Sunday, 5 October 2014

ሚ/ር ሽፈራው በመሥሪያ ቤቶች እና በትምህርት ቤት አካባቢ ክርስቲያኖች ክር እና መስቀል ከማሰር እንደሚከለከሉ አስታወቁ

የሐራ ተዋሕዶ ትንታኔ
ሚኒስትር ሺፈራው: በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የክርስቲያንነት መታወቂያችንን ማዕተብ ከማሰር እንደምንከለከል አስታወቁ፤ ማዕተባችንን እናጥብቅ!
ከሥልጠናው ተሳታፊዎች ከፍተኛ ተቃውሞ አጋጥሟቸዋል፤ ከሥራ ባልደረቦቻቸውም ጠንካራ ጥያቄ ቀርቦባቸዋል፡፡
‹‹በሴኩላሪዝም ሰበብ ማዕተብኽን በጥስ ማለት ሃይማኖትን ከማስካድና እንደ ሰቃልያነ አምላክ አይሁድ መስቀሉን ለመቅበር ከመሞከር ተለይቶ አይታይም፡፡ ሃይማኖት፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እና ታሪካዊ ትውፊት እንዳይፋለስ የመጠበቅና የማስጠበቅ ሓላፊነት ያለበት ቅዱስ ሲኖዶስ በጥንቃቄ ሊከታተለው ይገባል፡፡›› /የሥልጠናው ተሳታፊዎች/
‹‹ፈትል አንድነት እየሸረቡ ለክርስትና ሕይወት መግለጫ በክርስትና ጥምቀት ጊዜ አንገት ላይ ማሰር በቤተ ክርስቲያናችን የጸና ኾኖ ሲሠራበት ይኖራል፡፡›› /የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ/
* * *
የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም
የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ሺፈራው ተክለ ማርያም
‹‹ሚኒስትሩ የመንግሥትን ሴኩላርነት ለማረጋገጥ በሚል የሰጧቸው አስረጅዎች የግልጽነትም የአግባብነትም ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ የሚበዛው ኢትዮጵያዊ አማኝ ከመኾኑ አንፃር ትርጉም እንዳለውና በሕገ መንግሥቱ እምነት ነክ ድንጋጌዎች እንደተንጸባረቀ ከሚታመነው የሴኩላሪዝም ፈርጅ (positive secularism) ይልቅ በርእዮትና አሠራር የተደገፈ ሃይማኖትንና ሃይማኖተኝነትን የማዳከም (negative secularism) አዝማሚያዎች ያይልባቸዋል፡፡ ከእምነት ተቋማት ጀርባ የግንባሩን አባላት ጨምሮ ሰፊው አማኝ ሕዝብ መኖሩን ታሳቢ ያደረገ ‘በነፃነት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ መስተጋብር’ እንደሚኖር በመንግሥት የኢንዶክትሪኔሽን ጽሑፎች ከተቀመጡት አቅጣጫዎች ጋራም የሚጣጣሙ አይደሉም፡፡ በተለይ ከቤተ ክርስቲያናችን አንፃር ለተነሡ ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ፣ በፓወር ፖይንት ካቀረቡት ዶኩመንት ያለፈና ‘more of personal’ የሚመስል ‘issue’ ያላቸው ነው የሚመስለው፡፡ በዚኽ አኳኋን እንዴት ነው ዜጎች ‘ሚዛናዊ አስተሳሰብ’ እንዲያዳብሩ የሚጠበቀው? ከመንግሥት ጋራ አብሮ መሥራትስ እንዴት ይቻላል?››
‹‹ክርስትናችን ‘የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጥ’ የሚል ሴኩላሪዝምን በአዎንታዊነትና በቀላሉ የሚገልጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ያለው ነው፡፡ በሚኒስትሩ የተብራራው የሴኩላሪዝም መርሖ ግን ምእመኑን ለእምነቱ ለዘብተኛ በማድረግ በሒደት ወደ ሃይማኖት አልባነት የመምራት ተንኰል የተሸሸገበት ያስመስላል፡፡››
‹‹ክርስቲያንነታችንን በየራሳችን የምንመሰክርበት መለዮአችን ማዕተብ ለመንግሥት ሴኩላርነት ተፃራሪ እንደኾነና ሊከለከል እንደሚችል መናገር ስለ መንግሥት የሴኩላሪዝም መርሖ የተሳሳተ መልእክት በማስተላለፍ ሰፊውን አማኝ ፀረ – ሴኩላር የሚያደርግ፣ ሕዝቡንና መንግሥትንም ፊት ለፊት የሚያፋጥጥ እንዳይኾን ያሰጋል፡፡››
/የመንግሥት መካከለኛ አመራሮች የኾኑ ኦርቶዶክሳውያን የሥልጠናው ተሳታፊዎች/

የክርስቲያንነት መለዮአችን፣ የርትዕት ሃይማኖት ምስክራችን የኾነውን ማዕተብ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና በትምህርት ተቋማት አስሮ ከመታየት ልንከልከል እንደምንችል የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ሚኒስትር ሺፈራው መናገራቸው ተሰማ፡፡
የመንግሥትን የሴኩላሪዝም መርሖና የፀረ አክራሪነት አጀንዳ ተገን በማድረግ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ርእዮታዊ እና ሃይማኖታዊ ጥላቻቸውን በማስተጋባት የሚታወቁት ሚኒስትር ሺፈራው፣ ይህን መናገራቸው የተጠቆመው፣ ከነሐሴ ፲፰ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ጀምሮ እስከ መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ድረስ በዘለቀውና በኹለት ዙሮች በተካሔደው የመንግሥት መካከለኛ አመራሮች ሥልጠና ላይ ነው፡፡
በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ በተካሔደውና 800 ያህል መካከለኛ አመራሮች በተሳተፉበት የፖሊሲና ስትራተጂ ሥልጠና ‹‹የልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ግንባታና ፈተናዎቹ›› የሚለውን ሰነድ የሚያብራራና በፓወር ፖይንት የተደገፈ ጽሑፍ ያቀረቡት ሚኒስትሩ የመንግሥትን የሴኩላሪዝም መርሖ መነሻ ያደረገ ነው የተባለ ጥያቄ ከአንዲት ተሳታፊ ቀርቦላቸዋል፡፡
እንደ ስብሰባው ምንጮች፣ የተሳታፊዋ ጥያቄ፣ ‹‹በቢሮ ፊታቸውን ተሸፍነው የሚመጡ ሙስሊሞችን አለባበሳቸው ከቦታው አንፃር ያለውን ተገቢነት በማንሣት እንዲያወልቁ ስንጠይቃቸው ‘እኛ ይኼን የምናወልቅ ከኾነ ኦርቶዶክሱም ክሩን ይበጥስ’ ይሉናል፤ ይኼን እንዴት ነው የምንታገለው?›› የሚል ነበር፡፡
‹‹መንግሥታችን ሴኩላር ነው›› ሲሉ በጠያቂዋ የተጠቀሰውን ዐይነት አለባበስ የተቹት ሚኒስትሩ፣ ‹‹እርሱም [ማተቡም] ቢኾን የጊዜ ጉዳይ ነው፤ እንደ የሃይማኖት መለያ እስካገለገለ ድረስ አደረጃጀታችንን ስንጨርስ ማተብም ቢኾን መውለቁ አይቀርም፤›› የሚል ምላሽ መስጠታቸው ተገልጧል፡፡
የሥልጠናው ተሳታፊዎች ከፍተኛ ማጉረምረም በማሰማት በሚኒስትሩን ምላሽ ላይ ተቃውሟቸውን መግለጣቸው ተጠቅሷል፡፡ ሌላው ተሳታፊም፣ ‹‹በመሠረቱ ፊት መሸፈንን ማዕተብ ከማሰር ጋራ ማመሳሰል ልክ አይመስለኝም፤ ማተብም ቢኾንኮ ከሃይማኖታዊነት አልፎ ማንነትና ባህል ኾኗል፤ ማስቀረቱ አደጋ አለው፤›› ሲሉ ከተሳታፊው ከፍተኛ የጭብጨባ ድጋፍ እንደተቸራቸው ተዘግቧል፡፡
ሚኒስትሩ ‹‹ይኼ ግን የዚኽ ሥልጠና አካል አይደለም›› በሚል የተሰብሳቢውን ተቃውሞ ለማለሳለስና እንደዋዛ ለማለፍ ቢሞክሩም ጉዳዩ በዕረፍት ሰዓት በከፍተኛ ስሜት ከማወያየት አልፎ የሚኒስትሩን አጠቃላይ አቀራረብና ስውር ፍላጎት የተመለከቱ ቅሬታዎች ሲሰነዘሩም እንደነበር ተሰምቷል፡፡ ‹‹የሰውዬው ዓላማ ኹላችንን ፕሮቴስታንት ማድረግ ነው ወይ?›› ያሉ አንድ ተሳታፊ የሥልጠናውን አስተባባሪዎች ‹‹ለምንድን ነው የማትነግሩት?›› በማለት በቁጣ ጠይቀዋል፡፡
የሚኒስትሩ ምላሽ ጥንቃቄ የጎደለው እንደኾነ የጠቀሱ ሌላ አስተያየት ሰጭ፣ መንግሥታዊ ሥራን ከሃይማኖታዊ ውግንና አድልዎ ተጠብቆ በገለልተኝነት ማካሔድ እንደሚገባ ቢያምኑም ይህ በዋናነት የሚገለጸው በሲቪል ሰርቪሱ ሓላፊዎች አመራርና የውሳኔ አሰጣጥ፣ በሠራተኞች አቀራረብና የሥራቸው አፈጻጸም እንደኾነ አስረድተዋል፡፡ እንደ ጥያቄው አቀራረብና እንደ ሚኒስትሩ ምላሽ፣ ማዕተብ ከአለባበስ ጋራ ተዘምዶ ከተወሰደም የሴኩላር መንግሥትን የገለልተኝነትና የእኩልነት መርሕ የሚጥስበት አልያም የሠራተኛውን ገጽታ በግልጽ ለመለየት የሚያግድበት ከዚኽም ጋራ ተያይዞ የማኅበረሰብ ሰላምና የደኅንነት ጥያቄ የሚያሥነሳበት ኹኔታ በማንም ዘንድ ሊኖር እንደማይችል አብራርተዋል፡፡
‹‹ከአለባበስ አኳያ የሴኩላሪዝም መርሖን ለማረጋገጥ ሃይማኖታዊ ግዴታ ያለባቸውንና የሌለባቸውን አለባበሶች ከግምት ያስገባል፤›› ያሉት አስተያየት ሰጭው፣ ማዕተብ *÷ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጥምቀተ ክርስትና አፈጻጸም * * እያንዳንዱ ተጠማቂ የእግዚአብሔር ልጅነትን በጸጋ አግኝቶ የተስፋው ተካፋይ የርስቱ ወራሽ ለመኾን በሰማያዊ ዜግነት የሚታተምበት የሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን አካል የመኾኑን የሃይማኖት መግለጫነት መሠረታዊነት በአጽንዖት አስገንዝበዋል፤ ዕቱባን አንትሙ በቅድስት ጥምቀት እንዲል፡፡
ከዚኽም በተጨማሪ ማዕተብ÷ የሲኦል መሠረት የተናወጠበት፣ ሰውንና እግዚአብሔርን ለዘመናት ለያይቷቸው የነበረው የጠብ ግድግዳ የተናደበት፣ የሞት ኃይሉ ተሽሮ የትንሣኤ መንገድ የተከፈተበት መስቀል ትእምርት በመኾኑ በተሳሳተ የሴኩላሪዝም ግንዛቤ ‹‹ማዕተቡም ሊወልቅ ይችላል›› ማለት፣ ‹‹ሃይማኖትን ከማስካድና እንደ ሰቃልያነ አምላክ አይሁድ መስቀሉን ለመቅበር ከመሞከር ተለይቶ አይታይም፤ ጉዳዩንም ሃይማኖት፣ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንና ታሪካዊ ትውፊት እንዳይፋለስ የመጠበቅና የማስጠበቅ ሓላፊነት ያለበት ቅዱስ ሲኖዶስ በጥንቃቄ ሊከታተለው ይገባል፡፡›› ሲሉ አሳስበዋል፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን vs. ቦኮ ሐራም
mahbere qdusanየሚኒስትር ዶ/ር ሺፈራው ምላሽ ጥንቃቄ የጎደለው ነው የሚለውን አስተያየት የሚጋሩት ሌላው ተወያይ የበኩላቸውን ሲያክሉ፣ ‹‹ከዚኽም በላይ ግን በተለይ ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አንጻር ለተነሡ ጥያቄዎች፣ ‘ማኅበራት’ እያሉ በማስረገጥ ምላሽ ሲሰጡ፣ በፓወር ፖይንት ካቀረቡት ዶኩመንት ያለፈና ‘more of personal’ የኾነ ‘issue’ ያላቸው በሚያስመስል ልዩ አጽንዖት ሲናገሩ ነው የሚታዩት፤›› ብለዋል፡፡
‹‹አብረን ተቻችለን በሰላም ኖረናል እየተባለ ስለ አክራሪነት ተጋኖ የሚነሣበት ኹኔታ አለ፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለመንግሥት ተጨባጭ ስጋት የኾነ አካል አለ ወይ?›› ተብሎ በጽሑፍ ለቀረበው ጥያቄ ሲመልሱ ትኩረት ያደረጉት÷ ‘በትምክህተኝነት፣ በሥልጣን ጥመኝነት፣ በቀለም ዐብዮት ሰባኪነት’ በከሰሷቸው የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ላይ ነበር፤ ንጽጽራቸውም የፖሊቲካ ፓርቲ ኾኖ መንግሥታዊ ሥልጣን ለመያዝ ከበቃው የግብጹ ሙስሊም ወንድማቾቾች አንሥቶ ከናይጄሪያ መንግሥት ጋራ በትጥቅ የተደገፈ ፍልሚያ ውስጥ እስከገባው የሽብር ቡድን ቦኮ ሐራም ድረስ የጨከነ ነበር፡፡
ውንጀላው ከአነጋገሩ እንደሚታየው በማኅበሩ አባላት ላይ ብቻ ያነጣጠረ እንዳልኾነ የሚታየው፣ ‹‹የማኅበረ ቅዱሳን አባላት እዚህ ውስጥ አላችኹ፤ የድርጅትም አባል ናችሁ፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ ‹‹መታገል ያልቻላችኹት የማኅበሩ አባል ስለኾናችኁ ነው፤ ኹለቱን እያጣቀሳችኹ መሔድ አትችሉም፤›› ለማለት ሲደፍሩ እንደነበር ተወያዩ አስረድተዋል፡፡ ይህም ሚኒስቴሩ በሚያዝያ ወር ፳፻፮ ዓ.ም. ባወጣው ሰነድ፣ ‹‹በማኅበሩ ውስጥ የመሸጉ ግለሰቦችና ቡድኖች መኖራቸውን መጠቆም ማኅበሩን አክራሪ/ጽንፈኛ ብሎ መፈረጅ አይደለም፤ ማኅበረ ቅዱሳንም በዚኽ አልተፈረጀም፤›› በማለት የሰፈረውን ማብራሪያ ተቀባይነት እንደሚያሳጣው ተመልክቷል፡፡
ሚኒስትሩ ከአክራሪነት በአንጻሩ ‹‹አጥባቂነት›› ትክክለኛና ሰብአዊ መብት እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ ይኹንና ርቱዕነት፣ ቀናዒነት፣ ጽንዓት፣ ታማኝነት እና ትጉህነት እንጂ ‘አጥባቂ’ የሚባል ሃይማኖታዊ ቅጽል እንደማይስማማቸው፤ ልዝብነት ይኹን አጥባቂነት በቤታቸውም ይኹን በመጽሐፋቸው እንደሌለና እንደማይቀበሉትም ተወያዮቹ በግልጽ ይናገራሉ፡፡ በሚኒስትሩ አነጋገር ከትምክህት ርእዮት ጋራ በመዳበል ይታያሉ ያሏቸው የአክራሪነት አስተሳሰቦችም÷
የራስን እምነት በሌላው ላይ መጋት፤
የትምህርት ሥርዐቱን መረበሽ፤
በሃይማኖት ሽፋን ፖሊቲካዊ አቋም ማራመድ፤
የበላይነትን አጥተናልና ይህንኑ መመለስ ይገባናል፤
ቅዱሳት መጻሕፍትን እንደሚመች እየጠቀሱ መተርጎም እና
የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እኒኽ አመለካከቶችና ድርጊቶች ግና የራሳቸውን አሳልፈው መስጠት ለማይወዱት፣ የሌላውንም ለማይሹት ኦርቶዶክሳውያን ጠባይ የማይስማሙ፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ከተፈቀደውና ከታወጀው የማኅበረ ቅዱሳን ዓላማና ተልእኮ እንዲኹም ከእያንዳንዱ አባላቱ አስተሳሰብ አንፃርም ቢኾን ተቀባይነት የሌላቸው ከንቱ ውንጀላዎች ተደርገው ነው የተወሰዱት፡፡
በዚኹ ዐይን፣ በዩኒቨርስቲዎች የሚነሡ ሃይማኖት ነክ ጥያቄዎች ስለምን በወጣው የአምልኮ የአለባበስና የአመጋገብ መመሪያ መሠረት እንደማይስተናገዱ ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ‹‹በትምህርት በተቋማቱ አካባቢ ከሚገኙ የአምልኮ ተቋማት ጋራ በመነጋገር ችግሩን ማስቀረት ያስፈልጋል፤›› በሚል የሰጡት ምላሽ አፈጻጸምም ማኅበሩ ሃይማኖቱን ያወቀ፣ በምግባሩ የተጠበቀና ሀገሩን የሚረከብ መልካም ዜጋ ለማፍራት ባደራጃቸው ግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳይኖረው በትኩረት ሊጤን እንደሚገባው ያስጠንቅቃሉ፤ ግቢ ጉባኤያት፣ በሥነ ምግባር የታነጸ ዜጋና የቤተ ክርስቲያንን ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚያግዝ የአበው ተተኪ ትውልድ ማፍሪያ እንጂ ተንኰልና ክፋት በተጠናወተው አእምሮ እንደሚባለው ‹‹የአክራሪነት/ጽንፈኝነት አስቀጣይ ኃይል መመልመያ መድረክ›› አይደሉምና፡፡
‹‹መንግሥት አክራሪዎችን ለምንድን ነው መቆጣጠር ያቃተው? ለምን ርምጃ አልወሰደባቸውም? የሃይማኖት አክራሪነትን የሚያስፋፉ ድረ ገጾችንስ ለምንድን ነው ማገድ ያልቻለው?›› ለሚለው የተሳታፊዎች ጥያቄ÷ ‹‹ወደ እያንዳንዱ ሰው መዝመት አዋጭ አይደለም፤ ዋናው የአመለካከትና የአስተሳሰብ ዝንባሌን ማስተካከል ነው፤ ሐሳብን በሐሳብ የማሸነፍ ስልት ነው የምንከተለው፤›› በማለት የሰጡትን ምላሽ በአዎንታ እንደሚቀበሉት አስተያየት ሰጭዎቹ አልሸሸጉም፡፡
ነገር ግን፣ ቅዱስ ሲኖዶሱን ሳይቀር የእግራቸው መረገጫ እስከ ማድረግና በሃይማኖት ተቋማቱ ላይ የአብዮታዊ ዴሞክራሲን የበላይነት ለማስፈን እስከ መመኘት የናረ ለከት ያጣ ርእዮታዊ እና ምናልባትም ሃይማኖታዊ ጥላቻቸውን ጭምር በመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና በግንባሩ በካር ካድሬዎች ፊት ለመናገር የቀለላቸው ሚ/ር ሺፈራው፣ በቃል የሚሉትን ያኽል በመረጃና በዕውቀት ላይ ለተመሠረተ ገንቢ የሐሳብ መተጋገል ብቃቱም ፍላጎቱም አላቸው ብለው አያምኑም፡፡
ከዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር አኳያ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር በሚል ለኢንዶክትሪኔሽን የተዘጋጁት የመንግሥት ጽሑፎች ሊታረሙና በአጽንዖት ሊመረመሩ የሚገባቸውን ጉዳዮች የያዙ ቢኾንም በአጻጻፍ ደረጃ እንኳ፡-
አክራሪነትን ለመዋጋትና ከምንጩ ለማድረቅ፣ ልማታዊ ባህሎችንና ሥነ ምግባሮችን ለማጎልበት ከእምነት ድርጅቶች ጋራ በነፃነት ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ መስተጋብር ሊኖረን ይገባል፤ በዴሞክራሲያዊ አኳኋንና የማንንም ወገን ነፃነት በማይነካ መልኩ መመካከር መቻል አለብን፡፡
የሃይማኖት ተቋሞች ከሃይማኖት እኩልነት፣ ከሕዝቦች መፈቃቀድ፣ ከሠርቶ መክበር ጋራ የተያያዙ የሞራል ትምህርት ማስተማር ከቻሉ ከዚያ በላይ እንዲሔዱ ማድረግ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፤
ከእምነት ድርጅቶች በስተጀርባ አባሎቻችንን ጨምሮ ሰፊው ሕዝብ እንዳለ መገንዘብ ይገባናል፤
የሚሉ የጥንቃቄ አገላለጾችን በሚያሳዩበት ኹኔታ፣ የሚኒስትር ሺፈራው ጥናት የጎደለውና እርስ በርሱ የሚጋጭ የመድረክ አያያዝ በሰፊው አማኝ ሕዝብ ዘንድ ድርጅቱን እንዳስጠቆረው፣ በራሳቸው በሚኒስትሩም ላይ ከቅርብ የሥራ ባልደረቦቻቸው ጠንካራ ጥያቄ እንዳስነሣባቸውና በበላይ አለቆቻቸው ሳይቀር ክፉኛ እንዳስገመገማቸው መረጃው እንዳላቸው የስብሰባው ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
በሴኩላሪዝም ሰበብ…
በታሪክ የአንድ ሃይማኖት መሠረታዊነት (hegemonic religion) በነበራቸው አገሮች የሚመሠረቱ ሴኩላር መንግሥታት ከሃይማኖት ተቋማት ጋራ ስለሚኖራቸው ግንኙነትና ስለሚከተሉት ሴኩላሪዝም “Secularism and State Policies towards Religion: The United States, France, and Turkey” በተሰኘው መጽሐፋቸው የተነተኑት የሳንዴያጎው ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር አኸመት ኩሩ፣ ከቀደሙት አገዛዞች ተጠቅሟል በሚባለው ነባር ሃይማኖት ላይ ጥላቻን ለማስፈን፣ አገራዊ ሚናውን ለመቀነስ ብሎም ከሕዝቡ ሕይወት ጨርሶ ለማጥፋትና በሴኩላሪዝም የበላይነት (the dominance of assertive secularism) ለመተካት መርሖውን በመሣርያነት የሚጠቀሙ ከልኩ ያለፉ ጠርዘኛ ዓለማዊ ኃይሎች (ultra-secularist circles) አይለው እንደሚታዩ የፈረንሳይንና የቱርክን ልምዶች በመጥቀስ አስረድተዋል፡፡
ከዚኽ በመነሣት ከኢትዮጵያ ታሪክና ወቅታዊ ኹኔታ እንዲኹም ከሃይማኖትና መንግሥት መለያየት ጋራ በተገናኘ፣ በአንዳንድ ሰሞናዊ የፖሊሲና ስትራተጂ ሥልጠና መድረኮች በጥንታዊት፣ ሐዋርያዊትና ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚሰነዘሩ ጽርፈቶች እምብዛም ባያስደንቁም ብዙኃኑን የሥልጠና ተሳታፊዎች ማሳዘናቸው እና በመድረኮቹ ዓላማና ግብ ላይም የብዙኃኑን ኦርቶዶክሳዊ ጥርጣሬ ማስነሣታቸው አልቀረም፡፡
የጽርፈቶቹ መግፍኤ፣ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በመጽሐፋቸው ስለ ቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ሥሪት በውል እንዳስቀመጡት÷ ስሙ እንጂ ጥቅሙ የሌላ በነበረውና ለሕዝቡም ግልጥ ባልተደረገው ‘ሲሶ መንግሥት አላት’ አነጋገር ቤተ ክርስቲያናችን የንግድ ምልክት ኾና ለዘመናት ስትገፋ የኖረችበት ሥሪት አገሪቱንም ቤተ ክርስቲያኒቱንም የጎዳበትን አሠራር በውል አለመረዳት ብቻ አይደለም፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በርስተ ጉልት የአድባራት አስተዳደር ካህናቷ ቶፋ በሚል ስመ ጽዕለት የነገሥታቱና የመሳፍንቱ ድርጎኛ ኾነው የአገልግሎታቸውን ዋጋ ያላገኙበት መኾኑን ያለመገንዘብ ብቻም አይደለም፡፡ በስመ ሴኩላሪዝም በአይዲዮሎጂ ላይ የተመረኮዘ ቤተ ክርስቲያናችንን የማጥላላትና ከሕዝቡ ነጥሎ የማዳከም ዝንባሌና የተግባር ውጣኔ እንጂ!
ጊዜ ተገኘ ተብሎ፣ ቤተ ክርስቲያናችን ከእርሷ በኋላ ለመጡ እምነቶች በሰላም አብሮ መኖር አንዳችም ሚና እንደሌላት ያኽል ‹‹መውጫ መግቢያ እንዳሳጣቻቸው››፤ አእላፍ ቅዱሳኗ በአራቱም የአገሪቱ ማእዝናት በሐዋርያዊ ትጋት አስተምረው ክርስትናን እንዳላስፋፉ ኹሉ ኦርቶዶክሳዊነት ‹‹በመንግሥት ሥልጣን ተደግፎ በሌሎች እምነቶች ላይ የተጫነ›› እንደኾነ፤ ከሐዋርያት ዘመን አንሥቶ የሚቆጠረው ታሪኳ ‹‹ረዥም ነው›› ማለታችንም ዕብለት እና የአክራሪነት/ጽንፈኝነት ዝንባሌ እንደኾነ፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያበረከተቻቸውን የሥልጣኔ ስጦታዎች ሳይጨምር ትውልዱ ጀግንነትን፤ አገር ወዳድነትን፤ ለታሪክ፣ ለባህልና ለሃይማኖት ተቆርቋሪነትን ይዞ እንዲያድግ ማስተማሯንና ማበረታታቷን ከትምክህት ርእዮትና በዚኹ ርእዮት ላይ ይመሠረታል ከሚባለው አሸባሪነት ጋራ በማጃመል ከአገዛዞቹ ስሕተት ጋራ ተደርባና ተዳብላ እንደምትታይ፤…አፍ እንዳመጣ መለፈፍ በርግጥም በስመ ሴኩላሪዝም በአይዲዮሎጂ ላይ የተመረኮዘ የማጥላላትና ከሕዝቡ ነጥሎ የማዳከም ዝንባሌና የተግባር ውጣኔ እንጂ ሌላ ሊኾን አይችልም! ጥቂት በማይባሉ ወገኖች አረዳድም ዝንባሌውና የተግባር ውጣኔው መንግሥታዊ ሥልጣንን ተጥቅሞ ፕሮቴስታንታዊነትን በማንገሥ የራስን እምነት የበላይነት የማስፈን አካሔድ እንደኾነ በስፋት ከታመነበት ውሎ ያደረ ጉዳይ ኾኗል!!
maeteb
ሚኒስትር ሺፈራው፣ ‹‹በሃይማኖት ሽፋን የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ለመቆጣጠር›› በሚል በሃይማኖት ተቋማቱ ላይ በምዝገባ መመሪያ በተደገፈ ጥብቅ ቁጥጥር ርእዮተ ዓለማዊ የበላይነትን ማስፈን የሚኒስቴራቸው ቁልፍ ሥራ እንደሚኾን፣ በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የግንባሩ በካር ካድሬዎች ፊት እንደተናገሩ የቀድሞው ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኤርሚያስ ለገሰ በቅርቡ ባወጡት መጽሐፋቸው ያሰፈሩት ርግጥ ከኾነም መግፍኤው ከዚኽ ተለይቶ የሚታይ አይኾንም፡፡
ደጉ ነገር፣ የቤተ ክርስቲያናችን ከፍተኛ አመራር የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ በጥቅምት ፳፩ ቀን ፳፻፮ ዓ.ም. ውሳኔው፣ በእነሚኒስትር ሺፈራው ሥልጠና ከትምክህት ርእዮትና ከአገዛዞች ስሕተት ጋራ ተዳብለን የተፈረጅንበት÷ የታሪካዊነታችንና የቀዳሚነታችን ጥሬ ሐቅ ኹሉም ሰው ሊጽፍበት የሚገባ እንደኾነ፤ ይኽን በመፃረር የሚነገረውና የሚጻፈው ኹሉ ደግሞ ‹‹እውነት ያልኾነና አስመሳይነት እንደኾነ›› በግልጽ ማስቀመጡ ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ እውነት ያልኾነው፣ በማስመሰል የሚነገረውና የሚጻፈው ታርሞና ተስተካክሎ እውነተኛውና ትክክለኛው ለሕዝብ፣ ለትውልደ ትውልድ መተላለፍ እንደሚገባው ምልዓተ ጉባኤው ጽኑ አቋም መያዙ ነው፡፡ ይህም እንዲፈጸም የሊቃውንት ጉባኤ፣ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊነትና ታሪካዊነት በጽሑፍ አብራርቶ፣ አስፍቶና አጉልቶ እንዲያቀርብ ቀን ቆርጦ መመሪያ መስጠቱ ነው፡፡ የአፈጻጸሙን ነገር አደራ እንጂ!
የሴኩላሪዝም መርሖ ምርጫ
ከአጠቃላይ ሕዝቡ ከ97 በመቶ ያላነሰው የአንዱ ወይም የሌላው እምነት ተከታይ በኾነባት አገራችን ከሃይማኖትና ሃይማኖተኝነት ጋራ የሚጫረቱ የሴኩላሪዝም ፈርጆች በጤናማ መርሖው ላይ የሰፊውን አማኝ ግንዛቤ በማዛባት ፍጥጫን እንዳያስከትሉ ጥንቃቄ እንደሚያሻው አስተያየት ሰጭዎቹ ያሳስባሉ፡፡
መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ እንደኾኑ የተደነገገበት ሕገ መንግሥታዊ አንቀጽ÷ አንዳቸው ከሌላቸው አሉታዊ ተጽዕኖ ተጠብቀው በየራሳቸው የሚጠናከሩበትንና እንዳስፈላጊነቱም የሚተባበሩበትን (the government and religion should not unduly influence each other) እንጂ ሃይማኖትና ሃይማኖተኝነት ከግለሰቡና ከሕዝቡ ሕይወት ጨርሶ የሚጠፋበት የሴኩላር አክራሪነት (secularist fundamentalism) አልያም መርሖውን መሣርያ አድርጎ ጥንታዊውን ሃይማኖትና ተቋማቱን በማዳከም ‹‹ሌላ ገጽታ ያለው የተዛባ የሃይማኖቶች ግንኙነት መፍጠር›› የሚደገፍበት እንዳልኾነ ይታመናል፡፡
በዚኽ ረገድ ከአጠቃላይ ሕዝባቸው የኖሩ ሃይማኖት ተከል – የማንነት ዕሴቶች ጋራ ያልተገናዘበ፣ ግልጽነት የጎደለው ኢ-ፍትሐዊና የማሰነ (unjust and corrupt) የሴኩላሪዝም መርሖ ማራመዳቸው ከስማዊ ልማትና የይስሙላ የሰላም ኹኔታቸው ጋራ ተደማምሮ በእርስ በርስ ግጭትና እምነት ወለድ ሽብር ዋጋ እየከፈሉ ካሉት እንደ ናይጄሪያና ሕንድ ካሉ አገሮች ትምህርት መውሰድ ይገባል፡፡
በፈረንሳይ ነበር-ካቶሊካዊነት እና በቱርክ ነበር-እስላማዊነት ላይ የገነገነው ሴኩላሪዝም (assertive secularist policies) በድጋፍና ተቃውሞ ባስከተለው ፖሊቲካዊና ማኅበራዊ ባላንጣነት ሳቢያ አገሮቹ ከኖሩባቸው ዕሴቶች ጋራ ተራርቆ ሊራመድ ወደሚችለው መርሖ (passive secularism) የመሸጋገር ርምጃዎች እያሳዩ እንደኾነ የሳንዴያጎው ዩኒቨርስቲ ምሁር ይገልጻሉ፡፡ አዎ! በሴኩላሪዝሙ ሃይማኖትና መንግሥት ተነጣጥለዋል፡፡ መንግሥት በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አይገባም፡፡ ሃይማኖትም በመንግሥት አስተዳደር ጉዳይ እጁን አያስገባም፡፡ እዚኽ ላይ ግልጽና የሠመረ ምላሽ የሚሻው ጥያቄ ግን መለያየቱና መነጣጠሉ እንዴትና በምን ደረጃ (the levels of the exclusion) ይኹን ነው፤ ይላሉ ምሁሩ፡፡
ሴኩላር ነው የሚባለው የአገራችን ሕገ መንግሥት ከሃይማኖት ጋራ ለተገናኙ ጉዳዮች የያዛቸው መሠረታዊ መርሖዎች÷ የእምነት ነፃነት እና እኩልነት ሕገ መንግሥታዊ ዋስትና እንዳገኘ እንዲኹም መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ መኾናቸውን የሚደነግጉ ናቸው፡፡
ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ በፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ሲባረኩዜጎች የእምነት ነፃነት ተጎናጽፈዋል ሲባል የሚያምኑበትን ነገር በግልና በቡድን የመግለጽ፣ የማስተማርና የመተግበር መብቶችን ያካትታል፤ የአምልኮአቸውን አስተምህሮና አተገባበር ተቋማዊ መዋቅር በመዘርጋት የማደራጀት፣ የማስተዳደርና የማስፋፋት መብታቸው የተረጋገጠ ነው፤ የሕዝብ ደኅንነትና ሰላም፣ ጤናንና ትምህርት፣ የሞራል ኹኔታ፣ የሌሎችን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች የማይጋፉና የማይጎዱ እስከኾኑ ድረስ በኃይልና በሌላ መልኩ ሊገደብ አይችልም፡፡
ከዚኽ አኳያ ቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያዊ ተልእኮዋን ለማጠናከርና አስተምህሮዋን ለትውልድ ለማስተላለፍ የምእመኗን አቅም በማስተባበር ባቋቋመቻቸው የቴዎሎጂ ኮሌጆች ገብተው እንጀራዋን እየበሉ የሌላ እምነትና ባህል ለማስረግ ሲሞክሩ በማስረጃ በተረጋገጠባቸው ላይ ርምጃ እንዳትወስድ ጸጥታዊ ጫና ለመፍጠር፣ ከዚኽም አልፎ መምህራኑን ‹‹መናፍቅ አትበሉ፤ መናፍቃን እያላችኹ አታስተምሩ፤ አክራሪነትና ኋላቀርነት ነው›› ብሎ መመሪያ ለማውረድ የሚሞክሩ ግለሰብ ባለሥልጣናት በሕገ መንግሥታዊ መርሖው መሠረት በሕግ የሚያስጠይቅ የጣልቃ ገብነት ተግባር እየፈጸሙ መኾኑ ሊስተዋል ያስፈልጋል፡፡ በኮሌጆቻችን ለሐዋርያዊ ተልእኳችን የምንፈልጋቸውን ምሁራን በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሯችን ብቻ የማሠልጠንና የአፈጻጸሙን አግባብነት የመቆጣጠር መብቱ የእኛው ነውና፡፡
ሃይማኖት በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ መግባቱ እምነቶችን የበላይና የበታች በማድረግ የዴሞክራሲን መሠረት መናድና ደብዛውን ማጥፋት እንደኾነ ከተገለጸ፣ በተመሳሳይ አኳኋን በአንዳንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትም ተማሪው – ምእመን በግሉ በሚፈጽመው ሥርዐተ እምነት ውስጥ ጥቂት ሓላፊዎች በራሳቸው አካሔድ ጣልቃ ሲገቡ የሚወስኑበት ኹኔታ፣ ከተማሪው – ምእመን ሃይማኖታዊ መርሕ ጋራ የሚጋጭና የአንዱ ሃይማኖታዊ ትምህርትና ሥርዐት በሌላው ጫናው ውስጥ እንዲወድቅ የሚፈቅድ በመኾኑ የእምነት ነፃነታችን የሚሸራረፍበት አሠራር አስቸኳይ እርማት ሊደረግበት ይገባል፡፡
በተከታታይ ዘገባዎች እንደታየው፣ በጅማ ዩኒቨርስቲ አራቱም ካምፓሶች ባለፉት ሦስት ዓመታት በአጽዋማት ወቅት የምግብ ቤት አገልግሎቱ በሙስሊም እና በኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች መካከል የመስተንግዶ ልዩነት የሚታይበት መንሥኤ ምንድን ነው? ቤተ ክርስቲያናችን፣ ምእመናን ኹሉ ሰባት የዐዋጅ አጽዋማትን እንዲጾሙ ባዘዘችበት ኹኔታ ‹‹ኹለት አጽዋማትን ብቻ ነው የምናጾማችኹ፤ ሌላውን የማጾም ግዴታ የለብንም፤ የሐዋርያት ጾም የሚባል የምናውቀው የለም፤›› የሚለው የተማሪዎች ዲኑ ውሳኔ በየትኛው አሠራር የተደገፈ ይኾን? ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች የተመደበላቸውን በጀት በነፍስ ወከፍ ተጠቅመው ሥርዐተ አጽዋምን በየራሳቸው ማለትም በግላቸው ቢፈጽሙ በመንግሥት ጽሑፎች ከተገለጹልን የሴኩላሪዝም መርሖዎች የትኛውን ይጥሱ ይኾን?
የመንግሥትና የሕዝብ የትምህርት ተቋማት ከሃይማኖታዊ ትምህርትና ሥርዐት ተጽዕኖ ነፃ መኾናቸውን ለማረጋገጥ፣ አክራሪነትንና ጽንፈኝነትን የማስፋፋት ዕድል ለመገደብ በሚል የተቀመጠው ክልከላ በጥቅሉ የሚለው፣ ‹‹በትምህርት ተቋማት ውስጥ በቡድን መጸለይ፣ በቡድን መስበክ፣ በቡድን መዘመር፣ በቡድን መስገድ፣ በሃይማኖት አለባበስ ሽፋን ማንነትን ለመለየት የማያስችል አለባበስ የተከለከለ ነው፤›› ኾኖ ሳለ የዩኒቨርስቲው የተማሪዎች ዲን ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎችን ለይተው ከትምህርት ገበታቸው እስከማሳገድ ድረስ የሚበድሉበት ‹የሴኔት ሕግና ፕሪንስፕል› ምን ይኾን? የጅማ ዩኒቨርስቲው አድልዎ ዐደባባይ መውጣቱን ተከትሎ በሌሎቹ ተቋማትም በኦርቶዶክሳውያንና በሥርዐተ እምነታቸው ላይ ያነጣጠሩ የሃይማኖታዊ መልካም አስተዳደር በደሎች እየተፈጸሙ ስለመኾኑ የሚያመላክቱ መረጃዎችና ሪፖርቶች እየወጡ ነው፡፡
የሴኩላሪዝማችን መርሖ÷ ‹‹የአስተሳሰብ ግልጽነትና የአፈጻጸም ወጥነት የጎደለው (vacuous secularism) ነው፤›› በሚል የሚተቸውና በሰበቡም አንዳንድ ባለሥልጣናት በጥንታዊት፣ ብሔራዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ ርእዮታዊና ሃይማኖታዊ ጥላቻቸውን ለማስፋፋት፣ በፖሊሲዎችና በመዋቅራዊ አሠራሮች ተቋሞቿንና የተከታዮቿን ሃይማኖተኝነት ለማዳከምና ከተከታዮቿ ለመነጠል በመሣርያነት ይጠቀሙበታል፤ የምንለው እንዲኽ ባሉትና በመሰሏቸው ማሳያዎች አስረጅነት እንደኾነ ቢታወቅ መልካም ነው፡፡
ማዕተባችንን እናጠብቃለን፤ ግዴታችንም እንወጣለን
ማዕተብ ከክርስቲያንነት መለዮነቱ (በአእምሮ ወንድማገኘኹ “The Ethiopian Orthodox Church” መጽሐፍ አገላለጽ ‘’badge of Christianity’’) አልፎ ማንነት እና ባህል እንደኾነ የሚኒስትር ሺፈራውን ‹‹ማተቡም ቢኾን የጊዜ ጉዳይ ነው፤ መውለቁ አይቀርም›› ማሳሰቢያን ተቃውመው አስተያየት የሰጡ የሥልጠናው ተሳታፊ ገልጸዋል፡፡
ማዕተብ ባህል ኾነ ሲባል በአባባል፣ በአነጋገር፣ በልማድ፣ በሕግ፣ በሥርዐት የእምነትና ክሕደት፣ የፍርድና ውሳኔ መግለጫነቱን ያሳያል፡፡ ማተበ ቢስ ማለት ማተቡን የማያስር ብቻ ሳይኾን ማተብ እያለው ሕገ ወጥ ሥራ የሚሠራ ሰው ማለት ነው፡፡ ማተብ የለሽ በአንገቱ ክር የሌለ፣ በሓላፊነቱ ያልታመነ ሰው ነው፡፡ ማተቡ ተያዘ ማለት የማይገባ ሥራ ስለሠራ ከክርስቲያን ተለየ ማለት ነው፡፡ ማተቡን በጠሰ ማለትም ክርስትናው ካደ ማለት ነው፡፡
በዚኽ ደረጃ ከእምነታችንና ማንነታችን ጋራ የተዋሐደ ይትበሃላችንን በመፃጉዕ አስተሳሰብና ተግባር ለማክሰም ከመጣጣር ይልቅ ሴኩላሪዝማችንን ቢያውደውኮ መርሖውን የፖሊቲካዊና ማኅበራዊ ባላንጣነት መንሥኤ ሳይኾን ሙሉዓ ዕሴት (value-laden) የኾነ የሰላምና የብሩህ ተስፋ ምንጭ ያደርገዋል፤ ሃይማኖት እና አዎንታዊው ሴኩላሪዝም ለሚጋሯቸው የነገረ ሰብእ እና ሞራላዊ ዕሴቶች ማበብም (development of humanistic and moral values) የበኩሉን ሚና ይጫወታል፡፡ ልማታዊነት የምንለው የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዕድገትስ ቢኾን በሃይማኖተኝነትና ሞራላዊ ሥሡነት ካልታረቀ መጨረሻው ምን እንደሚኾን ከኹላችን የተሰወረ ነውን?
የመንግሥት መካከለኛ አመራሮች ‹‹ሞተር ኃይል እና ቁልፍ ሚና ይዘው የሚንቀሳቀሱ›› እንደኾኑ በሥልጠናው መዝጊያ ላይ ከመገለጹ አንፃር፣ በዚኽ ደረጃ በሚገኘው አካል ዘንድ ‹‹ማተቡም ቢኾን የጊዜ ጉዳይ ነው፤ መውለቁ አይቀርም›› ዐይነት እምነትንና ማንነትን በቀጥታ የሚፃረር ድፍረት፣ ከአነጋገር ማዳጥ የተፈጠረ ‹‹የግለሰብ የአፈጻጸም ጉድለት›› ተብሎ ይታለፋል ወይስ በሴኩላሪዝሙ መርሖና በፖሊሲው የታዘለ ‹‹ሥርዐታዊ ጥሰት›› ተደርጎ ይወሰዳል!?
ክርስትናችን ‘የቄሣርን ለቄሣር የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ስጥ’ የሚል ሴኩላሪዝምን በአዎንታዊነትና በቀላሉ የሚገልጽ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ ያለው እንደኾነ የሥልጠናው ተካፋዮች ይገልጻሉ፡፡ የአገራችን የሴኩላሪዝም መርሖም ምእመኑን ለእምነቱ ለዘብተኛ በማድረግ በሒደት ወደ ሃይማኖት አልባነት የመምራት ተንኰል የተሸሸገበት ከሚያሰኝ አቀራረብ ሊጠበቅ እንደሚገባው ይመክራሉ፡፡
ክርስቲያንነታችንን በየራሳችን የምንመሰክርበት መለዮአችን ማዕተብ ለመንግሥት ሴኩላርነት ተፃራሪ እንደኾነና ሊከለከል እንደሚችል መናገር፣ የመንግሥትን የሴኩላሪዝም መርሖ በማማሰንና የተሳሳተ መልእክት በማስተላለፍ ሰፊውን አማኝ ፀረ – ሴኩላር የሚያደርግ፣ ሕዝቡንና መንግሥትንም ፊት ለፊት የሚያፋጥጥ እንዳይኾንም የሚኒስትር ሺፈራው አነጋገርና ጠቅላላ አካሔድ እርምትና ማስተካከያ ሊደረግበት እንደሚገባ ያስጠነቅቃሉ፡፡

No comments:

Post a Comment