Thursday 9 October 2014

ከመላው የኢትዮጵያ ዩኒቨርስቲዎች የታሰሩ ሙስሊም ተማሪዎች የጥፋተኝነት ውሳኔ ተሰጠባቸው!

እነ ፈትህያ ጥቅምት 4/2007 የቅጣት ውሳኔ ይተላለፍባቸዋል!
ማክሰኞ መስከረም 27/2007፡ ከጥር 2005 ጀምሮ ከሚማሩባቸው የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች ታፍሰው በእስር ላይ የሚገኙት ሙስሊም ተማሪዎች የጥፋተኛት ውሳኔ በፍርድ ቤቱ ተሰጠባቸው፡፡ በእነ እስማኤል ኑርሑሴን መዝገብ የተከሰሱትና ‹‹በመላው አገሪቱ አመጽ ለማስነሳትና በመንግስት የወጣውን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአለባበስ ደንብ በመቃወም ህገ ወጥ ተግባር ሊፈጽሙ ሲሉ›› በሚሉና በሌሎችም የፈጠራ ክሶች ከ18 ወራት በላይ በእስር የቆዩት ተማሪዎች ጥፋተኛ መባላቸው ከፍተኛ ቁጣ ፈጥሯል፡፡ እነዚህ በግንቦት 2005 ክስ የተመሰረተባቸው ተማሪዎች አብዛኞቹ እድሜያቸው በሃያዎቹ መጀመሪያ ላይ የሚገኝ ሲሆን በመንግስት ኃይሎች ታፍነው ሲወሰዱም የዩኒቨርሲቲ
ትምህርታቸውን ለማጠናቀቅ ጥቂት ጊዜያት ብቻ ይቀራቸው ነበር፡፡
በእስራቸውም ወቅት ከፍተኛ ቶርቸር እንደተፈጸመባቸው መግለጻቸው ይታወሳል፡፡ በተማሪዎቹ ላይ መንግሰት ክስ መስርቶ ራሱ በሚዘውረው ችሎት ጉዳያቸው ሲታዩ የቆዩት ተማሪዎች ውሳኔ ለመስማት በርካታ ቀጠሮዎችን ያሳለፉ ሲሆን የመጨረሻውም ቀጠሮ ለመስከረም 22/2007 ነበር፡፡ በእለቱም ችሎቱ ለትናንት ሰኞ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ቀጠሮ ተቀምጦ ነበር፡፡ ጥፋተኛ የተባሉት ተማሪዎች እስማኤል ኑር ሁሴን፣ ሰይድ ኢብራሂም፣ ሙሐመድ
ሰይድ፣ ፈትሂያ ሙሐመድ፣ ኑርዬ ቃሲም፣ ያሲን ፈያሞ፣ መሃመድ አሚን፣ ዩሱፍ ከድር፣ ጣሂር መሃመድ፣ መሃመድ ሰይድ፣ አብደላ መሃመድ፣ አብዲ ሙሐመድ እና ኢብራሂም ዩሱፍ ናቸው። ከተከሳሾቹ መካከል ብቸኛ ሴት የሆነችው
የህክምና ተማሪዋ ፈትህያም በአሁኑ ሰዓት በቃሊቲ እስር ቤት ትገኛለች፡፡
ችሎቱ የቅጣት ውሳኔ ለማስተላለፍ ለጥቅምት 4/2007 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል። ተማሪዎቹ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1/ሀ፣ አንቀጽ 38/1 እንዲሁም አንቀጽ 257/ሀ ላይ በሰፈሩ ወንጀሎች መሰረት ‹‹በመላው አገሪቱ አመጽ በመቀስቀስ በሃይማኖት ሽፋን በአገሪቱ ያለውን ሰላም ማወክ›› እና ‹‹የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎቹን በኃይል ለማስፈታት በመጣር›› የሚሉ ክሶች ተመስርተውባቸው ክሳቸው በልደታ ፍርድ ቤት ከ18 ወራት በላይ ሲታይ
ቢዘልቅም በተለያዩ ሰበብ አስባቦች ምክንያት ሂደቱ ሳይጠናቀቅ ቆይቷል፡፡
በችሎቱ መጓተት ምክንያትም ተማሪዎቹ ጥፋተኛ ሆነው ቢገኙ ክሳቸው ከሚያስፈርድባቸው በላይ በእስር እየቆዩ እንደሆነ ባለሙያዎች ሲገልጹ ነበር፡፡ ንጹሃንን ማንገላታት ህገ መንግስቱን መጣስ ነው!

ምንጭ፡ ድምፃችን ይሰማ!

No comments:

Post a Comment