦና ከታረቁ አብረው ከሠሩ በኢትዮጵያዊና በኢትዮጵያዊያን ላይ ለዘመናት እንደ መዥገር ተጣብቀው ደማችንን የሚመጡትን፣ ክብራችንን ገፈው እርቃን ያስቀሩንን፤ ድኅነት፣ እርዛት፣ አንባገነናዊ ሥርዓትና ጭቆና፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት፣ ጦርነትና የእርስ በርስ ግጭቶች፣ ድንቁርና፣ ጨለምተኝነት፣ ፍርሃት፣ ሙስና እና ጥላቻን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ነቅለን መጣል እንችላለን። ቅን ልቦና ይኑረን! ለዘመናት የተጫነንን ሸክማችንንም እናራግፍ። ያኔ ለፍቅር በፍቅር፣ ለሰላም በሰላም፣ ለነጻነት በነጻነት፣ ለአንድነታችን በአንድነት የምንሰራበትና ታሪክ ዘካሪ ብቻ ሳንሆን ታሪክ ሰሪ የምንሆንበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም።
ቸር እንሰንብት!

አንድነትና የሚሊየንም ድምጽ ለነጻነት ንቅናቄ – አማኑኤል ዘሰላም

ታህሳስ 15 ቀን 2006 ዓ.ም
 
የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር፣ አቶ ይልቃል ጌትነት፣ በዉጭ አገር የሥራ ጉብኘት እያደረጉ እንደሆነ በስፋት እየተዘገበ ነዉ። ታዲያ «ስለ ሰማያዊ ብዙ እየሰማን፣ የአንድነት ፓርቲ ድምጽ ግን ምነዉ ጠፋ። የሚሊየነሞች ድምጽ ለነጻነትስ ወዴት ገባ ?» ብለን የምንጠይቅ ልንኖር እንደምንችል አስባለሁ። በዚህም ረገድ በአንድነት ፓርቲ ዙሪያ አንዳንድ ሃሳቦች ለአንባቢያን ለማካፈል እሞክራለሁ።
በቅድሚያ አንድ መረዳት ያለብን ነገር አለ። የአንድነት ፓርቲና እና ሰማያዊ ፓርቲ፣ ሁለቱም ተመሳሳይ የፖለቲካ ፕሮግራም ቢኖራቸውም ፣ ሁለቱም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለዉጥ ለማምጣት ቢታገሉም፣ የአሰራር ልዩነቶች አሏቸው። የአንድነት ፓርቲ፣ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ የትግሉ አካል እንደሆነ ቢያውቅም፣ መሰለፍ ብቻ በራሱ ምንም ሊያደርግ እንደማይችል ጠንቅቆ የተረዳ ደርጅት ነዉ። በዚህም ምክንያት ግብታዊ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን ከማድረግ ብዙ ይቆጠባል። ሰልፎችም ሆነ ማናቸዉም አይነት ሰላማዊ እንቅስቅሴዎች ተጠንተዉ፣ በጥንቃቄና ዉጤት በሚያመጣ መልኩ መደረግ አለባቸው ብሎ ያማናል። ካለፈው የቅንጀት ስህተቶች ብዙ የተማረ ነው።
በመሆኑም ሰልፍ አልተደረገም ማለት እንቅስቃሴ የለም ማለት አይደለም። የአንድነት ፓርቲ በአሁኑ ወቅት እያደረጋቸው ያላቸዉን አራት በጣም አስፈላጊና መሰረታዊ ጉዳዮች እንዳካፍል ይፈቀድልኝ፡
1. አንድነት፣ ከሰኔ እስከ መስክረም የተደረገዉን የሚሊየኖችም ድምጽ ለነጻነት እንቅስቃሴዎች፣ እንዲሁም የፓርቲዉ ጠቅላላ ስራዎች፣ ወደ ኋላ ተመልሶ ግምገማ እያደረገ ነዉ። «የቱ መስተካከል አለበት ? የቱ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ? ..»እየተባለ ፣ ጠቃሚ ትምህርቶችን ለማሰባሰብ እየተሞከረ ነዉ። ዝም ብሎ መሮጥ አይደለም። ቆም ብሎም ማሰብና እራስን መመርመር፣ ካለፉትን ተግባራት መማር ያስፈልጋል።
2. ፓርቲው በቅርቡ የአመራር አባላትን ይመርጣል። አብዛኞቹ አገር ዉስጥም ሆነ በዉጭ ያሉ ድርጅቶች አንድ መሪ ነው ለዝንተ አለም የሚመራቸው። የአንድነት ፓርቲን መጀመሪያ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ከዚያም ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራዉ፣ ከዚያም ዶር ነጋሶ ጊዳዳ መርተዋል። አሁን ደግሞ ዶር ነጋሶን ለመተካት ሶስት እጩዎች የምረጡኝ ዘመቻ ላይ ናቸው። እነርሱም የፓርላማ አባል የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ፣ ቀድሞ ፓርቲዉን ሲመሩ የነበሩትና በበርካታ አባላት እንደገና እንዲወዳደሩ ግፊት እንደተደረገባቸው የሚነገረዉ፣ አንጋፋው ኢንጂነር ግዛቸው እንዲሁም ኮንሴንሰን ቢልድ በማድረግና በአስተዋይነታቸው የሚታወቁት፣ በአሁኑ ወቅት ፓርቲዉን በፋይናንስ ሃላፊነት የሚመሩት፣ አቶ ተክሌ በቀለ ናቸው።ይህ በአንድነት ዉስጥ እየተደረገ ያለው ፉክክር ፣ በማንም የአገራችን ድርጅቶች ያልታየ ዴሞክራሲያዊ  ፉክክር ነዉ።
3. እርግጥ ነዉ ከአሁን ለአሁን ሕብረት ያስፈልጋል ተብሎ፣ ወደ ኋላ ከሚጎትትና ስራን ከማያሰራ ድርጅት ጋር ሕብረት አይፈጠርም። ሕብረት ሲፈጠር ለዉጤት መሆን አለበት። በዚህም ረገድ አንድነት ከዚህ በፊት አካል ከሆናቸው እንደነ መድረክ ካሉ ስብስቦች ጋር ያለዉን ግንኙነት እየፈተሸ ነዉ። በአንጻሩም ደግሞ ፓርቲውን ሆነ ትግሉ ወደፊት እንዲሄድ ሊረዱ የሚችሉ ፣ ከሌሎች ድርጅቶች ጋር ፣ የላይ ላይ ትብብር ሳይሆን የዉህደት እንቅስቃሴ እያደረገ ነዉ። ከዚህ በፊት እንደ ብርሃን ፓርቲ ያሉ ድርጅቶች ከአንድነት ጋር መዋሃዳቸው ይታወቃል። አሁን ደግሞ አንድነት ፓርቲ ከአንጋፋዉ መኢአድና በአሁኑ ወቅት አስደሳች እንቅስቅሴ በሜዳ ላይ አያደረገ ካለው ከአረና ጋር ለመዋሃድ ትልቅ ሥራ እየሰራ ነዉ።
4. ሰላማዊ ሰልፍ ሆነ ሌላም ሌላም እንቅስቅሴዎች እንዲሁ በግብታዊነት አይሰሩም። ጥናት፣ ጥንቃቄ፣ ዝግጅት ያስፈልጋል። የስሜት ትግል የትም አያደርሰም። ትግሉ የሰከነ፣ የበሰለና ዉጤት የሚያመጣ መሆን አለበት። የአንድነት ፓርቲ የሚሊየነም ድምጽ ለነጻነት በሚል ስም የጀመረው እንቅስቃሴ ክፍል ሁለት፣ ከአመራር አባላት ምርጫ በኋላ፣ ይታወጃል። ይህ እንቅስቃሴ አዲስ አበባ ዉስጥ ብቻ ያተኮረ ሳይሆን፣ በመላ አገሩቷ ያተኮረ፣ ትግሉን አንድ እርምጃ ወደፊት የሚወስድ እንቅስቃሴ ይሆናል። ለዚህም እንዲረዳ አባላት በሰላማዊ ትግል ዙሪያ የተለያዩ ስልጠናዎች እየወሰዱ ናቸው።
እንግዲህ አገር ዉስጥና ከአገር ውጭ ለምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን እንዲህ እላለሁ። በአገራችን ሙስና የመስፋፋቱ፣ ዘረኝነት የመብዛቱ፣ የሕግ ስርዓት ያለመኖሩ፣ የኑሮ ዉድነቱ፣ የሰባአዊ መብት ረገጣዉ ፣ ኢትዮጵያ ለብዙሃኑ ሲኦል፣ ከገዢው ፓርቲ ጋር ግንኙነት ስላላቸው ብቻ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ሚሊየንር ለሆኑት ለጥቂቶች ገነት ለመሆኗ ምክንያቱ የፖለቲካዉ ችግር ነው። የፖለቲካ ችግርን ለማስተካከል ደግሞ የፖለቲክ ትግል ይጠይቃል። የአንድነት ፓርቲ ይህ ለሰላምና ለፍትህ የሚደረገዉን የፖለቲክ ትግል ለመምራት እየሰራ ነዉ።
የአንድነት ፓርቲ ከሁለት ወራት በፊት ባደረጋቸው አገረ ሰፊ፣ የሚሊየም ድምጽ ለነጻነት እንቅስቃሴዎች፣ በአዲስ አበባ፣ በመቀሌ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በደሴ፣ በጂንካ፣ በአርባ ምንጭ፣ በወላይታ ሶዳ፣ በባሌ/ሮቢ ፣ በፍቼና በአዳማ ሰላማዊ ሰልፎች አድርጓል። በመቀሌ ሰልፉ ሊደረግ አንድ ቀን ሲቀረዉ የሕወሃት ባለስልጣናት «እንኳን አንድነት፣ ቅንጅትም መቀሌን አልደፈረም»በሚል የቅስቀሳ መኪናዎችን እና ማይክሮፎኖችን በማገታቸውና የአመራር አባላትን በማሰራቸው፣ ከአሥር አምስት ቀናት ቅስቀሳ በኋላ ሰልፉ ሊሰረዝ ችሏል። በባሌ/ሮቢ፣ ኦሕድዶች ሰልፉ ከመደረጉ አንድ ቀን በፊት፣ «ሰልፉን ካደረጋቸው ከፍተኛ ደም መፋሰስ ይሆናል» የሚል ዛቻ በመሰንዘራቸው ፣ ሕዝብን አደጋ ላይ ላለመጣል ሲባል፣ ሰልፉ ሳይደረግ ቀርቷል።
የአንድነት ፓርቲ በአዋሳ፣ በጋምቤላ፣ በወሊሶ፣ በድርደዋና በአሳሳም ሰልፎች ለማድረግ እቅድ ነበረዉ። ነገር ግን በገንዘብ ማነስ ምክንያት እነዚህ ከተሞች ሰልፍ ማድረግ እንዳልተቻለ ነው።
አሁንም ፓርቲዉ የተቻለዉን ለማድረግ የወሰነነ የቆረጠ ቢሆንም፣ ፓርቲዉ የሕዝብ ድጋፍ ከሌለዉ ሊያደርግ የሚችለው የተወሰነ ነዉ። በተለይም የገንዘብ አቅም ላይ ትልቅ ትኩረት መስጠት እፈልጋለሁ። እንዲሁ ለዉጥ ስለተመኘን ለዉጥ አይመጣም። አገር ቤት ያሉ ኢትዮጵያዉያን በጓዳና በሹክሹክታ ብሳታችንን መግለጽ ማቆም ይኖርብናል። ትግሉ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊን ተሳትፎ ይጠይቃል። ጠንካራ ፓርቲ ሲመጣ መቀላቀሉ ሳይሆን፣ አሁን ያሉትን፣  እንድ አንድነት ፓርቲ አይነቶችን ጠንካራ እንዲሆኑ ማድረጉ ይበጃል።
ዉጭ አገር ያለነው ፣ ምን እንኳን የመገደል፣ የመታሰር፣ የመዋከብ አደጋ ባያገኝንም፣ ቢያንስ ስራችን እና አፋችን መገናኘት ያለባቸው ይመስለኛል። «አገር ቤት ካሉት ድርጅቶች ለዉጥ ለምን አያመጡም» ብለን መናገርና መጠየቅ ሳይሆን፣ ለዉጥ እንዲያመጡ የነርሱ አካል ሆን ድጋፋችንን መስጠት ይጠበቅበናል። ሕዝቡ ካልተነሳና ካልተነቃነቀ በምን ሁኔታ ለዉጥ ሊመጣ አይችልም። ህዝቡ እንዲነሳ ሕዝቡ መሃከል ሆኖ ትልቅ ድርጅታዊ ሥራ መስራት ያሰልጋል። ይህን አይነት ድርጅታዊ ሥራ ለመስራት፣ ሕይወታቸው ለዚህ ሥራ አላልፈው ከሰጡ አገር ቤት ካሉ ጀግኖች ጎን መቆም ይኖርብናል።
እንግዲህ ለሚሊዮኖች ድምጽ ለነጻነት እንቅስቃሴ ክፍል ሁለት ከወዲሁ ሁላችንም እንዘጋጅ። ፓርቲዉን በገንዘባችን እንደግፍ። በገንዘብ ለመርዳትና ከሚሊዮኖች አንዱ ለመሆን የሚፈልጉ ከሆነ የሚከተለዉን ድህረ ገጽ ይጎብኙ !
http://www.andinet.org/

የቁጫ ህዝብ ጥያቄ የሚፈታው የዜጎች መብት ሲከበር ነው!!አንድነት ፓርቲ ልዩ ጠቅላላ ጉባኤውን ታህሳስ 19እና20/2006ዓ.ም ያደርጋል – ከአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት)የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

ኢህአዴግ በሚከተለው የዘረኝነት ፖሊሲና የከፋፍለህ ግዛው አገዛዝ መርህ ዛሬ በሃገራችን የአንድ አካባቢ ህዝብ በሌላው አካባቢ በነፃነት ሰርቶ የመኖር ህገ-መንግስታዊ መብት በገዢው ፓርቲ አመራር አባላት ሴራ ሲጣስ ይታያል፡፡ ባሳለፍናቸው አመታት በማንነታቸውና በእምነታቸው ምክንያት ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ተረግጠው በአስርና በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖቻችን ተወልደው ወልደው ሃብት ንብረት ካፈሩበት መሬት ተፈናቅለውና በዚሁ ሳቢያ ለስደትና ለልመና የመዳረጋቸው ሚስጢር በማናቸውም መልኩ የኢህአዴግ አምባገነናዊ አገዛዝ ድምር ውጤት ነው፡፡
ካለፈው አመት መጨረሻ አካባቢ በደቡብ ክልል በጋሞ ዞን በቁጫ ወረዳ ህዝብና ነዋሪዎች ላይ እየደረሰ ያለውን እስራት፤ ስደት፤ ወከባና እንግልት እንዲሁም ሞት በተለያየ የመገናኛ ብዙሃን ድህረ ገፆች መረጃው በስፋት መቅረቡን ተከትሎ ፓርቲያችን በዚህ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ አቅዋም ለመያዝ እንዲያስችለው አንድ በፓርቲው ከፍተኛ አመራር የሚመራ ቡድን ወደ ቦታው በመላክ የተሰበሰበውን መረጃ የፓርቲው ብሄራዊ ምክር ቤት ታህሳስ 13ቀን 2006ዓ.ም በጠራው አስቸካይ ስብሰባ በቁጫ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን የፖለቲካ አለመረጋጋት መርምሮ ውሳኔ አስተላልፉዋል፡፡
የቡድኑ የመስክ ጉብኝት መረጃ እንዳመለከተው የቁጫ ህዝብና ነዋሪዎች ጥያቄ ማቅረብና ህዝባዊ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ የጀመሩት በወረዳዉ ምንም አይነት ልማትና ህዝቡም በፖለቲካውና በኢኮኖሚው ዘርፍ ለመሳተፍ የተሰጠው እድል ዝቅተኛ ወይም የለም በሚል ቁጭት ደረጃ በደረጃ የመብት ጥያቄ በማንሳት ነው፡፡ በተለይ ከሰኔ ወር 2005ዓ.ም ጀምሮ የህዝቡ ብሶት እየተባባሰ በመምጣቱ መንግስት ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል እርምጃ መውሰዱ በሪፖርቱ ተመልክቱዋል፡፡ 1015 የሚሆኑ ሰዎች በወረዳው ፖሊስ ጣቢያ፤ በአርባ ምንጭና በጨንቻ ወህኒ ቤቶች መታሰራቸው፤ አቶ ዛራ ዛላ የተባሉ የሁለት ልጆች አባት ህዳር 14ቀን 2006 ኮዶ ኮኖ ቀበሌ ውስጥ በጥይት ተመተው ሞተዋል፤ ሰውየው በጥይት ሲመቱ በቦታው የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ሶጋት ሳንታ፤ አቶ አሸብር ደምሴ የገዢው ፓርቲ የወረዳው ድርጅት ጉዳይ ሃላፊ እና አቶ አያኖ መሰና የወረዳው የፀጥታ ሃላፊ መኖራቸው ደግሞ የመንግስት ኃላፊዎችን ተባባሪ ወይም አስተኩዋሽ ያደርጋቸዋል፡፡ ከዚህም በቀር ህዝቡ በገዢው ፓርቲ ካድሬዎችና ፀጥታ ኃይሎች ማስፈራራት፤ ማዋከብና ሰርቶ የመኖር ነፃነቱ እንደሌለው እንዲሁም ያለመረጋጋትና የፀጥታ ስጋት ስላለ በርካታ ሰዎች ወደ ጎረቤት አካባቢዎች እየተሰደዱ መሆናቸውን ሪፖርቱ ይገልፃል፡፡
በተጨማሪም የወረዳው ህዝብ በሚጠራባቸው ስብሰባዎች ሁሉ የአንድነት ፓርቲ በወረዳው የዘረጋው ጠንካራ መዋቅር እንዲበተን በአንዳንድ የስብሰባው ተካፋዮች “አንድነት ፓርቲ እያለ ልማት አይኖርም፤ እንዴት አንድነትን መንቀል አቃታችሁ፤ የእኛው አካባቢ የፓርቲውን ሰዎች እንዴት ይዛችሁ ማሰር አቃታችሁ” የሚል አስተያየት በተሳታፊዎች የቀረበ በማስመሰል ኢህአዴግ የተለመደውን ድራማ እየሰራ ስለመሆኑ በቡድኑ ሪፖርት ተመልክቱዋል፡፡
እንዲሁም የልዑካኑን መሪ አቶ ትዕግስቱ አወሉ የብሄራዊ ምክር ቤት ዋና ጸሃፊን ጨምሮ ሰባት አባላት “እንዴት መጣችሁ፤ መንግስት በፀጥታ ችግር ላይ ነው፤ ይህንን ለመፍታት በሚደረገው ታላቅ ህዝባዊ ኮንፈረንስ እለት መገኘታችሁ አፋራሽ ተልእኮ ይዛችሁ የመጣችሁ ሰለሚሆን እንጠረጥራችኃለን” በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከአራት ሰዓት በላይ በማዋል በፀጥታ ኃይሎች የማዋከብ ተግባር ተፈፅሞባቸዋል፡፡ የአንድነት ፓርቲ ብሄራዊ ምክር ቤቱ በቀረበው ሰፊ ሪፖርት ላይ ውይይት ካደረገበት በኃላ የሚከተለውን የፖለቲካ ውሳኔ አስተላልፉዋል፡፡
1. በቁጫ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለው የሰብአዊ መብት ረገጣ በአስቸካይ እንዲቆምና ስለደረሰው ሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት የሚያጣራ በገለልተነኛ ወገን እንዲጣራ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲወሰን፤
2. የቁጫ ህዝብ ጥያቄ የስራዓቱ አምባገነናዊነት እንዲቆም በመሆኑ የህገ መንግስታዊ መብቶቻቸው ተከብረው ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያዘ የታሰሩት ዜጎች በአስቸካይ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱ፤
3. ቁሳዊና ስነልቦናዊ ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች የሞራል ካሳ እንዲሰጣቸው፤
4. በዜጎች ላይ ጉዳት ያአደረሱት ግለሰቦች ለህግ እንዲያቀርቡ፤
5. የገዢው ፓርቲ ካደሬዎች በየስብሰባው ፓርቲያችንን አሉታዊ በሆነ መልኩ ከመፈረጅ ይልቅ የዘጎችን ጥያቄ በህግና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት መንግስት ጥረት ያድርግ፤
6. የቁጫ ወረዳ ተወላጅ የሆነው የፓርቲያችን ከፍተኛ አመራር አባላትን ማሳደድና ማወከብ እንዲቆም፤
7. ይህ ሁኔታ የማይሻሻል ከሆነ በመዋቅራችን በመጠቀም በከፍተኛ ሰላማዊ ሰልፍ ህዝባዊ ተቃውሞ ፓርቲው በአካባቢው እንደሚጠራ፤ የፓርቲያችን ብሄራዊ ምክር ቤት ወስናል፡፡
በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ማንሳት የምንፈልገው ጉዳይ የኢህአዴግ አምባገነናዊ ስርአት በህዝብ ሙሉ ተሳትፎ በማስወገድ በአገራችን ዴሞክራሲያዊ ስርአት ለመገንባት አንድነት ፓርቲ እንደ አንድ የፖለቲካ አማራጭ ታግሎ ለማታገል ከተደራጀ አምስት አመት አልፎታል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ታህሳስ 19እና20 2006ዓ.ም የሚደረገውን ስትራቴጂካዊ ጠቅላላ ጉባኤን ጨምሮ ሶስት ጠቅላላ ጉባኤዎችን አድርጉዋል፡፡
የአሁኑን ጉባኤ ከአንድ ወር በፊት ለማድረግ ታቅዶ ለስብሰባ የሚሆነንን አዳራሽ ለማግኘት ከፍተኛ ፈተና ገጥሞናል፡፡ የአዳራሾቹ አከራዮች በምንፈልገው ቀን አዳራሹ አለመያዙን ይነግሩንና ለአንድነት ፓርቲ ለስብሰባ ነው የፈለግነው ሲባሉ አንዳንዶቹ እንደውልላችኃለን ሲሉን አንዳንዶቹ ደግሞ በግልጽ “እንስራበት ተውን” ይሉናል፡፡ የምርጫ ቦርድን አዳራሽ እንካን ጠይቀን የተሠጠን ምልሽ “ለስልጠና ፕሮግራም ተይዞበታል” ነው የተባልነው፡፡ በመጨረሻ ፈቅደው ያከራዩን ሰዎችንም ቢሆን ከፍተኛ ጫና ተደርጎባቸዋል፡፡ ከዚህ ሁኔታ መረዳት የሚቻለው ገዢው ፓርቲ ተቃዋሚዎችን ፈርቶ የንግዱን ህብረተሰብ ማሸበር እንደሆነ ነው፡፡
በጉባኤችን እስከ 500 የሚደርሱ የድምፅ ተሳታፊዎች፤ እስከ 150 ሚደርሱ ተጋባዥ የፖለቲካ መሪዎችና እንግዶች እንዲሁም የሚዲያ ባለሞያዎች ይገኙበታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ጉባኤው የፓርቲውን ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ፤ የብሄራዊ ምክር ቤት አባላትን፤ የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን ሪፖርቶችን ያዳምጣል ውሳኔም ያስተላልፋል፡፡እነዲሁም የፓርቲውን ፐሬዚደንት፤ የብሄራዊ ምክር ቤትና የኦዲትና ቁጥጥር ኮሚሽን አባላትን ይመርጣል፡፡ የፓርቲውን ፕሮግራምና ደንብ የማሻሻያ ረቂቆችን መርምሮ ያፀድቃል፡፡ ሌሎች ከተሰናባቹ ምክር ቤት የሚቀርቡለትን የውሳኔ ሃሳቦችን መርምሮ ያፀድቃል፡፡
አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ(አንድነት)
ታህሳስ 17ቀን 2006ዓ.ም
አዲስ አበባ

Monday 23 December 2013

በእስር ላይ የሚገኙት የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ አባላት በእስር ቤት ስቃይ እንደተፈጸመባቸው ገለጹ

በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የስነልቦናዊ እና አካላዊ ስቃይ አድርሰውብናል የሚሉት በእስር ላይ የሚገኙት የሙስሊሙ የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት፣ የደረሱባቸውን በደሎች ዘርዝርው አቅርበዋል።  ” ከአስራ አራት ሰአት በላይ ያለ እረፍት ቀጥ ብለን እንድንቆም በማድረግ፣ ጀርባችን ሰንበር እስኪያወጣ እና እስኪገሸለጥ ራቁታችንን በሽቦ በመግረፍ፣ በሰንሰለት በማሰር እና አይናችንን በጨርቅ በመሸፈን የውስጥ እግራችን እስከሚላጥ ገልብጦ በመግረፍ፣ ቀንና ማታ አሰቃቂ በሆነ ምርመራ እና ድብደባ እንቅልፍ በመንሳት፣ ሃይማኖታችንንና ክብራችንን በመንካት፣ ጺማችንን በመንጨትና እንድንላጭ በማስገደድ፣ እንዲሁም ሶላት በመከልከል፣ ቤተሰብ፣ ጠበቃ ፣ሀኪምና ሀይማኖት አባት እንዳናገኝ በማድረግ፣ ከአቅም በላይ የሆነን ስፖርት በግድ በማሰራት፣ ብልት በመግረፍ፣ ” ልጅህን እንገለዋለን! ሚስትህን አስረን በፊትህ ቶርች እናደርጋታለን! ብልትህ ላይ ሀይላንድ በማንጠልጠል ማሀን እናደርግሀለን” ሲሉ በማስፈራራት ከፍተኛ ስቃይ አድርሰውብናል ብለዋል።
በህገመንግስቱ አንቀጽ 18 ንኡስ አንቀጽ 1 ” ማንኛውም ጭካሄ ከተሞላበት፣ ኢሰብአዊ ከሆነ ወይም ክብርን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው” ቢልም፣ እኛ ግን ” ዜጎች መሆናችንን ጥርጣሬ ውስጥ በሚከት መልኩ ከያዙን በሁዋላ በማእከላዊ በክረምት ቀርቶ በበጋ እንኳን ቅዝቃዜው በማይቻለው ” ሳይቤሪያ” ተብሎ በሚጠራው ጨለማ ክፍል ለ3 ዋር አገሩው መቋቋም የሚአዳግተውን የማሰቃያ ስልታቸውን በመጠቀም አላሰብነውንና ያልሰራነውን ” እመኑ! ተናገሩ! ፈርሙ! ብለው አስገድደውናል”  ሲሉ በመግለጫቸው ጠቀስዋል።
ፍርድ ቤት ስቃዩን እንዲያስቆምልን ብንጠይቅም፣ ያገኘነው ውጤት ግን ወደ ማእከላዊ ስንመለስ ከመርማሪዎቹ በቀልና ተጨማሪ ስቃይ ነበር፣ የሚሉት ኮሚቴዎቹ፣ አሰቃዮቻችን ስለህገመንግስቱ እና መብት ስንናገር ” ህገ-መንግስቱን ቀደህ ጣለው፣ እኛ መስዋትንት ከፍለን ነው እዚህ የመታነው በማለት ለህግም ሆነ ለሰው ክብር ዴንታ እንደሌላቸው አሳይተውናል” ሲሉ አክለዋል።
ከቤተሰብ፣ ከጠበቃና ከሀኪም ጋር እንዳንገናኝ አድረገው የፈጸሙብን የህግ ጥሰት እና አስገድደው በማስፈረም እና ድምጽና ምስላችንን በመቅረጽ የፈጸሙብን በደል በወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቁጥር 424 መሰረት እስከ አስር አመት የ አስቀጣ ኢ-ሰብአዊ ተግባር ቢሆንም የፖሊሱም፣ አቃቢህጉም ፣ የፍርድ ቤቱም አለቃ በሆነውና የፍትህ ስርአቱን ሰብስቦ በያዘው ገዢው ፓርቲ አምባገነንነት በተቃራኒው እኛ ተከሳሽ ሆነን ጉዳያችን በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ይገኛል ብለዋል።
መንግስት በአግባቡ ሊተውነው ያልቻለውን አሳፋሪ የፍርድ ቤት ድራማውን ህዝብ እንዳያይበት ለመሸሸግ በመገደዱ የተከሰሱ ሰዎች ክስ ከቀረበባቸው በሁዋላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ በመደበኛ ፍርድ ቤት ለህዝብ ግልጽ በሆነ ችሎት የመስማት መብት አላቸው የሚለውን ህገመንግስታዊ መብት በመጣስ ችሎቱ ዝግ እንዲሆን ተደርጎ ቆይቷል የሚሉት የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት፣  በዝግ ችሎቱ የምስክር መስሚያ ጊዜ ብዙ አስገራሚ ድራማዎችን አይተናል፣ አቃቢ ህግ ዳኞች የሚሰጡትን ብይን እንደማይቀበሉ እስከመግለጽ የደረሱበትን እና ምስክሮችን ማለት ያለባቸውን አሰልጥነዋቸው እንደሚያመጡ አምልጧቸው የተናገሩበትን አጋጣሚ ” መታዘባቸውን ይገልጻሉ።
የኮሚቲው አባላት ” በሙስሊሞች መካከል እና በሙስሊሙና በክርስቲያኑ መካከል የታየውን አንድነትና መከባበር በጋራ መጠበቅ እንደሚያስፈልግ መክረዋል።  በጽናት ሰላማዊ የመብት ትግሉን የሚቀጥሉ መሆናቸውንና የሚያስከፍለውን መስዋትንት ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል። ለቀጣዩ ሰላማዊ የመብት ትግል እርከንም  በሙሉ ዝግጅት ላይ መሆናቸውን” ገልጸው፣ መንግስት በማእከላዊ እስር ቤቶች የሚፈጸሙትን ኢ-ሰብአዊ ድርጊቶች እንዲያስቆምና የህሊና እስረኞችን እንዲለቅ ጠይቀዋል።

በቀብሪ ቤያህ እስር ቤት ውስጥ የሞቱ ሰዎች የሉም ሲል የክልሉ ፖሊስ አዛዥ አስተባበሉ

የክልሉ ጽህፈት ቤት ፖሊስ አዛዥ  ከጅጅጋ 25 ኪሜ ገደማ በምትገኘዋ ቀብሪበያህ እስር ቤት ውስጥ የሞቱ ሰዎች ስለመኖራቸው ሪፖርት እንዳልደረሰቻው ገልጸዋል። አዛዡ እንዳሉት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ሽብረተኞችን በተመለከተ ከፌደራል መንገስቱ የጸረ ሽብር ግብረሀይል ጋር በጋራ የሚሰሩ በመሆኑ፣ በዚሁ ወንጀል ተጠርጥረው የሚያዙ ካሉ በጋራ የሚታይ ጉዳይ ይሆናል ሲሉ አክለዋል
በጅጅጋ የተከበረውን የብሄር ብሄረሰቦች በአል ምክንያት በማድረግ “መታወቂያ የላቸውም፣ የከተማዋን ገጽታ ያበላሻሉ፣ ከተማዋን ያቆሽሻሉ፣ የጸጥታ ስጋት ደቅነዋል በሚል ከ770 በላይ ሰዎች ቀብሪበያህ በሚባለው ወረዳ ውስጥ በአንድ ክፍል ውስጥ እንዲታሰሩ ከተደረጉት መካከል ከ40 በላይ የሚሆኑት መሞታቸውን ማንነታቸው እንዳይታገለጽ ከጠየቁ የክልሉ ባለስልጣናት ያገኘውን መረጃ በመንተራስ ዘገባ መስራታችን ይታወሳል።
እስረኞቹ የሞቱት በምግብ እጥረትና በእስር ቤቱ ውስጥ በተነሳ የታይፎይድ ( ተስቦ) በሽታ መሆኑን የዜናው ምንጮች ገልጸዋል። ዘመዶች የሞቱባቸውንና ለቅሶ የተቀመጡ ሰዎችን ኢሳት ለማነጋገር ቢሞክርም፣ ሰዎቹ  ለደህንነታቸው በመስጋት ለመናገር ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ሰዎችን ከከተሞች በመውሰድ ያሰሩዋቸው በክልሉ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት ልዩ ሚሊሺያ እየተባሉ የሚጠሩት ታጣቂዎች መሆናቸውን ምንጮች አክለው ገልጸዋል። ማንኛውም የሰብአዊ መብት ድርጅት በአካባቢው በመሄድ በቀላሉ ማረጋገጥ የሚችለው ሀቅ ነው በማለት የክልሉ ፖሊስ አዛዥ የሰጡትን ማስተባበያ ውድቅ አድርገዋል። ለሁለት ወራት ያክል ታስረው የነበሩት በተለያዩ ምክንያቶች የታሰሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ባለፈው ሳምንት መለቀቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

ገዢው ፓርቲ የአንድ ለአምስት አደረጃጀትን ወደ ቤተሰብ አወረደ

 ገዢው ፓርቲ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ፣ በትምህርት ቤቶች ፣ በአርሶ አደሩና በከተማው ነዋሪዎች ላይ  ሲዘረጋ የቆየውን የአንድ ለአምስት አደረጃጀት በቤተሰብ ደረጃ ለማዋቀር የተለያዩ ደብደባዎችን እየበተነ ነው።
የቦሌ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ለወረዳ 02 የቤተሰብ አባላት ባዘጋጀው የቤተሰብ ማቋቋሚያ ቅጽ ላይ የቤተሰብ ፖሊስ መመስረት ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ” በቤተሰብዎ መካከል ለሚፈጠሩ የጸጥታ ችግሮች ማለትም ያለመግባባቶች፣ የተለያዩ ማህበራዊ ግችቶች ወዘተ የመሳሰሉት ችግሮች ሲፈጠሩ እርስዎ ወይም የቤተሰብዎ  ወኪል እንደ ፖሊስ ሆኖ በቅርበት ከፖሊስ ጋር እየተወያየ የማስታረቅ፣ የማስማማት ስራ እንዲሰራ እና ችግሩን እየተከታተለ እዛው መፍትሄ እንዲሰጥና መፍታት ያልተቻለ በአካባቢው ከተመደቡት የፖሊስ አባላት ጋር ለመፍታት ታስቦ የተዘጋጀ ነው” ይላል።
በቤተሰብ ፖሊስ ማቋቋሚያ ቅጹ ላይ ” የመራች የቤተሰብ ፖሊስ ወይም ተወካይ ስም፣ የቤተሰብ ብዛት፣ ስልክ ቁጥር፣ የተወካይ ፊርማ፣ መንደር ወይም ልዩ ቦታ፣ የብሎክ ቁጥር፣ ብሄርና መግለቻ የሚሉ  ጥያቄዎች ተካተዋል።
በተመሳሳይ ዜናም የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ በከተማው ውስጥ በሚገኙ አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የመማር ማስተማሩን ሒደት በጥራት ለማከናወን ይረዳል በማለት ‹‹ኮማንድ ፖስት›› የተሰኘና ሌሎች ተጨማሪ አደረጃጀቶች በማስተዋወቅ ላይ መሆኑን ሪፖርተር ዘግቧል።
የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በዳግማዊ ምኒሊክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በከተማው ከሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ለተጠሩ ርዕሳነ መምህራን፣ ሱፐርቫይዘሮችና ከሁሉም ክፍላት ከተሞችና ወረዳ ጽሕፈት ቤቶች ለተወከሉ ኃላፊዎች በአዲሶቹ አደረጃጀቶች ዙሪያ ገለጻ አድርጓል።
በቅርቡ ወደ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ይወርዳል ከተባለው የኮማንድ ፖስት አደረጃጀት በተጨማሪ፣ ‹‹ትራንስፎርሜሽን ፎረም›› እና ‹‹የልማት ቡድን›› የሚሰኙ አደረጃጀቶችም እንደሚተዋወቁ ጋዜጣው ዘግቧል።
‹‹ኮማንድ ፖስት›› አደረጃጀት ዋና ተግባሩ ትምህርት ቤቶችን ከሕዝባዊና ከመንግሥት ክንፎች ጋር ማስተባበር እንደሆነ የዘገበው ጋዜጣው ፣ የ‹‹ትራንስፎርሜሸን ፎረም›› እና ‹‹የልማት ቡድን›› የተባሉት አደረጃጀቶችም በየትምህርት ቤቱ በሚገኙ የትምህርት ክፍሎች ውስጥ ተግባራዊ የሚደረጉ ሲሆን፣ ‹‹አንድ ለአምስት›› በሚል ስያሜ የተጀመረውን አደረጃጀት ለማጠናከርና ለማስቀጠል ጠቃሚ መሆናቸው ተመልክቷል።
ላለፉት ጥቂት ዓመታት በ‹‹ግንባር ቀደም›› አደረጃጀት በኋላም በ‹‹ተጓዳኝ›› አማካይነት የተከናወነው ሥራ የታሰበውን ውጤት ማምጣት አለመቻሉ ግልጽ መሆኑ በመታወቁ ‹‹ኮማንድ ፖስት›› የተባለውን አደረጃጃት ለማስተዋወቅ አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ ተገልጿል።
መንግስት የትምህርት ጥራት ለማሻሻል ‹‹ተጓዳኝ›› የሚባለውን አደረጃጀት ማምጣቱን ቢገልጽም፣ አንዳንድ መምህራን ግን መንግሥት መምህራኑን ‹‹ለመጠርነፍ›› ሲል ያመጣቸውና ‹‹ከጥቅሙ ጉዳቱ የሚያመዝን አላስፈላጊ መሣሪያ›› ነው ሲሉ ውድቅ ያደርጉታል።
ጋዜጣው አያይዞም ፣ ‹‹አደረጃጀት በዛ፣ እኛም ለማስፈጸም እየተቸገርን ነው፤›› በማለት ርዕሰ መምህራን ለትምህርት ቢሮ ኃላፊው መግለጻቸውን ዘግቧል፡፡ ባለስልጣኑ ግን መምህራን የማሳመን ስራ መስራት ይኖርባቸዋል በማለት የርእሰ መምህራኑን ቅሬታ ሳይቀበሉት ቀርተዋል።
ጋዜጣው ያነጋገራቸው መምህር ስለአደረጃጀት መብዛት ተጠይቀው  ‹‹አደረጃጀት በማለት መንግሥት በየትምህርት ቤቶቻችን የሚያመጣብን አሠራሮች ብዙ ጊዜ መምህራንን ከማባሳጨት አልፎ የትምህርት ጥራትን የባሰ እየገደለ ነው፤›› በማለት መልሰዋል።
መንግስት የአገሪቱን ህዝብ በመላ በአንድ ለ አምስት አደረጃጀት ለመቆጣጠር ያስባል በሚል ወቀሳ እቀረበበት ቢሆንም፣ ኢህአዴግ በ9ኛው መደበኛ ጉባኤ በአደረጃጀቱ እንደሚገፋበት ውሳኔ አሳልፎአል።

በተንቤን ህዝባዊ ስብሰባ ተደረገ! (አብርሃ ደስታ – ከትግራይ)

መቀሌ መነሃርያ ስትገቡ ብዙ ተሽከርካሪዎች ተሳፋሪ ሲጠባበቁ ታያላቹ። ረዳቶች ‘የት ናችሁ? እዚህ ግቡ!’ ምናምን እያሉ ይሽቀዳደሙላችኋል፣ ይለሙኗችኋል። በመነሃርያው ብዙ አቅጣጫዎች መኪኖች መልተው ተጓዥ ሰው ይጠባበቃሉ። በአንድ ኮርነር ጥግ ግን ብዙ ተጓዝ ሰዎች የአንድ አውቶቡስ መምጣት ለብዙ ሰዓታት ይጠባበቃሉ። እነዚህ ለሰዓታት የሚንገላቱ ሰዎች ወደ ተምቤን ዓብይ ዓዲ የሚጓዙ ሰዎች ናቸው።
ቅዳሜ ጠዋት (ሁለት ሰዓት) ወደ ተምቤን ዓብይ ዓዲ ለመሳፈር መነሃርያ ገባሁ። ወደ ዓብይ ዓዲ ከተማ የሚሄድ መኪና የለም። ወደ ሌሎች ከተሞች የሚሄዱ መኪኖች ግን ሞልተዋል። በመነሃርያው የሚቆዩ በቂ ተሳፋሪ እስኪያገኙ ድረስ ነው። ወደ ተምቤን የምንጓዝ ግን የመነሃርያው አቧራ ሳይበግረን በትዕግስትና በተስፋ እንጠባበቃለን። ከሁለት እስከ አምስት ሰዓት ጠበቅን። ሲጨንቀን የትራንስፖርት ሓላፊዎቹ አማከርን። ‘ሁሌ እንደዛ ነው! ጠብቁ! ይመጣሉ’ አሉን።
ሁሌ እንደዛ መሆኑ አዋቅ ነበር። ወደ ተምቤን ዓብይ ዓዲ ስጓዝ ለሦስተኛ ግዜየ ነው። በሦስቱም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞኛል። ‘ግን ለምንድነው ወደ ተምቤን የሚሄዱ መኪኖች የሌሉ?’ ብለን ጠየቅን። ‘መንገዱ ችግር ስላለበት ሹፌሮች ወደ ተምቤን መሄድ ስለማይፈልጉ ነው’ የሚል መልስ አገኝን። ሚኒባሶች ጭራሽ አይሄዱም። የተወሰኑ አውቶብሶች ብቻ ናቸው ወደ ዓብይ ዓዲ የሚመላለሱ።
ምን ማድረግ እንዳለብን ጠየቅናቸው። ‘ፐርሰንት ከፍላቹ ከባለባሶች ጋር መደራደር ትችላላቹ’ አሉን። ለመደራደር ወስነን ተስማማን። ሰልፍ ይዞ የነበረ ህዝብ ግን ብዙ ነው። በአንድ አውቶቡስ ሊጫን አይችልም። በሃይል ሩጠን፣ ተረጋግጠን፣ ሴቶችና ህፃናት አልፈን ገባን (ሰብአዊነት ቀረ)። የተወሰንን ተሳፈርን አብዛኛው ቀረ። ሁለት ሰዓት መነሃርያ የገባን ሰባት ሰዓት ጉዞ ጀመርን።
ተምቤን ዓብይ ዓዲ ከመቀሌ በስተ ምእራብ (?) በ90 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኝ ነው። መንገዱ በጣም አስቸጋሪ ከመሆኑ የተነሳ ሰባት ሰዓት ተነስተን አስራ አንድ ሰዓት ደረስን። ለዘጠና ኪሎሜትር ርቀት አራት ሰዓት ፈጀብን።
ዓብይ ዓዲ የጥንት ከተማ ነው። ከዉቅሮ ቀጥሎ ለመቀሌ ቅርብ የሆነ ከተማ ዓብይ ዓዲ ነው። ሁሉም ዋና ዋና የትግራይ ከተሞች ከመቀሌ የሚያገናኝ አስፋልት መንገድ ተገንብቶላቸዋል (ከዓብይ ዓዲ ከተማ ዉጭ)። የኢህአዴግ መንግስት ዓብይ ዓዲ ከመቀሌ ከተማ ጋር በአስፋልት መንገድ ለማገናኘት ሃያ ሦስት ዓመት ፈጅቶበታል።
የተምቤን ህዝብ በ1996 ዓም ጥያቄ አስነስቶ ተቃውሞውን በሰለማዊ ሰልፍ ገልፀዋል። በወቅቱ ከተነሱት ጥያቄዎች የፍትሕ እጦት፣ የመብራትና የውኃ አገልግሎቶች፣ የአስፋልት መንገድ ጉዳይ ዋናዎቹ ነበሩ። የተቃውሞ ሰልፉ መሰረታዊ ምክንያትም ህወሓት በተምቤን ህዝብ ላይ አድልዎ እየፈፀመ ነው፤ ልማት እንዳናገኝ ተደርገናል፣ የተለየ ዓፈና ይደርስብናል ወዘተ የሚል ነበር።
ህወሓት ጥያቄያቸውን ከመመለስ ይልቅ ‘የተምቤን ህዝብ ከተነሳ ለስልጣን አደጋ ይሆናል’ በሚል ምክንያት የተቃውሞው አስተባባሪዎች በማስፈራራት ከተምቤን መሬት ለቀው እንዲጠፉ ተደረገ። አስተባባሪዎቹን በማባረር የተቀረውን በሃይል መጨፍለቅ ጀመሩ። የተቃውሞው መንፈስ አዳከሙት። አሁን የተምቤን ህዝብ አንድነት ፈጥሮ እንዳይታገላቸው በመስጋት ህዝቡ ይከፋፍሉታል፣ እርስበርሱ እንዳይተማመን ያደርጉታል። ጥያቄ ያነሳ ካለ ከሀገሩ ያባሩታል።
የተቃውሞ ሰልፉ ይመሩት ከነበሩ ወላይ ጫዓ አንዱና ዋነኛው ነበር። ወላይ ጫዓ ከተምቤን ተባሮ በሌላ ቦታ ለብዙ ግዜ ከተቀመጠ በኋላ አሁን ወደ ዓብይ ዓዲ ተመልሷል (በዓብይ ዓዲ ከተማ በ አካል አግኝቼው ነበር)። በ1996 ዓም የትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር የነበሩ አለቃ ፀጋይ በርሀ ወላይ ጫዓን በጣም ይፈሩት እንደነበር የዓብይ ዓዲ ኗሪዎች አጫውተውኛል። አለቃ ፀጋይ ወላይ ጫዓን ከመፍራታቸው የተነሳ የተቃውሞ ሐሳብ የሚያነሳ ሁሉ ‘ወላይ ጫዓ’ ይሉ እንደነበር ነው የተነገረኝ።
በ1996 ዓም የተጠየቁ የመብራትና የዉኃ ችግሮች እስካሁን ድረስ ተገቢ መልስ አልተሰጣቸውም ብለው ኗሪዎች ያምናሉ። የአስፋልት መንገዱ ጉዳይ ግን ከአስር ዓመት በኋላ አሁን ተጀምሯል (ይቅርታ ከተመጀመረ ዓመታት ተቆጠረዋል፣ ግን እስካሁን ድረስ 30% እንኳን አልተጠናቀቀም)። በመንገዱ ጥራትም ብዙ ጥያቄዎች ይነሳሉ። የመንገዱ የተወሰነ አካል ይሰራሉ፤ ከወራት በኋላ ደግሞ ችግር አለበት ተብሎ አስፋልቱ ሳይጨርሱ መጠገን ይጀምራሉ።
በዓብይ ዓዲ ከተማ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ችግር አለ። ህዝቡ የመንግስት አገልግሎት በአግባቡ አያገኝም። ‘የራሳችን ሰዎች ያስተዳድሩን’ የሚል ጥያቄ አለ። ህወሓት ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የዓብይ ዓዲ ህዝብ በተምቤን ተወላጆች እንዲተዳደር ለማድረግ ሞክሮ አልተሳካለትም። የዓብይ ዓዲ ከተማ ከንቲባ ለመምረጥ ሦስት የተለያዩ የተምቤን ተወላጆች ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። የተምቤን ተወላጆቹ ግን ቅድመ ሁኔታ አስቀመጡ። የተምቤን ተወላጆቹ ‘የከንቲባነት ስራ ለመስራት ከተፈለገ ህዝቡን በቅንነት ለማገልገል ነፃነቱ ሊሰጠን ይገባል! የህዝቡ ጥያቄዎች ለመመለስ ሊፈቀድልን ይገባል’ የሚሉ ቅድመ ሁኔታዎች አቀረቡ። ህወሓቶች አልተቀበሉትም። በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት የዓብይ ዓዲ ከተማ ለብዙ ግዜ ያለ ከንቲባ ቆየች። አሁን ሲጨንቃቸው ግን በሙያው ያልሰለጠነ የከተማው የፖሊስ አዛዥ የነበረ የከተማው ከንቲባ እንዲሆን መርጠውታል።
ዓረና መድረክ ዕለተ እሁድ ከተምቤን ህዝብ ጋር ለመወያየት ዕቅድ ይዞ ስለነበር ከአራት ቀናት በፊት ነበር ቅስቀሳ የጀመረው። ከዚህ በፊት በሌሎች አከባቢዎች ባደረግናቸው ቅስቀሳዎች (በቅስቀስ ወቅት) የተምቤን ያህል በአስተዳዳሪዎች ተፅዕኖ አልደረሰብንም። የዓረና መድረክ የተምቤን የቅስቀሳ ቡድን በየጭላ፣ ወርቅ አምባ፣ ሀገረሰላምና ዓብይ ዓዲ ታስረዋል። ይህ የተደረገው የቅስቀሳ ሂደቱ ለማሰናከል ነበር።
የተምቤን አስተዳዳሪዎች (በሌሎች አከባቢዎችም እንደሚደረግ ሁሉ) ህዝብ በስብሰባው እንዳይሳተፍ ለማፈን በየዘርፉና በየአከባቢው በዕለተ እሁድ የራሳቸው ስብሰባ ጠርተዋል። በተለየ ሁኔታ የዓብይ ዓዲ መምህራን ኮሌጅ መምህራንና ተማሪዎች በዓረና ስብሰባ እንዳይካፈሉ ለማድረግ ባልተለመደ መልኩ ለእሁድ ስብሰባ ተጠሩ። የኮለጁ አባላት ብዙ ጥያቄዎች አሉዋቸው።
እሁድ ጠዋት የማዘጋጃቤት ሰራተኞች፣ የፖሊስ አዛዦች፣ የዓብይ ዓዲ ከተማ የእያንዳንዱ ቀጠና ተጠሪ ካድሬዎች በስብሰባው አደራሽ በር አከባቢ ተቀመጡ። ለስብሰባ የመጣ ሰው እነሱን አይቶ ሰግቶ እንዲመለስ ለማድረግ ወይም በስብሰባው የተሳተፈ ሰው ለመመዝገብ ነበር የተቀምመጡት።
ህዝቡ ግን እነሱን ሳይፈራ በድፍረት ወደ አደራሹ መግባት ጀመረ። አደራሹ መልቶ ነበር ማለት ይቻላል። የተምቤን ስብሰባችን ለየት የሚያደርገው ህዝቡ ለመከልከል የተሰማሩ ካድሬዎች ራሳቸውም በአደራሹ ገብተው የስብሰባው ተካፋይ ሁነው፣ ጥያቄዎች መጠየቃቸውና መከራከራቸው ነበር። ካድሬዎቹም አመስግነናል (ከኛ ጋር መከራከር በመቻላቸው)። በስብሰባ ገብቶ የመከራከር ባህል ሊዳብር የሚገባ ነው።
ሞቅ ያለ ዉይይት ተደረገ። ደስ የሚል ነበር። ህዝቡ ስለሚደርሰው ችግር ተናገረ። ስለ የራስ አሉላ አባነጋ ትምህርትቤት ስያሜ መቀየር ያለው ቅሬታ ገለፀ። የተምቤን ህዝብ ለማዳከም ለሁለት መከፈሉ እንደሚቃወም አስረዳን። ደጉዓ ተምቤን ወረዳ ከዋናው ተምቤን ተነጥሎ ወደ ደቡባዊ ምስራቅ ዞን እንዲሆን መወሰኑ ይታወቃል። ተምቤን ራሱ የቻለ ዞን መሆን እንዳለበትም ተነስቷል። ተምቤን ዞን እንዲሆን ሕግም ይፈቅድለታል። ምክንያቱም አንድ አከባቢ አራትና ከዛ በላይ ወረዳዎች ካሉት የዞንነት ደረጃ የማግኘት ዕድል አለው። ተምቤን አራት ወረዳዎች አሉት፤ (1) ደጉዓ ተምቤን፣ (2) ጣንቋ አበርገለ፣ (3) ቆላ ተምቤንና (4) ዓብይ ዓዲ።
የተምቤን ህዝብ ለውጥ ፈላጊ ነው። ለለውጥ የሚመራው የተደራጀ ሃይል ብቻ ነው የሚያስፈልገው። የህወሓት ሰዎችም የተምቤንን ህዝብ በተለየ ሁኔታ ይፈሩታል። በተምቤን ህዝብ አጠራር ህወሓት ‘ቂመኛ’ ነው። ቂም ይዞ ነው ተምቤኖችን የሚበድለው።
ባጠቃላይ የተምቤን ስብሰባችን ተስፋ ሰጪ ነበር። በድልም ተጠናቋል። ቀጣዩ ጉዟችን ወደ ዓዲ ግራት ወይ ሽሬ ይሆናል።