Thursday 9 October 2014

ማተብ እናስወልቃለን? ሴኩላሪዝምስ ምንድን ነው?

(ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)
tigray-woman


ከአዘጋጆቹ ማሳሰቢያ፤ በዚህ ጽሁፍ ላይ የሰፈረው ሃሳብ በከፊል ወይም በሙሉ የጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣን አቋም የሚገልጽ አይደለም፡፡ እንደ ሚዲያ የማንንም ሃይማኖት በመንቀፍም ሆነ በመደገፍ አቋም አንይዝም፡፡ በዚህ ጽሁፍ ላይ የሰፈረው ሃሳብ በሙሉ የጸሃፊው ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው ነው፡፡ ጽሁፉን አስመልክቶ በጨዋነት ማስረጃዎችን በመጥቀስ ለመመለስ ለሚፈልጉ ሁሉ ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ይገልጻል፡፡

አሁን በሥልጣን ላይ የሚገኘው አገዛዝ በሲቪል ሰርቪስ ኮሌጅ ከነሐሴ 18 እስከ መስከረም 16 ድረስ 800 ለሚሆኑ የመካከለኛ አመራሮቹ የፖሊሲና ስትራቴጂ ሥልጠና በሚሰጥበት ወቅት የእስላም ሴቶች በትምህርት ተቋማትና መንግሥታዊ በሥሪያ ቤቶች ሂጃብና ኒቃባቸውን እንዲያወልቁ ሲጠየቁ “እኛ እንድናወልቅ የምንገደድ ከሆነ ክርስቲያኑም ማተቡን ይበጥስ” ማለታቸው በተነሣ ጊዜ አቶ ሽፈራው “ማተቡም ቢሆን የጊዜ ጉዳይ ነው እንደ የሃይማኖት መለያ እስካገለገለ ድረስ አደረጃጀታችንን ስንጨርስ ማተብም ቢሆን መውለቁ አይቀርም” በማለት የአገዛዝ ቡድኑ ከክርስቲያኖች አንገት ላይ ማተብ (ማእተብ) የማስወገድ የማስወለቅ አቅድ እንዳለውና ለዚህም አደረጃጀት እየዘረጋ መሆኑን የእብደቱን የመጨረሻ ድርጊት አስታውቋል፡፡ ጥሩ ነው! በግንባራቸው በአንገታቸው በእጃቸው የመስቀል ንቅሳት ያደረጉ እናቶቻችንንና እኅቶቻችንንስ መስቀላቸው እንዴት ተደርጎ እንዲወገድ ታስቦ ይሆን? ቆዳቸውን በመግፈፍ? አየ ምድረ መናፍቅ ለዚህም ተደርሷላ? ግድ የለም አስቀድሞም ቃሉ “ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ሆነው ይመላለሳሉና ብዙ ጊዜ ስለ እነሱ አልሏቹህ አሁንም እንኳ እያለቀስኩ እላለሁ መጨረሻቸው ጥፋት ነው ሆዳቸው አምላካቸው ነው ክብራቸው በነውራቸው ነው ሐሳባቸው ምድራዊ ነው” ፊል. 3፤18-19 ይላልና አውሬው በልጆቹ አድሮ ይሄንን ሊያደርግ እንደሆነ በሰማን ጊዜ አልደነቀንም፡፡
በዚህ አገዛዝ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ የመናፍቃን ቁጥር አለ፡፡ አገዛዙ እንደዚህ ዓይነቶችን ድርጊቶች መከወን ሲፈልግ የሚጠቀመው እነሱን ነው፡፡ እዚህ ላይ የሰንደቅ ዓላማን አዋጅ ቤተክርስቲያን አስተምህሮዋ ከሚያዛት በተጻራሪ እንዲፈጸም ማድረጋቸውን ያስታውሷል፡፡ አነዚህ ሰዎች ከመናፍቅነታቸውና መናፍቅነታቸው እንዲያደርጉ ከሚገፋፋቸው ጥፋት የተነሣ እንዲህ ዓይነቱን ጉዳይ ሲፈጽሙ በደስታና በነቃ ትኩረት ነው፡፡ እነኝህ መናፍቃን መናፍቃን ቢሆኑም ማተብ ለእኛ ለክርስቲያኖች ምን ማለት እንደሆነ፣ ምንን እንደሚወክል፣ ምን ትርጉም እንዳለውና የአገልግሎቱን አስገዳጅነት አያውቁም ማለት አይቻልም፡፡ ከዚህ የተነሣ አገዛዙም መናፍቃን የአገዛዙ ባለሥልጣናትም የተናገሩት ቃል ምን ያህል ከባድና ምድር የሚንጥ የመጨረሻ ከባድ ነገር እንደሆነ እያወቁ እየገባቸው ትንሽም እንኳን የንዝረት መጠኑ እንዲሰማቸው አልፈለጉም፡፡ በዚህ በማተብ ጉዳይ ላይ ሕዝበ ክርስቲያኑ ሊከፍል የሚችለውን ዋጋ ምንነት አለቅጥ ንቀውና አቅለው ተመልክተውታል፡፡ ለማንኛውም ለሁሉም ሰው ግልጽ ይሆንለት ዘንድ የማተብንና የሂጃብ ሊቃብን ምንነት ማየት ይኖርብናልና ዕንይ፡-
ማተብ (ማዕተብ) ፡-
ማተብ (ማዕተብ) ቃሉ ግእዝ ሲሆን ዐተበ ከሚለው ግስ የወጣ ቃል ነው፡፡ ዐተበ ማለት አማተበ ባረከ ማለት ሲሆን ማተብ (ማዕተብ) ደግሞ በጥምቀት መባረክን የእግዚአብሔርን ልጅነት ማግኘትን የሚያመለክት ቋሚ ምልክት ማለት ነው፡፡ ማተብ ለእኛ ለክርስቲያኖች የምርጫ ጉዳይ አይደለም፡፡ ወንድ ልጅ በ40 ቀኑ ሴት ልጅ በ80 ቀኗ ቤተክርስቲያን በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቃ የእግዚአብሔርን ልጅነት እንድናገኝ ካደረገችበት ቀን ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስ የሚደረግ ከሞትንም በኋላ አብሮን የሚቀበር ክርስቲያናዊ ግዴታ ያለበት በአንገት የሚታሰር ክርና መስቀል ነው፡፡ የማተብ መበጠስ ወይም መውለቅ ሃይማኖትን የመካድ ተምሳሌታዊ ትርጉም አለው፡፡ አንድ ክርስቲያን በአንድም በሌላም ምክንያት በአርባና በሰማንያ ቀን የታሰረለትን ማተቡን ያወለቀ የፈታ የተወ እንደሆነ ሃይማኖቱን ባይክድም እንኳን የመንፈስ ቅዱስ ጸጋና ጥበቃ እንደተለየው እንደሚርቀው ለተለያየ ዓይነት አጋንንታዊ ጥቃት (ለጸብአ አጋንንት) እንደተጋለጠና እንደሚጋለጥ እንደሚጠቃም ይታመናል ይታወቃልም፡፡ “ልጀ ሆይ! የአባትህን ትእዛዝ ጠብቅ የእናትህንም ሕግ አትተው ሁልግዜ በልብህ አኑረው በአንገትህም እሰረው ስትሄድ ይመራሀል፣ ስትተኛ ይጠብቅሀል፣ ስትነሣ ያነጋግርሀል፡፡ ትእዛዝ መብራት ሕግም ብርሃን ነውና” ምሳ. 6፤19-23 በነገራችን ላይ ማተብ የምናደርገው እኛ ኢትዮጵያዊያን ብቻ አይደለንም ከእኅት አብያተክርስቲያናት (Oriental Churches) ማለትም ከግብጽ፣ ከሶሪያ፣ ከሕንድ፣ ከአርመን በተጨማሪ ላቲኖችም ማተብ የማድረግ ባሕል አላቸው፡፡
አገዛዙ በዚህ ከገፋበት ክርስቲያን ነን ባዮች አባላቱ አንድ አስታራቂ ሐሳብ የሚሉትን ሊያመጡ እንደሚችሉ ይሰማኛል፡፡ “ማተብ የሚታየው አንገት ላይ በአጭሩ ወይም ጠበቅ ተደርጎ ሲታሰር ነውና ሰፊ ወይም የማይታይ ማተብ እናስራለን” የሚል፡፡ ነገር ግን ማተብ ሰፊ ወይም የማይታይ ሆኖ ከታሰረ ከማውለቅ ወይም ከመበጠስ ተለይቶ የማይታይና ማተብ እንዲታሰር ከሚደረጉበት ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች አንዱን ያሽራል፡፡ እሱም እኛ ክርስቲያኖች ማተብ የምናስርበት ምክንያት በኢየሱስ ክርስቶስ (እግዚአብሔር በሆነ በእግዚአብሔር ልጅ) ማመናችንን ለሌሎች ለሚያዩን ሁሉ ለመመስከር ወይም ክርስቲያን መሆናችንን ለሌሎች ለማረጋገጥና ክርስቲያን በመሆናችንም እንደማናፍርበት ይልቁንም እንደምንኮራበት ለማረጋገጥ ነው፡፡ ስለሆነም ማተብ በቀላሉና በሳል በሆነ መንገድ አንደበትን ከፍቶ ምንም ማለት ግድ ሳይል ይሄንን ታላቅ ምሥጢር የምንመሰክርበት ሁነኛ መንገድ ነው “ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ፤ በሰው ፊት የሚክደኝን (የሚያፍርብኝን) ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት ባለው በአባቴ ፊት እክደዋለሁ” ማቴ. 10፣32-33፡፡
ስለዚህ ክርስቲያን ነኝ የሚል ወይም በመሲሑ በኢየሱስ ክርስቶስ (በመድኃኔዓለም) አምናለሁ የሚል ማተቡን ባጭርና በግልጽ በሚታይ መልኩ ማሰር ግዴታው ነው ማለት ነው፡፡ በመሆኑም ማተብን ልንደብቅ የምንችልበት ምንም ምክንያት እንዲኖር አይፈቀድም፡፡ ማተባችንን ለሌሎች ማሳየታችንን የምናፍርበት ከሆነ በክርስቲያንነታችንም እናፍርበታለን ማለት ነው ይሄም ደግሞ እኛ እንላለን እንጅ ክርስቲያኖች አለመሆናችንን በክርስቶስም ገና አማመናችንን ያረጋግጣል፡፡ በዚህም ምክንያት ክርስቶስ በቃሉ እንዳለው በኋላ ላይ በሰማያት ባለው በአባቱ ፊት ይክደናል፡፡ እራሳቹህን ታዘቡ ክርስቶስ በሰማያት ባለው በአባቱ ፊት የሚመሰክርልን ዓይነት ክርስቲያኖች ነን ወይስ የሚክደን የሚያፍርብን?
ሂጃብ ኒቃብ፡-
ሂጃብና ኒቃብ የሚያደርጉ እስላም ሴቶች በእርግጥ ያንን አሉ የተባለውን ነገር ብለው ከሆነ በጣም በጣም መሳሳታቸውን ሊያውቁት ይገባል፡፡ በየትኛውም መመዘኛ ሊነጻጸር የማይችል የማይገባ ነገርን ለማነጻጸር በመሞከራቸው አለማወቃቸው ባመጣባቸው ስሕተት ሊያፍሩ ይገባል፡፡ በእርግጥ ሂጃብና ኒቃብ በቁርአንም ይሁን በሸሪአ ሕግ የተደነገገና የአለባበስ ሥርዓት እንደሆነ እስልምናን የሚከተሉ ይናገራሉ፡፡ ይሁን እንጅ መቸም የትም ቢሆን ከቶ የማይወልቅ ልብስ አይደለም፡፡ የሚለበሰው የእስላም ሴቶች ከቤት ወጥተው ከቤተሰብ አባል ውጭ በሆኑ ሰዎች ሊታዩ በሚችሉባቸው ቦታዎች በሴትነታቸው ሰው እንዳይፈትኑ ወይም እንዳይፈተንባቸው እንዳያሰናክሉ ወይም እንዳይሰናከሉባቸው ተብሎ ከእግር ጥፍራቸው እስከ እራስ ጠጉራቸው ድረስ ምንም የሚታይ ነገር እንዳይኖራቸው ተሸፋፍነው  እራሳቸውን ከዐይን ዕይታ እንዲሰውሩ የሚገደዱበት እስላማዊ የአለባበስ ሥርዓት ነው፡፡ ከባሎቻቸው ወይም ከቤተሰቦቻቸው ጋር እያሉ ግን ይሄንን ልብስ ስንዲያደርጉ አይገደዱም፡፡ ሲተኙም አውልቀውት ይተኛሉ ሲታጠቡም አውልቀውት ይታጠባሉ እንጅ እንደለበሱት እንዲተኙ እንደለበሱት እንዲታጠቡ አልተደነገገባቸውም፡፡
በመሆኑም ሂጃብና ኒቃብ ለመከለያነት ለመሸፈኛነት ለመደበቂያነት ለመሸሸጊያነት ከሚያገለግል ልብስነት የዘለለ ትርጉምና አገልግሎት የለውም ማለት ነው፡፡ ይሄም ሆኖ እስልምናቸው እስካዘዛቸው ጊዜ ድረስ ሊያደርጉት ይችሉ ነበር፡፡ ነገር ግን የሂጃብና የኒቃብ አለባበስ ከራስ ጸጉር እስከ እግር ጥፍር ድረስ በመሆኑና የለባሹን ማንነት ወንድ ይሁን ሴት፣ ወንጀለኛ ይሁን ሰላማዊ፣ ተፈላጊ ይሁን ነጻ ሰው፣ የውጭ ዜጋ ይሁን ሐበሻ ለመለየት የሚቻልበት ዕድል ባለመኖሩ ለአሸባሪዎች መጠቀሚያነት የሚያመች ከመሆኑ የተነሣ የሀገርንና የሕዝብን ደኅንነት ለአደጋ የሚዳርግ በመሆኑ ለጋራ ደኅንነታችን ሲባል መከልከሉ ግድ ነው፡፡ በእርግጥ በዚህች ሀገር ከወያኔ በላይ አሸባሪ ባይኖርም ወያኔ እንደሚለው እስላማዊ አሸባሪ ኢትዮጵያ ውስጥ ኖረም አልኖረ የሚጠቅመን ነገር አይደለምና ለአሸባሪዎቹ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራልና እነሱ ለእናንተም ቢሆን የሚመለሱ አይደሉምና ለእስልምና ተከታዮች ወገኖቻችን ይሄንን ጉዳይ ከዚህ አንጻር ብታዩት መልካም ነው ማለት እወዳለሁ፡፡
እናም የማተብና የሂጃብ ኒቃብ ምንነትና አገልግሎት ባጭሩ ሲታይ ይሄንን ይመስላል፡፡ ስለሆነም ማተብን በሂጃብ ኒቃብ ምንነትና አገልግሎት አንጻር ማየት ፍጹም የተሳሳነና ከድንቁርና የመነጨ ከባድ ድፍረትም ነው፡፡ አገዛዙን ይሄ ስሕተቱ ሳይውል ሳያድር ለከባድና ለማይጠቅም ጸጸት ሊዳርገው እንደሚችል አልጠራጠርም፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔርን ማታለል ይችል ይመስል ክርስቲያን ነኝ እያለ እያስመሰለ የሚኖረው ምድረ ካድሬ ወይም ደጋፊ ሁሉ ከዚህ በኋላ ወይ ወያኔን ወይ እግዚአብሔርን እንዲመርጥ መገደዱ ስለሆነ ጉዳቸው መፍላቱ ነው፡፡ ለነገሩ እንዳልኩት ሊያስመስሉ እስከቻሉና የምርጫ ጉዳይ እስካላጋጠማቸው ጊዜ ድረስ እንጅ ሃይማኖተኛ ሆነው እንኳን አይደለም፡፡ ወያኔን ሲመርጡ ዐይናቸውንም አያሹ፡፡
ሴኩላር አሥተዳደር (ከምንም እምነት ጋራ ያልወገነ ዓለማዊ አሥተዳደር)፡-
እኔን የሚገርመኝ ወያኔ በማያውቀውና ባልገባው ነገር መዘባረቁ ነው፡፡ አገዛዙ ዓለማዊ (secular) አሥተዳደር ይላል እንጅ ስለ ሴኩላሪዝም ጨርሶ ምንም የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ ዓለማዊ የመንግሥት አስተዳደር (Secular Governmental Administration) አይደለም በእኛ በሠለጠነው በምዕራቡ ዓለም እንኳን ተተግብሮ ሊታይ ያልቻለ የአሥተዳደር ሥርዓት ነው፡፡ ወያኔ ይሄንን ማገናዘብ አልቻለም፡፡ በእኔ እምነት ዓለማዊ የመንግሥት አስተዳደር (Secular Governmental Administration) ሙሉ ለሙሉ አይደለም በከፊል እንኳን ተግባራዊ ያደረገ መንግሥት በዓለም የለም፡፡ ዓለማዊ የመንግሥት አሥተዳደር ሃይማኖታዊ ሥርዓትና አገልግሎትን ለአሥተዳደር ሥርዓቱ አገልግሎት በግብዓትነት መጠቀምን አይፈቅድም፡፡ በምዕራቡ ሀገራት በግልጽ እንደምናየው የመንግሥታቶቻቸው መሪዎች ዳኞችና የሥራ ኃላፊዎች መንግሥታቶቻቸው የጣሉባቸውን የሥራ ኃላፊነት በታማኝነት እንደሚወጡ የሚያረጋግጡት በሲመት ሥነ-ሥርዓት ወቅት (Inaugural ceremony) መጽሐፍ ቅዱስን በእጃቸው ጨብጠው በሚሰጡት ቃለ መኃላ ነው፡፡ እነኝህ የምንግሥት ባለሥልጣናትና ሹማምንት ሃይማኖታዊ በዓላት በሚከበርበት ወቅትም ሁሉ በይፋ (በኦፊሴል) ወደ እምነት ቦታዎች ይሄዳሉ ለሕዝባቸውም የመልካም ምኞት መግለኛ ይሰጣሉ፡፡
አንዱ ይሄ ሲሆን ሌላው ደግሞ እነዚያ መንግሥታት አሥተዳደሬ ዓለማዊ (ሴኩላር) ነው ስለሆነም በሀገሬ ካሉ የእምነት ድርጅቶች ላንዳቸውም አልወግንም አንዱ ከሌላው በተለየ መንገድ አይስተናገድም አይታይም ብለው በመመሪያ ደረጃ ያስቀምጡ እንጅ በተግባር ግን ሁሉንም የእምነት ድርጅቶች አናሳ ብዙ፣ ክርስቲያን እስላም፣ ሂንዱ ቡድሂ ሳይሉ በእኩል ደረጃ ማስተናገድና ማገልገል የቻለ መንግሥት ወይም ሀገር በምዕራቡ ዓለም እንኳን የለም፡፡ ወደፊትም ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ በተለይ ለእስልምና ያላቸው ንቀት ሊነገር ከሚችለው በላይ ነው፡፡ እስላም የሆነ ሰው ማሰብ የሚችል አይመስላቸውም፡፡ እስልምናን እንኳን እኩል አድርገው ሊያዩትና ሊያስተናግዱት ይቅርና በተለያየ መንገድ እምነቱን ከሰብአዊነትና ከሞራል ሕግጋት አንጻር እየተነተኑ ያበሻቅጡታል፡፡ እንደነ ሳልማን ሩሽዲ ያሉ ደራስያንንም እየተጠቀሙ የእስልምናል መመሪያ ቁርአንን የመጨረሻ ያራክሳሉ ያዋርዳሉ፡፡
 ይህ ደራሲ The Satanic Verses  በሚለው መጽሐፉ ዝርዝር ውስጥ መግባት አልፈልግም እስልምናን እንዳይሆን አድርጎ አዋርዶታል፡፡ ኢራን ሳልማን ሩሽዲን በተገኘበት እንዲገደል ፈርዳበታለች ለገደለውም አምስት ሚሊዬን ዶላር እንደምትሸልም ያስታወቀች ቢሆንም እንግሊዝ ግን በልዩ ኃይል አስጠበቀችው፡፡ ምዕራባዊያን ሳልማን ሩሽዲን ኖቬል ብቻ 11 ጊዜ ሸልመውታል፡፡ የሌላ ሽልማቱማ ተቆጥሮ የሚዘለቅ አይደለም፡፡ ምእራባዊያኑ እንደሚያወሩት ሳይሆን ሴኩላሪዝም ከሽፎ እንዲህ እየታየ እንዳለው እንዲሆን የተገደዱበት ምክንያት የየሀገራቱ ታሪካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባሕላዊና ፖለቲካዊ ተጨባጭ ሁኔታዎችና አስተሳሰቦችን በዚህ በሴኩላሪዝም የአሥተዳደር ሥርዓት ጋር ማጣጣምና ማስተካከል እንዳይቻል ስላደረገ ነው፡፡
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
እንግዲህ ሁለንተናዊ አቅም አላቸው ተብሎ በሚታሰቡት በምዕራቡ ዓለም ሀገራት እንኳን ያለው ሁኔታ እንደዚህ በሆነበት ሁኔታ ወያኔ ማን ሆኖ ነው ሲባል ተሰምቶ ጨርሶ ባልገባው ነገር ላይ የሚቀባዥርብን? ያለአቅሟና ያለ ምቹ ነባራዊ ሁኔታ ተወጣጥራ ፈንድታ ለመሞት ካልሆነ በስተቀር፡፡ ወይ ደግሞ እርስ በእርሳችን የሚያተራምስ የሚያባላ የክፋት የተንኮል የሸር ጥንስስ መጠንሰሳቸው መቀመራቸው መተብተባቸው ሊሆንም ይችላል፡፡ እንጅ ወያኔ አቅሙን እያወቀ እንዲህ ዓይነቱን እብደት ይሞክረዋል ብየ አልገምትም፡፡ እንግዲህ ከገፋበትም እንተያያለን! ወንድ የሆነ መጥቶ አንገቴን ይንካ! የወያኔን ጥቅም ለማስጠበቅ የቤተክርስቲያንን የበላይ አሥተዳደር የተቆጣጠሩት ተባብረዋቸው ማተባቹህን ፍቱ በጥሱ ቢሉም እንኳን እንደሚሉም አልጠራጠርም በዚህ ጉዳይ ላይ ሀገር ሳይተራመስ ነገሩም የወያኔ መጥፊያ ሳይሆን አይቀርም፡፡
ቸሩ አምላክ መድኃኔዓለም ክርስቶስ ደንቀራ መሰናክሎቻችንን ሁሉ አንሥቶ የዚህችን ሀገርና ሕዝብ ክብር ነጻነት ሉዓላዊነት ኃያልነት ይመልስ ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን አሜን!!!
ኢትዮጵያ ከሃይማኖቷና ከእሴቷ ሁሉ ጋር በሉዓላዊ ክብር ለዘለዓለም ትኑር!!! አሜን!!!
(ፎቶ: ባለማተብ የትግራይ ሴት)

No comments:

Post a Comment