Tuesday, 6 January 2015

ወሎ ውስጥ በኦሮሞዎች ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመ ነው ተባለ

ታኀሳስ ፳፰(ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአፍሪካ ቀንድ የሰብዓዊ መብቶች ሊግ፤ ከአማራ ክልል ኦሮሚያ ዞን ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ  ታስረው ከስምንት ወራት በላይ ፍርድ ቤት ያልቀረቡ ታሳሪዎችን ስም ዝርዝር ይፋ አደረገ።
ሊጉ  የ 26  እስረኞችን ስም ዝርዝር በማያያዝ ባወጣው መግለጫ፤ ከወራት በፊት የአዲስ አበባን አዲስ ማስተር ፕላን በመቃወም ተነስቶ ከነበረው ሰላማዊ ተቃውሞ ጋር በተያያዘ  የወሎ ኦሮሞዎችን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ በሚገኙ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ እየተፈፀመ ያለው ማዋከብና እስር ሊቆም አለመቻሉን አስታውቋል።
በዚህም የተነሳ አንዳንዶች የት እንደደረሱ ባልታወቀ ሁኔታ መሰወራቸውንና በርካቶች “አጋዚ”ተብሎ በሚጠራው የኮማንዶ አባላት ጥቃት እንደፈፀመባቸው የገለጸው ሊጉ፤ እነዚህ  ታጣቂ ሀይሎች በማስተር ፕላኑ ምክንያት ከተነሳው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ እስካሁን ድረስ ዜጎችን ከየቦታው ማሰራቸውን አላቆሙም ብሏል።
የሚጠብቃቸውን እስር በመፍራት በመቶዎች የሚቆጠሩ የዩኒቨርሲቲ፣የኮሌጅና የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ  ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው አለመመለሳቸውን በመግለጫው ያወሳው ሊጉ፤ አብዛኞቹ  ለህይወታቸው አስጊ ወደሆኑ ወደ ሶማሊዩ ላንድና ወደ ፑንት ላንድ ለመሰደድ መገደዳቸውን ገልጿል።
የጥቃቱ ሰላባ ከሆኑት መካከል በአማራ ክልል የኦሮሚያ ልዩ ዞን ነዋሪ የሆኑ የወሎ ኦሮሞዎች እንደሚገኙበት የጠቆመው የሰብዓዊ መብት ሊጉ፤ ከተቃሞው ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች “የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባል ናችሁ” ተብለው ያለፍርድ ቤት ማዘዣ መታሰራቸው እና ላለፉት ስምንት ወራት  ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በወህኒ እየተሰቃዩ እንደሚገኙ አመልክቷል።
እስረኞቹ በአሁኑ ወቅት በደሴ ወህኒ ቤት እንደሚገኙ ያመለከተው የሰብዓዊ መብት ሊጉ፣ ሰብዓዊ መብታቸው እንዲጠበቅላቸውና በሚታሰሩበት ጊዜ የተወሰደባቸው የእጅ ስልካቸውና ገንዘባቸው እንዲመለስላቸው እና ያለምንም ቅድመ-ሁኔታ እንዲፈቱ  ፤ ለጋሸ ሀገሮች፣ ዓለማቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማትና አክቲቪስቶች በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ጫና ያሳድሩ ዘንድ ተማጽኗል።

No comments:

Post a Comment