Thursday, 4 February 2016

ማኅበረ ቅዱሳን ለፓትርያርኩ ምላሽ ሰጠ | መልካም ሞላ

በቅርቡ ማኅበሩን አስመልክቶ በቅዱስ ፓትሪያሪኩ የተጻፈው መመሪያ/ ደብዳቤ አሳዝኖናል የደብዳቤው ዓላማ እና ተልእኮ ምን እንደሆነ መገመት አስቸግሮናል ያለው ማኅበረ ቅዱሳን፤ የተከሰስንበት ጉዳይ መሰረት የሌለው እና እኛን የማይወክለን ነው ሲል ለቀረበበት ክስ በቁጥር ማቅሥአመ/239/02/ለ/08 በቀን 24/05/2008 ዓ/ም በተጻፈ ደብዳቤ ምላሽ ሰጥቷል፡፡
ጋዜጠኛ መልካምሰላም ሞላ
ጋዜጠኛ መልካምሰላም ሞላ

‹‹ማኅበረ ቅዱሳን ጥቅሙና ጉዳቱ በሚገባ ሳይጠና ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንጻር የሚያስከትለው የሃይማኖት እና የስርዓት ተፋልሶ ሳይፈሽ ራሱ አርቅቆ ባጸደቀው ደንብ በቅ/ሲኖዶስ የተፈቀደልኝ ህጋዊ ማኅበር ነኝ ይላል …›› ለሚለው የፓትሪያርኩ ክስ፤ ማህበሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃና መምሪያ ስር ህጋዊ በሆነ ስርዓት በቅዱስ ሲኖዶስ ሙሉ እውቅናና ፈቃድ ተዋቅሮ የሚመራበት ደንብ በመጀመሪያ በማደራጃ መምሪያው በኩል በኋላም በ1992 ዓ/ም በቅዱስ ፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት በኮሚቴ ታይቶና ተመርምሮ የጸደቀለት እንዲሁም በ1994 በቅ/ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ደረጃ ቀርቦ የታየ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት እና ሊቃነ ጳጳሳት የተሳተፉበት ለ 6 ወር የፈጀ ጥናት የተደረገበት የማኅበሩ ደንብ በምልዓተ ጉባኤው የፀደቀና ሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት የፈረሙበት መሆኑን ጠቅሰው ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ በ2004 ዓ/ም ከማኅበሩ አገልግሎት መስፋት ጋር ተያይዞ ከማደረጃ መምሪያው ጋር በነበረ አለመግባባት ለጊዜው ማኅበሩ ተጠሪነቱ ለብጹዕ ዋና ስራ አስኪያጅ እንዲሆን እና ማኅበሩን የበለጠ እንዲሰራ የሚያደርገው ደንብ ማሻሻያ እንዲያደርግ ኮሚቴ ተቋቁሞ ስራውን አጠናቆ ቢጨርስም ፓትርያርኩ በተደጋጋሚ አልቀበልም በማለታቸው መዘግየቱን በደብዳቤ ተገልጧል፡፡
abune matias
ቀደም ሲል በቅዱስ ሲኖዶስ የተሰየመው ኮሚቴን ጥናት አልቀበለም በማለት ሌላ የማኅበረ ቅዱሳን ተወካይ የሌለበት ኮሚቴ እንግዳ በሆነ መልኩ ቢያቋቁሙም ለቤተ ክርስቲያን ካለን አመኔታ አኳያ ይሁን ብለን ብንቀበልም ‹‹ በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነውን ደንብ ማርቀቅ ስራ ሆን ብሎ በማሰናከል ያለ ደንብ እየሰራ ይገኛል›› የሚለው ወቀሳ እንዳስገረመው ማኅበረ ቅዱሳን ገልጧል፡፡ ከስድስት ጊዜ በላይ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር ቀርበን ለመወያት ብንሞክርም ፍቃደኛ አልሆኑልንም ሲል ማኅበሩ ቅሬታውን በደብዳቤው አትቷል፡፡
በ2007 ዓ/ም ቅዱስ ሲኖዶስ ተሀድሶን በተመለከተ በቃለ ጉባኤው ‹‹የተሀድሶ የችግር ምንጭ ኮሌጆቹ እንደሆኑ ያመለክታል›› በማለት በኮሌጆች ውስጥ ያለው አሰራር መታየት እና መፈተሸ አለበት የሚል ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወቃል፡፡ ቢሆንም ኮሌጆቹ ላቀረቡት የሀሰት ክስ እኛ ተገኝተን ሳንጠየቅ ውሳኔ ማሳለፍዎ ቅር አሰኝቶናል፤ በበጎ ፍቃድ ቤተ ክርስቲያንን ማገልገላችን የሚያስመሰግን እንጂ የሚያስወቅስ አይደለም ብለዋል፡፡
ማኅበሩ የዓመቱን እቅድና በየስድስት ወሩ የአፈጻጸም ሪፖርት ተጠሪ ለሆነለት አካል ሲያስገባ እንደቆየ እና የገቢ እና የወጭ አሰራሩንም በመንግስት በተፈቀደላቸው የውጭ ኦዲተሮች ጭምር በየዓመቱ እያስመረመረ ሪፖርት ያቀርባል ያለው ደብዳቤው፤ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ተፈቅዶ በሚሰጣቸው ደረሰኝ መጠቀም እንደጀመረ አስረድቷል፡፡ ማኅበሩም በበጎ ፈቃድ የተመሰረተ በመሆኑ የማህበሩ የስራ ማስኬጃ በአባላቱ እንደየገቢያቸው መጠን በሚከፍሉት የአባልነት አስተዋጾ ይሸፈናል፡፡ ተጨማሪም ወጭ ሲኖርም አባላቱ አዋጥተው እንደሚሸፍኑ ቢታወቅም ‹‹ማኅበሩ በማይታወቅ ሁኔታ ገንዘብ እየሰበሰበ ለማይታወቅ አገልግሎት ያውላል›› ተብሎ መገለጹ የውሸት ውንጀላ ከመሆኑም በላይ ከአንድ ቅዱስ አባት የማይጠበቅ ተግባር ነው ሲል በደብዳቤው ተገልጧል፡፡ ማኅበሩ ገዳማት ራሳቸውን እንዲችሉ፣ የአብነት ተማሪዎች ድጋፍ አጥተው እንዳይበተኑ ለማድረግ ፕሮጀክት ቀርጾ ግልጽ እና ተጠያቂነት በሰፈነበት አሰራር ለሚመለከተው ክፍል አቅርቦ ስራ ላይ ያውላል፡፡ ስራውም በየሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳሳት የቅርብ ክትትል እንደማይለየው እየታወቀ ‹‹ከቤተ ክርስቲያን አባቶች የሚሰጠውን አመራር አይቀበልም ፤ አባቶችን ይዳፈራል›› ተብሎ መገለጹ አግባብነት አለው ብሎ እንደማያምን ማኅበሩ አስታውቋል፡፡
አብዛኛው የማኅበሩ አባላት ወጣት በመሆናቸው ተምረው መስፈርቱን እያሟሉ ክህነት እንደሚቀበሉ እና እርስዎም አሜሪካ እያሉ ክህነት መስጠትዎ አይዘነጋም ያለው ደብዳው፤ ክህነቱ የሚሰጠው በብጹዓን አባቶች በመሆኑ ቀኖና ቢጣስ እንኳን ማኅበሩ የሚጠየቅበት ምክንያት የለም ሲሉ ‹‹ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጭ በጅምላ ክህነት እያሰጠ›› በማለት የተገለጸው አግባብነት እንደሌለው አስረድተዋል፡፡
‹‹ባለፉት ሶስት አመታት እረስተውት ካልሆነ በቀር የማኅበሩ አባላት ለቤ/ን አንድነት በሚያደርጉት ከፍተኛ ተጋድሎ እንደ ገና ዳቦ ከሁሉም አቅጣጫ እሳት እየነደደባቸው የሚታገሱ መሆኑን በየጊዜው ለቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ከውጭ ሀገር በመጡ ቁጥር ይመሰክሩ ነበር፡፡ በቅርቡም አሜሪካ ሄደው በነበረ ጊዜ የተጋበዙባቸው አብያተ ክርስቲያናት እንዴት እዚያ ደረጃ እንደደረሱና ማን መስዋዕትነት እንደከፈለባቸው ፤አሁንም ቢሆን በቅዱስነትዎ ጉዞ ወቅት ማን እንዳስከበርዎ ልቦናዎ ያውቀዋል፡፡ … በሀገር ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ጉዞ ሲያደርጉ በደማቅ ሰልፍ የሚቀበሎት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበረ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲያውቁና አባቶቻቸውን እንዲያከብሩ ስላስተማራቸው መሆኑ ግልጽ ነው›› ሲል አቡነ ማትያስ ፓትሪያሪክ ከመሆናቸው በፊት ለማኅበሩ ሲያደርጉት የነበረውን እገዛ እና ቀና አስተሳሰብ በማስታወስ አሁንም ማኅበሩ ወጣቶች ላይ እየሰራ ያለውን እንቅስቃሱ ገልጦ ጽፏል፡፡
‹‹በሌለው ስልጣን የጾም አዋጅ እስከማወጅ ደርሷል ›› ለሚለው ውንጀላም ማኅበረ ቅዱሳን እስከዛሬ ያወጀው ጾም የለም ያለ ሲሆን ክሱ ‹በቤተክርስቲያን ጾም በዝቷል ካልተቀነሰ› የሚሉት ተሀድሶዎችን ሀሳብ ለምን አትደግፉም የሚል ይዘት አለው ብሏል፡፡ በተሃድሶ እምነት አራማጆች በሚያዘጋጇቸው እና በሚመሯቸው ድረ-ገፆች እና ብሎጎች ማህበሩን ጥላሸት ለመቀባት ይነሱ የነበሩ ሃሳቦች በእርስዎ ደብዳቤ ማየታችን አሳዝኖናል አስገርሞናልም፡፡ እነሱን ንቀን መልስ ሳንሰጣቸው የቆየን ቢሆንም በእርስዎ ደረጃ ይህ በመነሳቱ ለመመለስ ተገደናል ሲል የገለጠው የማኅበሩ ደብዳቤ አሁንም ተነጋግረን መፍትሄ ማምጣት የተሻለ አካሄድ መሆኑን ጠቁሟል፡፡
ማኅበሩ አጥጋቢ ስራ ሰርቷል ወይም አልሰራም፤ ስሕተቶችንም ይፈጽማል አይጽምም ብሎ መከራከር መውቀስ እና በሃሳቦም መወያየት አስፈላጊም ሲሆን መገሰጽ እየተቻለ ከአንድ ቅዱስ አባት የማይጠበቅ የሰዎችን ስሜት በሚያስቆጡ ቃላት መሸንቆጠረ በእጅጉ አሳዝኖናል ብለዋል፡፡
ስለዚህ ጉዳዩን ቅዱስ ሲኖዶስ ተመልክቶ ተወያይቶ እርምትና መፍትሄ እንዲሰጥበት እንጠይቃል በማለት የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ የሆኑት ቀሲስ ዶክተር ሰሙ ምትኩ ደብዳቤውን በፊርማቸው አረጋግጠዋል፡፡

No comments:

Post a Comment