Thursday, 4 February 2016

ማኅበረ ቅዱሳን ለፓትሪያርኩ ደብዳቤ ጻፈ | “የፓትርያርኩ መመሪያ የእውነት ጠብታ የለበትም”

§ ቅዱስ ሲኖዶስ እርምት እና አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥበት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳቱን ተማፅኗል
§ ከአስተዳደር በደል እና ከዝርፊያ የተነሣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ወቅታዊ ሁኔታ እንዳሰጋው ገልጧል
§ አግባብነቱን የጠበቀ ወቅታዊ እርምትና መተማመኛ ያለው አሠራር ተግባራዊ እንዲኾን ጠይቋል
በአዲስ አበባ ዛሬ ታትሞ የወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ እንደዘገበው:-
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ አባ ማትያስ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ ኮሌጆች በማኅበረ ቅዱሳን ላይ የማያቋርጥ ትግል እንዲያካሒዱ በደብዳቤ ላስተላለፉት ክሥ እና ወቀሳ አዘል መመሪያ ማኅበሩ የጽሑፍ ምላሽ ሰጠ።
mahibere-kidusan-logo
የማኅበሩ ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ፥ በኮሌጆቹ ውስጥ በስውር የሚካሔደው “የተሐድሶ መናፍቃን” እንቅስቃሴ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን በመጥቀስ ያቀረበውን ተከታታይ ዘገባ ተከትሎ ፓትርያርኩ ባለፈው ሳምንት ሰኞ ለቅድስት ሥላሴ፣ ለሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ እና ለቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጆች በአድራሻ በጻፉት ደብዳቤ፥ ማኅበሩ የቅዱስ ሲኖዶስን ሥልጣን በመጋፋት በቤተ ክርስቲያንና በት/ቤቶቿ ላይ የጥፋት ጣቶቹን መቀሰሩን በመግለጽ ለሕግ ተገዥ እስኪሆን ድረስ እንዲታገሉት ኮሌጆቹን አሳስበዋል።
ክሡን በግልባጭ እንኳ እንዲያውቀው አለመደረጉንና የደብዳቤው ዓላማና ተልእኮው ምን እንደሆነ ለመገመት መቸገሩን የገለጸው ማኅበረ ቅዱሳን በበኩሉ፤ ፓትርያርኩ ያስተላለፉት መመሪያ ፍጹም እውነትነት በሌለው መረጃ ላይ የተመረኮዘና ማኅበሩን የማይገልጽ እንደኾነ በመጥቀስ ዝርዝር የጽሑፍ ምላሽ ሰጥቷል። በዘገባው በተነሡት ሐሳቦችና ስለማኅበሩ አሠራር መወያየት አስፈላጊ ሲሆንም መገሠጽ እየተቻለ ሰዎችን በሚያስቆጡ ቃላት መሸንቆጥ የምእመናኑን ትዕግሥት እየተፈታተነ እንዳለ በምላሹ ተገልጧል።
ማኅበሩ፥ ጥር 24 ቀን 2008 ዓ.ም. በቁጥር ማቅሥአመ/239/02/ለ/08 ለፓትርያርኩ፣ ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት እና ለብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በአድራሻ በጻፈውና ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱና ለተለያዩ መንግሥታዊ አካላት ደግሞ በግልባጭ ባሳወቀው ደብዳቤ፤ አባታዊ መመሪያና ቡራኬ ለመቀበል፣ በሚነሡበትም ክፉ ጉዳዮች ለመወያየት በአካል በመቅረብ፣ ለስድስት ጊዜያት ደብዳቤ በመጻፍ እንዲሁም ብፁዓን አባቶችን ጨምሮ በተለያዩ አካላት በኩል ፓትርያርኩን ለማነጋገር ቢጠይቅም ጊዜ ሰጥተው ሊያወያዩት እንዳልቻሉ አውስቷል።
abune matias
በአንጻሩ ማኅበሩን በመክሰስ ለሚቀርቡ የተለያዩ አካላት ፓትርያርኩ ጊዜ እየሰጡ እንደሚያነጋግሩ የጠቀሰው ደብዳቤው፣ “ለአንድም ቀን እንኳን በተከሰስንበት ጉዳይ ቀርበን ቃላችንን እንድንሰጥ አለማድረግዎ አስደንቆናል፤” ብሏል። “የተሐድሶ እምነት አራማጆች” በሚያዘጋጇቸውና በሚመሯቸው ድረ ገጾችና ብሎጎች ማኅበሩን ለመክሰስ የሚያወጧቸው ሐሳቦች በፓትርያርኩ መመሪያም ተጠቅሰው መታየታቸው እንዳሳዘነውና እንዳስገረመው ማኅበሩ ገልጾ፣ ከሳሾች ባቀረቡት ቃል ላይ ብቻ ተመሥርቶ ፍርድ መስጠት እውነተኛውን ሕግ በምትተረጉመው ቤተ ክርስቲያናችን ፍጹም እንግዳ ሥርዓት እንደኾነ ተችቷል፤ እውነታውን ለማወቅና ለሚነሡ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት የጉዳዩን ባለቤቶች ጠርቶ ፊት ለፊት በማነጋገርና በመመካከር መፍታት እንጂ አንድ ጩኸት በተሰማ ቁጥር ደብዳቤ መጻፉ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንደማይበጅ ማኅበሩ አስገንዝቧል። (የማኅበረ ቅዱሳን ደብዳቤ ሙሉ ቃል ከዚህ በታች ተያይዟል)
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
ቁጥር ማቅሥአመ/239/02/08
ቀን 24/05/2008
ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ፣ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም፣
ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
አዲስ አበባ ፤ ኢትዮጵያ
ለብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ
በያላችሁበት
ለቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት
አዲስ አበባ ፤ ኢትዮጵያ
ጉዳዩ፡- በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ስለተጻፈና የተሳሳተ መረጃ
የያዘ ደብዳቤን ይመለከታል
ቅዱስ አባታችን ሆይ፡-
በደብዳቤ ቁጥር ል/ጽ/179/338/2008 ጥር 16 ቀን 2008 ዓ.ም ከቅዱስነትዎ የተጻፈና ለቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ ለሰዋሰወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ እና ለቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሳቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ በአድራሻ የተጻፈ፤ ማኅበረ ቅዱሳንን አስመልክቶ ፍጹም እውነትነት የሌለው መረጃ ላይ በመመርኮዝ መመሪያ ያስተላለፉ መሆኑን የሚገልጽ ደብዳቤ በተለያዩ ሚዲያዎች ተሰራጭቶ ተመልክተናል። ይህም ጉዳይ እኛን የቤተ ክርስቲያን አካል የሆንን ልጆችዎን እጅግ አሳዝኖናል። የደብዳቤው ዓላማና ተልእኮም ምን እንደሆነ ለመገመት አስቸግሮናል። ምንም እንኳ በደብዳቤው የሰፈረው ሃሳብ ፍጹም እኛን የማይገልጸን ቢሆንም ስለተከሰስንበት ጉዳይ በግልባጭ እንኳ እኛ እንድናውቀው አልተደረገም። ይሁንና እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን ካሁን ቀደም በተደጋጋሚ እንዳደረግነው እውነቱን ለማስገንዘብ አሁንም ይህንን ደብዳቤ ለመጻፍ ተገደናል።
ማኅበረ ቅዱሳን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የሰንበት ት/ቤቶች ማ/መምሪያ ስር ሕጋዊ በሆነ ሥርዓት፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ሙሉ ዕውቅናና ፈቃድ ተዋቅሮ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ እነሆ 23 ዓመታትን አሳልፏል። ማኅበሩ የሚመራበትና የሚተዳደርበት ደንብም በመጀመሪያ በማደራጃ መምሪያው በኩል በኋላም በ1992 ዓ.ም በቅዱስ ፓትርያሪኩ ልዩ ጽ/ቤት በኩል በዝርዝር የሚያጠኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚመሩት ኮሚቴ ታይቶና ተመርምሮ የጸደቀለት እንዲሁም በ1994 ዓ.ም በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ደረጃ ቀርቦ የታየ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የሚመሩት፣ የተለያዩ የቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት እና የሕግ ባለሙያዎች የተሳተፉበትና ከ6 ወራት በላይ የፈጀ ጥናት የተደረገበት የማኅበሩ መተዳደሪያ ደንብ እንደገና ታይቶና ተፈትሾ በምልዓተ ጉባኤው የጸደቀና ሁሉም ሊቃነ ጳጳሳት ፊርማቸውን ያስቀመጡበት መሆኑን ቅዱስነትዎ ጠንቅቀው ያውቁታል ብለን እናምናለን። ይህንንም ማድረጋቸው ብፁዓን አባቶቻችን ዘመኑን በመዋጀት በዘመናዊ ትምህርት የሚመረቁ ወጣቶች በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ አርቀው በማሰባቸው ነው። እውነታው ይኽ ሆኖ ሳለ በደብዳቤዎ ላይ ማኅበሩን «ጥቅሙና ጉዳቱ በሚገባ ሳይጠና ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን አንጻር የሚያስከትለው የሃይማኖትና የሥርዓት ተፋልሶ ሳይፈተሽ በአንድ ወቅት ራሱ አርቅቆና አዘጋጅቶ ባቀረበው ደምብ በቅዱስ ሲኖዶስ የተፈቀደልኝ ሕጋዊ ማኅበር ነኝ ይላል$ በማለት መግለጽዎ ለምን እንደሆነ አልገባንም። ይህ ሀሳብም ከቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔና አሠራር የተቃረነ ሆኖ አግኝተነዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በ2004 ዓ.ም የማኅበሩ አገልግሎት እየሰፋ በመሄዱ እና በወቅቱ ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ኃላፊዎች ጋር የነበረውን አለመግባባት ቅዱስ ሲኖዶስ በምልዓተ ጉባኤ ደረጃ በአጽንኦት ከተመለከተ በኋላ ለጊዜው የማኅበሩ ተጠሪነት ለብፁዕ ዋና ሥራ አሥኪያጅ እንዲሆንና ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ይቻል ዘንድ እና ማኅበሩን ከነበረበት ደረጃ የበለጠ ሊያሠራው የሚችል ደንብ እንዲኖረው በማሰብ ቅዱስ ሲኖዶስ እርስዎም በተገኙበት ጉባኤ ደንቡን የሚያሻሽል (የጉዳዩ ባለቤት የሆኑ የማኅበሩ አባላትም የተካተቱበት) ኮሚቴ መሰየሙ ይታወሳል። ይኸው ማሻሻያ ተሠርቶ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እስኪያገኝ ድረስ ግን ማኅበሩ በ1994 ዓ.ም ጸድቆ የተሰጠው መተዳደሪያ ደንብ ሕጋዊ ሆኖ እንደሚቀጥልም አጽንኦት ተሰጥቶበት መታለፉ ግልጽ ነው። ቅዱስነትዎ በመንበሩ ከተሰየሙ በኋላም ይኽው አጥኚ ኮሚቴ ሥራውን አጠናቅቆ ቢያቀርብም ቅዱስነትዎ በተደጋጋሚ አልቀበልም በማለትዎ መዘግየቱን የሚዘነጉት አይመስለንም። እንዲያውም ከዚህ አንፃር በርስዎ በኩል የቀረበ እና በየትኛውም አሠራር ቢሆን እንግዳ የሆነ ውሳኔን ማኅበሩ ይሁን ብሎ ተቀብሎታል። ይኸውም በመንግሥታትም አሠራር ቢሆን አንድ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሊሰጥ የሚደራጅን ማኅበር ሊያገለግልበት የፈለገበትን አቅጣጫና የሚመራበትን ውስጠ ደንብ ከተቋሙ ሕግ አንፃር አርቅቆ በማቅረብ በፈቃድ ሰጪው አካል ያስጸድቃል እንጂ ፈቃድ ሰጪው አካል ራሱ ሕገ ደንብ አርቅቄ ካልሰጠኹህ አይልም። ሆኖም ግን ቀደም ሲል ቅዱስ ሲኖዶስ የሰየመውና በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መሪነት ከአንድ ዓመት በላይ የደንብ ማሻሻያውን ጥናት ሲሠራ የቆየው ኮሚቴ ያዘጋጀውን ጥናት አልቀበልም ብለው እንግዳ በሆነ መልኩ አንድም የማኅበረ ቅዱሳን ተወካይ የሌለበት ሌላ አዲስ ኮሚቴ እንዲቋቋም መደረጉን ሲሰማ ማኅበሩ በይሁንታ ነው የተቀበለው። ይህንንም ያደረግንበት ምክንያት በብፁዓን አባቶቻችን ላይ ካለን አመኔታና ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ታዛዥ ከመሆናችን የተነሣ ነው። ይሁንና ቅዱስነትዎ ይህንን በአዲስ መልክ የተቋቋመውን ኮሚቴ አባላቱ እነማን እንደሆኑ እንኳ ለኛ ባላሳወቁበት ሁኔታ “በቅዱስ ሲኖዶስ የተወሰነውን የደንብ ማርቀቅ ሥራ ሆን ብሎ በማሰናከል ያለ ደንብ እየሠራ ይገኛል” በማለት በደብዳቤዎ ላይ ማስቀመጥዎ እጅግ አስገራሚ ነው።
ይህ ሁሉ ቢሆንም ማኅበረ ቅዱሳን በአባቶች ምክር፣ ጸሎት እና ድጋፍ ምንም ዓይነት የሕግም ሆነ የሥርዓት ተፋልሶ ሳያስከትል ለአባቶች እየታዘዘ አሁንም አገልግሎቱን ግልጽ በሆነ አሠራር እያከናወነ ይገኛል። ከእርስዎ ከቅዱስ አባታችንም ዘንድ ቀርበን አባታዊ ቡራኬና መመሪያ ለመቀበል፣ እንዲሁም አንዳንድ ለቤተ ክርስቲያናችን ቅን የማያስቡ ወገኖች የማኅበሩን ስም በክፉ ባነሱበት ጊዜ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ በተደጋጋሚ ከእርስዎ ጋር ለመወያየት በአካልም እየቀረብን በደብዳቤም ከስድስት ጊዜ በላይ (በቁጥር ማቅሥአመ/80/02/ለ/06 ቀን 21/1/06 ዓ.ም፣ በቁጥር ማቅሥአመ /118/02/ለ/06 ቀን 9/5/06 ዓ.ም፣ በቁጥር ማቅሥአመ/127/02/ለ/06 ቀን 25/6/06 ዓ.ም፣ በቁጥር ማቅሥአመ /138/02/ለ/06 ቀን 24/8/06 ዓ.ም፣ በቁጥር ማቅሥአመ/165/02/ለ/07 ቀን 01/02/07 ዓ.ም፣ በቁጥር ማቅሥአመ /212/02/ለ/07 ቀን 3/13/07 ዓ.ም) ለቅዱስነትዎ በቀጥታ ጽፈን መጠየቃችን ይታወሳል። ከዚህም በተጨማሪ ከብፁዓን አባቶች ጀምሮ የተለያዩ አካላትንና ግለሰቦችን ከርስዎ ጋር እንዲያወያዩን በተደጋጋሚ ጠይቀን ነበር። ነገር ግን እርስዎ ጊዜ ሰጥተው ሊያነግግሩን አልቻሉም። በአንጻሩ ማኅበሩን ከቅዱስነትዎ ዘንድ ከስሰው የሚቀርቡ የተለያዩ አካላትን ጊዜ እየሰጡ ማነጋገርዎ ብቻ ሳይሆን አንድ ቀን እንኳን በተከሰስንበት ጉዳይ ቀርበን ቃላችንን እንድንሰጥ እንኳ አለማድረግዎ አስደንቆናል። ክስ የቀረበበትን አካል አቅርበው ሳይጠይቁ ከርሱም ሳይሰሙ ከሳሾች ባቀረቡት ቃል ላይ ብቻ ተመስርቶ ፍርድ መስጠት በማንኛውም አካል ዘንድ በተለይም እውነተኛውን ሕግ በምትተረጉመው ቤተ ክርስቲያናችን ፍጹም እንግዳ የሆነ ሥርዓት ነው።
ቅዱስ አባታችን ሆይ፡-
የቤተ ክርስቲያንን ልዕልና የሚያስጠብቀው ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት 2007 ዓ.ም ባደረገው ጉባኤ ከተወያየባቸው ጉዳዮች መካከል ተሐድሶን በተመለከተ በቃለ ጉባኤው ያሰፈረው እንደሚከተለው ይነበባል “… የተሐድሶ መናፍቃን መገኛ ምንጫቸው ከየት እንደሆነ ጉባኤው በመወያየት ደቀ መዛሙርቱ ከየአኅጉረ ስብከቱ ሲላኩ ጤናማ እንደሆኑ ነገር ግን ተመርቀው ሲመለሱ ግን ከነችግራቸው ሌላ ሰው ሆነውና መስለው ይመለሳሉ። ለዚህ የችግሩ ምንጮች ኮሌጆቹ እንደሆኑ ያመለክታል። ምክንያቱም መንፈሳዊ ኮሌጆች ተልከው መናፍቃን ሆነው ሲመለሱ እያንዳንዱን ኮሌጅ ጥርጣሬ ውስጥ ያስገባዋል። ስለዚህ ሁሉም ኮሌጆች ሊፈተሹና ሊመረመሩ ይገባል …“ ካለ በኋላ ቃለ ጉባኤው የሚከተለው ውሳኔ መተላለፉን ይገልጻል። “… የመምህራን ክህሎት እና የሃይማኖታቸው ጉዳይ፣ የኮሌጆች የትምህርት ካሪኩለም አቀራረጽ፣ የመማሪያ መጻሕፍት ዝግጅት ምን እንደሚመስል ታይተውና ተፈትሸው ሊሠራባቸው ይገባል” የሚል ውሳኔ ማስተላለፉና ይህንንም የሚያጠና አንድ ኮሚቴ ማቋቋሙ ይታወቃል። ይህንን ውሳኔ ለተቋቋመው ኮሚቴ ለማሳወቅ ቅዱስነትዎ ኅዳር 4 እና 11 ቀን 2007 ዓ.ም በጻፏቸው ደብዳቤዎች ላይ “መናፍቃንና የተሐድሶ አራማጆች በቤተ ክርስቲያናችን ኮሌጆች ተምረው ስውር ዓላማቸውን በማካሄድ ሕዝበ ክርስቲያኑን በመከፋፈል ላይ ስለሚገኙ ከኮሌጆቻችን ጀምሮ … በማስረጃ የተደገፈ ጥናት እንድታቀርቡ” በሚል አጽንኦት ሰጥተው መግለጽዎ ይታወሳል። ከዚህ በተጨማሪ ባለፉት ሁለት ዓመታት በተደረጉት የሰበካ አጠቃላይ መንፈሳዊ ጉባኤ ላይ ከተለያዩ አኅጉረ ስብከት የቀረቡ ሪፖርቶችና አስተያየቶች ከየመንፈሳዊ ኮሌጆች የተመረቁ አንዳንድ መምህራን የተሐድሶ መንፈስ እያራመዱ እንዳስቸገሯቸውና የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ማወካቸውን በግልጽ ማቅረባቸው፣ እነዚህም ሀሳቦች በጉባኤዎቹ ሲቀርቡ በተሰብሳቢዎቹ ከፍተኛ ድጋፍ ሲሰጣቸው እንደነበር ይታወሳል።
የማኅበረ ቅዱሳን ሚዲያ የሆነችው ስምዐ ጽድቅ ዘኦርቶዶክስ ጋዜጣም ይህንን የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔና የአኅጉረ ስብከት ሪፖርቶች መነሻ በማድረግ ከመስከረም ወር 2008 ዓ.ም ጀምሮ በተከታታይ ንቁ በሚለው አምዷ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየቀያየረ እና በረቀቀ መልኩ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሕልውና አደጋ ውስጥ እየከተተ የመጣውን የተሐድሶ መናፍቃኑን አጠቃላይ የኅቡዕ እንቅስቃሴ የሚያሳይ ዘገባ እየሠራች መረጃ መስጠት ቀጥላለች። በተለይም በኅዳር እና በታኅሣሥ አጋማሽ እትሞቿ ተሐድሶዎች ቤተ ክርስቲያናችን በምትመካባቸው መንፈሳዊ ኮሌጆቻችን ውስጥ በስውር ምን እያደረጉ እንደሆነ እና ለነርሱም መግቢያ ቀዳዳ ሊሆኑ የሚችሉ ጉዳዮችን በማሳያነት በመጥቀስ ዘገባ ማቅረቧ እውነት ነው። ለዚህም ዘገባ የተለያዩ አካላት ያወጧቸውን ሪፖርቶች ጋዜጠኛው ወይም ጸሐፊው በመጠቀም በኮሌጆቹ አካባቢ የተሐድሶ መናፍቃንን እንቅስቃሴ የሚያመላክት የዳሰሳ ጥናት ማድረጉ ተገልጿል። በንጹሕ ስንዴ መካከል እንክርዳድ መገኘቱ ፍጹም እንግዳ ባይሆንም ቁጥሩ እየጨመረ መምጣቱ ግን አሳሳቢ መሆኑ በጽሑፉ ተዳስሷል። በሌላ መልኩ ደግሞ ቤተ ክርስቲያናችን እጅግ የምትኮራባቸው መምህራንና ሊቃውንት ከነዚሁ ኮሌጆች በብዛት መገኘታቸውን እና የየኮሌጆቹ የሥራ ኃላፊዎችም ሆኑ እውነተኞቹ ደቀ መዛሙርት ይህንን የተሐድሶዎችን እንቅስቃሴ ተረድተው ምን ዓይነት ተጋድሎ እያደረጉ መሆኑን፣ ችግሩ ግን ሰፊ ሆኖ ከዐቅማቸው በላይ እንዳይሆን የሁሉም የቤተ ክርስቲያን አካላት የነቃ ተሳትፎና ርብርብ እንደሚያስፈልግ በጋዜጣዋ በሰፊው ታትቶ ቀርቧል። ማኅበረ ቅዱሳንም ችግሩን በአጠቃላይ አሠራር ደረጃ እንዲፈታ ማድረግ ላይ ማተኮር እንጂ በቤተ ክርስቲያናችን የሚመለከተው አካል ውሳኔ ሳይሰጥባቸው አንዳንድ የችግሩ መገለጫ የሆኑ ግለሰቦችን በስም እየጠቀሱ በጋዜጣ የማውጣት ዓላማ የለውም።
ሆኖም ግን ይኸው መረጃ በይፋ መውጣቱና ጉዳዩም ከቅዱስ ሲኖዶስ ጀምሮ በየደረጃው ባሉ እውነተኛ የቤተ ክርስቲያናችን አካላት ሁሉ ዘንድ ትኩረት በማግኘቱ የተደናገጡት የተሐድሶ እምነት አራማጆች የሰርጎ ገብ እንቅስቃሴያቸው እንዳይገታባቸው ማዘናጊያ መፍጠር ነበረባቸው። ለዚህም እንዲረዳቸው ማኅበረ ቅዱሳን በስምዐ ጽድቅ ዘኦርቶዶክስ ጋዜጣው “መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶቹን በጅምላ በሕፀፀ ሃይማኖት ከሰሰ” በማለት የጋዜጣዋን አንድ እትም አንጠልጥለው ከአንድ ወር በኋላ ወሬውን በአዲስ መልክ በየኮሌጆቹ አካባቢ በስፋት ማናፈስ ጀመሩ። ይህንን ወሬ የሰሙ አንዳንድ እውነተኛ ሰዎችም ሳይቀር ሙሉውን ተከታታይ ጽሑፍ ሳያነቡት ቅሬታ ተሰምቷቸው ቀርበው አነጋግረውናል ፤ አንዳንዶቹም የተወሰነውን ጥቅስ በማንሳት ለምን እንዲህ እንደተገለጸ እንድናብራራላቸው በደብዳቤ የጠየቁንም አሉ። ከእነዚህ ጋር ጥሩ ውይይት አድርገን መግባባት ላይ ደርሰናል። ነገር ግን ይህንን የተሐድሶዎቹን ድብቅ ዐላማ ያልተረዱ አካላት አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አባቶችን ጭምር በማሳሳት የዚህ የስውር እንቅስቃሴያቸው ደጋፊ እንዲሆኑ አድርገዋቸዋል። እንግዲህ በዚህ ሁኔታ ከየኮሌጆቹ ከሚማሩ ደቀ መዛሙርት መካከል በውድም ሆነ በግድ እንዲፈርሙ ተደርገው ለቅዱስነትዎ የቀረበልዎትን የቅሬታ ጥያቄ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነው ውሳኔ መሆኑ ተዘንግቶና የማኅበረ ቅዱሳን አንድ ተወካይ እንኳ ተገኝቶ ማብራሪያ እንዲሰጥ ሳይደረግ እንዲህ ዓይነት ብያኔ በርስዎ በቅዱስ አባታችን መሰጠቱ በከፍተኛ ሁኔታ አሳዝኖናል። ጥቂት የተሐድሶ እምነት አራማጆችን “በርቱ፣ ተቃውሟችሁንና ማደናገራችሁን ቀጥሉበት” የሚል የሚመስል መልእክት የያዘ ሐሳብ በቅዱስነትዎ ፊት መሰጠቱም እጅግ አስደንቆናል። እንደ እውነቱ ከሆነ በጋዜጣው ላይ የወጣው አጠቃላይ የጽሑፉ ጭብጥ ሲታይ ቅዱስ ሲኖዶስ ከወሰነው ውሳኔ የተለየ ስምዐ ጽድቅ የጻፈችው ምን አለ? በጥሞና ከታየ የቀረበውን መረጃ ወስዶ በቅዱስ ሲኖዶስ እንደገና የተቋቋመው ኮሚቴ እንዲያጠናው ማድረግ የሚገባ እንጂ ሊያስከስስም ሆነ እንዲህ ዓይነት ደብዳቤ ሊያስጽፍ የሚችል ነገር ለመኖሩ በፍጹም አልታየንም።
ቅዱስ አባታችን ሆይ፡-
የማኅበረ ቅዱሳን አደረጃጀት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎችን የመንፈሳዊ ትምህርት ሥርዓት ለመከታተል፣ አባላቱ በሙያቸውና በበጎ ፈቃዳቸው ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡትን የትሩፋት አገልግሎት ለማስተባበር ተብሎ በሀገረ ስብከትና በወረዳ ደረጃ ብቻ መዋቅር የተዘረጋለት መሆኑ ይታወቃል። በአጥቢያ ደረጃ ማኅበሩ ምንም ዓይነት ተቋማዊ አደረጃጀት እንደሌለውም የተገለጠ ነው። ይኽ አደረጃጀቱም በቅዱስ ሲኖዶስ ጸድቆ የተሰጠው መሆኑ ለሁሉም የቤተ ክርስቲያን አካላት ግልጽ ነው። ከዚህም በተጨማሪ የማኅበሩ አባላት በፍጹም ታዛዥነት ቀርበው በቤተ ክርስቲያን መዋቅር እየተመራንና ብፁዓን አበው መመሪያ እየሠጡን እንሥራ ብለው ወደ ቤተ ክርስቲያን ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት መቅረባቸው የሚያስመሰግን እንጂ የሚያስወቅስ አልነበረም።
በቤተ ክርስቲያናችን የአገልግሎት ማኅበር ሲቋቋም ማኅበረ ቅዱሳን የመጀመሪያው አይደለም። ቤተ ክርስቲያን እውቅና ሰጥታቸው የተቋቋሙ፣ የራሳቸው ጠቅላላ ጉባኤ ፣ የራሳቸው ውስጠ ደንብ ፣ የራሳቸው አመራር ያላቸው ብዙ ማኅበራት በቤተ ክርስቲያናችን ነበሩ፤ አሁንም አሉ። ሆኖም ግን በእንዲህ ዓይነት መንገድ የተቋቋሙትና የቤተ ክርስቲያን የቅርብ ክትትል ያልተለያቸው ማኅበራት ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ሲጠቅሙ እንጂ ጉዳት ሲያደርሱ ታይቶ አይታወቅም። በርግጥ ቤተ ክርስቲያን የማታውቀውና በቤተ ክርስቲያንም ሥርዓት የማይመራ ማኅበር ለቤተ ክርስቲያን ጠቃሚ ሊሆን እንደማይችል ግልጽ ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለእምነታቸው ቀናዕያን የሆኑ አንዳንድ ወጣቶች በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ተሰባስበው ሃይማኖታቸውን ለመማር መነሳሳታቸው፣ በተማሩትም ትምህርት መሠረት ስለወንጌል መስፋፋት እገዛ ማድረግና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለመስጠት መጀመራቸው እንዳሻቸው መሆን ለለመዱት ተሐድሶዎች እና ጥቅመኞች ነገሩ ስላላማራቸው ‹‹ማኅበራት በሌላ ቦታ እንጂ በቤተ ክርስቲያን አመራር ሥር መዋቀራቸው ቀኖና የጣሰ ነው›› የሚል ሀሳብ ይዘው ብቅ አሉ። ይህ አባባል እንደ እውነታ ተወስዶ በእርስዎ ደብዳቤም መጻፉ ቅር የሚያሰኝ ነው። ለቤተ ክርስቲያናቸው ቀናዒ ሆነው የድርሻቸውን ለመወጣት የሚደራጁ ማኅበራት ለአንዲት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መሳካት እስከሆነ ድረስ ማኅበረ ቅዱሳን ስለነዚህ ማኅበራት መደራጀት በጎ አመለካከት ቢኖረውም ማኅበረ ቅዱሳን ከራሱ ውጪ ለየትኛውም ማኅበር መቋቋምም ሆነ መክሰም ኃላፊነት የለበትም።
ማኅበረ ቅዱሳን ከቀድሞ ጀምሮ የዓመት ዕቅዱንና በየስድስት ወሩ ደግሞ የአፈጻጸም ሪፖርቱን ተጠሪ ለሆነለት አካል በጽሑፍ ሲያስገባ ቆይቷል። እንዲሁም የፋይናንስ (የገቢና የወጪ) አሠራሩን ዘመናዊ በሆነ መንገድ በመመዝገብ ገለልተኛ በሆኑና በመንግሥት በተፈቀደላቸው የውጭ ኦዲተሮች ጭምር በየዓመቱ እያስመረመረ ሪፖርቱን ለሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያናችን አካላት እያቀረበ መጓዙ ለማንም ግልጽ ነው። በ2007 ዓ.ም የጥቅምት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤ ላይ ለቤተ ክርስቲያን ቁጥጥር የተሻለ እንዲሆን በቤተ ክርስቲያን ሥር የተቋቋሙ ማኅበራት ሁሉ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ተፈቅዶ በሚሰጣቸው የገቢና የወጪ ደረሰኝ እንዲጠቀሙ በተወሰነው መሠረት ማኅበረ ቅዱሳን የዚህ ውሳኔ አፈጻጸም ፋና ወጊ በመሆን ይህንኑ ካርኒ አሳትሞ መጠቀም መጀመሩ ይታወቃል። ይህንኑም በያዝነው ዓመት በቀረበው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዓመታዊ ሪፖርት ላይ የቁጥጥር መምሪያውም ማረጋገጡን በግልጽ መስክሯል። ማኅበሩ የአገልግሎትና የፈቃድ ማኅበር እንደመሆኑ አባላቱ እንደየገቢያቸው መጠን የአባልነት አስተዋጽኦ ይከፍላሉ። የማኅበሩም ዋናውና ቋሚው የገቢ ምንጭ ይኸው በመሆኑ ማንኛውም የማኅበሩ የሥራ ማስኬጃ የሚሸፈነው በአባላቱ መዋጮ ነው። የማኅበሩ አመራር አባላትም አገልግሎታቸው የበጎ ፈቃድ በመሆኑ ጊዜአቸውን መስዋዕት አድርገው ከመስጠታቸው በተጨማሪ ለትራንስፖርትም ሆነ ሌሎች ወጫአቸውን ሁሉ የሚሸፍኑት ከኪሳቸው አውጥተው ነው። እንዲያውም ብዙ ጊዜ ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን ገንዘብ ሲያነስ ተጨማሪ መዋጮ እንዲያዋጡ ኃላፊነት ይኖርባቸዋል። እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ማኅበሩ በተለየ ሁኔታ ገንዘብ እየሰበሰበ ለማይታወቅ አገልግሎት ያውላል ተብሎ መገለጹ ፍጹም ከእውነት የራቀ ውንጀላ ከመሆኑም በላይ ከአንድ ቅዱስ አባት የማይጠበቅ በመሆኑ በእጅጉ ያሳዝናል።
ማኅበሩ በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ በግልጽ በተፈቀደለት መሠረት አባላቱ ሙያቸውንና ዕውቀታቸውን አስተባብረው ገዳማትን በልማት ራሳቸውን እንዲችሉና የአብነት ትምህርት ቤቶች በደጋፊ ማጣት የትምህርት አሰጣጣቸው እንዳይስተጓጎልና እንዳይበተኑ ለማድረግ ፕሮጀክት ቀርፀው ለቤተ ክርስቲያናችን አባላት ለሆኑ በጎ አድራጊዎች በማኅበሩ በኩል ያቀርባሉ። ለፕሮጅክቱ የሚሆን ገንዘብም ሲገኝ ማኅበሩ በሥራ ላይ አውሎ ለሚመለከተው አካል (ለገዳማቱ ወይም ለአብነት ትምህርት ቤቱ ኃላፊዎች) ያስረክባል። ይህም የሚፈጸመው በቅድሚያ በገዳማቱ በደብዳቤ ሲጠየቅ ወይም በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ወይም በሀገረ ስብከቱ የሥራ ኃላፊዎች ሲታዘዝ (ሲጠየቅ) ነው። የእነዚህ ፕሮጀክቶች አፈጻጸማቸውንም ሆነ የፋይናንስ አወጣጣቸውን የሚያሳየውን ሪፖርት በየጊዜው እየተዘጋጀ ገንዘቡን ላዋጡት ምእመናን (ወይም ማኅበራት) እንዲሁም ፕሮጀክቱ ለሚተገበርላቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት የሚቀርብላቸው ሲሆን ይህም በየዓመቱ በውጭ ኦዲተሮች እየተመረመረ ሪፖርቱ ለሚመለከታቸው የጠቅላይ ቤተ ክህነቱ አካላት እየቀረበ ይገኛል። በመሆኑም አገልግሎቱ የየሀገረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት የቅርብ ክትትል አይለየውም። እንግዲህ በዚህ አሠራር መጓዝ የትኛውን የቤተ ክርስቲያን ቀኖና እንደሚጥስ ለእኛ አልገባንም። እንዲሁም “ከቤተ ክርስቲያን የሚሰጠውን አመራር አይቀበልም፣ አባቶችን ይዳፈራል” ተብሎ በእርስዎ ደብዳቤ መገለጹ አግባብነት አለው ብለን አናምንም።
የማኅበሩ አባላት በአብዛኛው ወጣቶች የሆኑ የቤተ ክርስቲያናችን አማንያን ናቸው። ከነርሱ መካከልም የመንፈሳዊ አገልግሎት ዝንባሌ ያላቸው የአብነት ትምህርቱን ከትምህርታቸው ጎን ለጎን እየተማሩ፣ በየሊቃነ ጳጳሳቱ እየተፈተሹና መሥፈርቱን እያሟሉ ክህነት ይቀበላሉ። ቅዱስ አባታችን እርስዎም በአሜሪካ በነበሩ ጊዜ በዚሁ መንገድ ለአንዳንዶቹ ክህነት መስጠትዎን አይዘነጉትም። ይህ ደግሞ በሁሉም ብፁዓአን አባቶች የታወቀ ጉዳይ ሆኖ ሳለ በደብዳቤዎ ላይ “ከቀኖና ቤተ ክርስቲያን ውጪ … ለአባላቱ በጅምላ ክህነት እያሰጠ …” ብለው መግለጽዎ በምን ምክንያት እንደሆነ ግልጽ አይደለም። መቼም ክህነት የሚሰጠው በእናንተ በብፁዓን አባቶች እንጂ በሌላ አካል እንዳልሆነ ይታወቃል። ታዲያ በዚህ ጉዳይ ቀኖና ተጥሶስ ከሆነ የጣሰው ማን ነው ለማለት ነው; ምናልባት ካሁን ቀደም ብፁዓን አባቶችን ለማንቋሸሽ ሲባል አንዳንድ ሰዎች በየመድረኩ ሲናገሩት የነበረውን ድጋፍ ለመስጠት ታስቦ ካልሆነ በስተቀር ማኅበረ ቅዱሳን የሚከሰስበት አንዳች ምክንያት የለውም። ደግሞም አሁን ባለው ሁኔታ የዘመናዊውን ትምህርት መስፋፋት ተከትሎ ብዙ ብሩኅ አእምሮ ያላቸው ወጣቶች ከአብነት ትምህርቱና ከቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ አገልግሎት ተለይተው እንዳይቀሩ መሥራት የቤተ ክርስቲያናችን ድርሻ ነው። በአሁኑ ሰዓትም በርከት ያሉ የአብነት ትምህርት የተማሩና በትምህርቱም የገፉ ወጣቶች ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየገቡ በመሆኑ ገና ብዙ አብነቱን እና የአስኳላውን ትምህርት ያጣመሩ ምሁራን ቤተ ክርስቲያናችን ይኖሯታል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ይህም አርቆ ላሰበ ሰው ለቤተ ክርስቲያን አንድ ሰፊ የአገልግሎት አቅጣጫ ነው።
በውጭ ሀገር ስላለው የቤተ ክርስቲያን አገልግሎትም ምናልባት ያለፉት ሦስት ዓመታት አስረስተዎት ካልሆነ በቀር የማኅበሩ አባላት ስለቤተ ክርስቲያን አንድነት በሚያደርጉት ከፍተኛ ተጋድሎ እንደ ገና ዳቦ ከሁሉም አቅጣጫ እሳት እየነደደባቸው የሚታገሉ መሆኑን በየጊዜው ለቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ ከውጪ ሀገር በመጡ ቁጥር ይመሰክሩት የነበረ ነው። በቅርቡም በአሜሪካ ሄደው በነበረ ጊዜ የተጋበዙባቸው አብያተ ክርስቲያናት እንዴት እዚያ ደረጃ እንደደረሱና ማን መሥዋዕትነት እንደከፈለባቸው፣ አሁንም ቢሆን በቅዱስነትዎ ጉዞ ወቅት ማን እንዳስከበርዎ ልቡናዎ ያውቀዋል። ከዚህም በላይ በሀገር ውስጥ ለተለያዩ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎቶች በሚዘዋወሩበት ጊዜ በየቦታው በደመቁ ሰልፎች ተሰልፈው እየዘመሩ በማጀብ የሚቀበሉዎ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ማኅበረ ቅዱሳን ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲያውቁና አባቶቻቸውን እንዲያከብሩ ስላስተማራቸው መሆኑ ግልጽ ነው።
ቅዱስ አባታችን ሆይ፡-
በተጨማሪም በደብዳቤዎ ላይ አንዱ ዋና ወንጀል ተደርጎ የተገለጸው «በሌለው ሥልጣን የጾም አዋጅን እስከማወጅ ደርሷል” የሚል ይገኝበታል። በአጭር ቋንቋ ለመግለጽ ማኅበረ ቅዱሳን ያወጀው ጾም የለም። ጾም በቅዱስ ሲኖዶስ እንደሚታወጅም ጠንቅቆ ያውቃል፤ ያስተምራልም። ለጾም አድሉ ብላ በምታስተምር ቤተ ክርስቲያናችን ተጨማሪ ጾም ታውጃላችሁ ተብሎ የቀረበብን ክስ በቤተ ክርስቲያን ጾም በዝቷልና ካልተቀነሰ እያሉ በከንቱ የሚደክሙትን ተሐድሶዎች ሀሳብ ለምን አትደግፉም የሚል ያስመስለዋል።
በአጠቃላይ ካሁን ቀደም በተለያዩ የተሐድሶ እምነት አራማጆች በሚያዘጋጇቸውና በሚመሯቸው ድረ-ገጾችና ብሎጎች ላይ በተደጋጋሚ ማኅበረ ቅዱሳንን ለመክሰስ ሲያወጧቸው የነበሩትና አንድም የእውነት ጠብታ እንኳ የሌላቸውን ሀሳቦች በርስዎ ደብዳቤ በአጭር በአጭሩ ተጠቅሰው ማየታችን እጅግ አሳዝኖናል፤ አስገርሞናል። እነርሱ ሁል ጊዜም እውነት መናገር ልማዳቸው እንዳልሆነ በሁሉም ዘንድ ስለሚታወቅ ንቀን መልስ ሳንሰጣቸው ቆይተናል። በርስዎ ደረጃ ይህ እንደገና ሲስተጋባ ግን ዝም ማለቱ ተገቢ ስላልሆነ ነው ይህን ምላሽ ለመስጠት የተገደድነው። ይህ ለመንፈሳውያን ኮሌጆቹ በአድራሻ የተጻፈላቸው ደብዳቤም ዓላማው በእውነት ግልጽ አይደለም። ስለዚህ አሁንም ቢሆን እውነታውን ለማወቅና ለሚነሱ ችግሮች መፍትሔ ለመስጠት የጉዳዩን ባለቤቶች ጠርቶ ፊት ለፊት በማነጋገር እና በመካከር መፍታት እንጂ አንድ ጩኸት በተሰማ ቁጥር ደብዳቤ መጻፉ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚበጅ አይመስለንም። በርስዎ ስም የሚጻፉ ደብዳቤዎችም ቤተ ክርስቲያንን የሚወክሉና ክብርዋን የሚያስጠብቁ፣ በሁሉም አካላት ተአማኒነት ኖሯቸው ትኩረት ሰጥተው የሚመለከቷቸው እንዲሆኑ ቢደረግ እጅግ ደስ ይለናል።
ክቡራን ንዑዳን ብጹአን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሆይ፡-
ማኅበረ ቅዱሳን በናንተ ቡራኬና መመሪያ ሰጪነት በብዙ ገዳማውያን አባቶቻችን ጸሎት እና በምእመናን ከፍተኛ ድጋፍ ቤተ ክርስቲያንን በአገልግሎቱ ለመደገፍ ላለፉት 23 ዓመታት የዐቅሙን ያህል ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል። የነበረው አገልግሎት አልጋ በአልጋ ባይሆንም በተለይ በአሁኑ ወቅት ያለው የቤተ ክርስቲያናችን ሁኔታ እያሰጋን መጥቷል። የተሐድሶ መናፍቃኑ በማን አለብኝነት የቤተ ክርስቲያናችንን ትምህርተ ሃይማኖት እና ቀኖና በሚጻረር መልኩ የእምነት መግለጫቸውን በይፋ በመጽሐፍ መልክ አሳትመው እያሰራጩ ባሉበት ወቅት፣ ጥቅመኝነት በአንዳንድ የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ውስጥ ክብር ተሰጥቶት በይፋ ዝርፊያ በሚፈጸምበት እና አገልጋዮች ካህናት በየቦታው በሚበደሉበት በዚህ ጊዜ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ርዕሰ መንበር ደረጃ በቅዱስነታቸው እንዲህ ዓይነት ለቤተ ክርስቲያን የማይበጁ ደብዳቤዎች እየተፈረሙ ሲወጡ ማየት እጅግ ከባድ አደጋ እንዳለው ይሰማናል። ምንም እንኳ ማኅበሩን አጥጋቢ ሥራ ሠርቷል ወይም አልሠራም፣ ስሕተቶችንም ይፈጽማል አይፈጽምም ብሎ መከራከር መውቀስና በሀሳቦቹም መወያየት፣ አስፈላጊም ሲሆን መገሠጽ እየተቻለ ከአንድ ቅዱስ አባት ቀርቶ ከየትኛውም የተቋም ሓላፊ በማይጠበቁና የሰዎችን ስሜት በሚያስቆጡ ቃላት መሸንቆጥ በእጅጉ የሚያሳዝን ሆኖ ተሰምቶናል። ለአብነት ያህልም ማኅበሩን ከሳሾቹ እንኳን በማይሉት መንገድ “የቤተ ክርስቲያንን ቀኖና በመጣስ ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት እየፈጸመ ይገኛል” የሚለው ሊጠቀስ ይችላል። ይህ አገላለጽ ለማኅበሩ አመራርና አባላት ቀርቶ ደብዳቤውን በየሚዲያዎቹ ያዩት ሁሉ ትዕግሥትን የሚፈትን እንደሆነ እየገለጹልን ይገኛሉ። የጥቅምቱን ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተከትሎም ማኅበሩ የቤተ ክርስቲያናችንን ስብከተ ወንጌል ለዓለም የሚያሰራጭበት የቴሌቪዥን መርሐ ግብር ሲቋረጥ ለሚመለከተው የቤተ ክርስቲያናችን አካል ብናመለክትም በቅዱስነታቸው ደብዳቤ እንዲቆም መደረጉም ሌላው አሳዛኝ ተግባር ነው። ከዚህም በላይ በዘመናችን ባለው ቴክኖሎጂ ምክንያት የትኛውም መረጃ ወይም ጉዳይ በሚዲያ ለሕዝቡ በከፍተኛ ፍጥነት የሚዳረስ መሆኑ አይዘነጋም። ይህንም ተከትሎ ብዙ ዓይነት ስሜቶችና አጸፋዎች ከምእመናን ይደመጣሉ። በመሆኑም በወቅቱ አግባብነቱን የጠበቀ ዕርምትና ለወደፊቱም መተማመኛ ያለው አሠራር ተግባራዊ እስካልሆነ ድረስ የሚከተለው አደጋ ትልቅነት ይታየናል።
ስለዚህ ቅዱስ ሲኖዶስ በጉዳዩ ላይ በአንክሮ እንዲወያይበት እና እርምት እንዲሠጥበት ለእኛም ከዚሁ አንፃር አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠን እንድታደርጉልን ከእግረ መስቀላችሁ ሥር ወድቀን በፍጹም ትሕትና እንጠይቃለን።
የቅዱስነትዎ ቡራኬ ይድረሰን
የብፁዓን አባቶቻችን የጸሎታችሁ ረድኤት አትለየን
ግልባጭ፡-
Ø ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት
Ø ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት
Ø ለኢ.ፊ.ዲ.ሪ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር ጽ/ቤት
Ø ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፍትሕ ሚኒስቴር ጽ/ቤት
Ø ለኢ.ፌ.ዲ.ሪ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን
Ø ለብሔራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት
Ø ለውስጥ ደኅንነት ጥበቃ ዋና መምሪያ
Ø ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽ/ቤት
አዲስ አበባ
Ø ለትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ርእሰ መስተዳድር ጽ/ቤት
Ø ለትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን
Ø ለትግራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፍትሕ ቢሮ ጽ/ቤት
መቐሌ
Ø በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ለሚመሩት አህጉረ ስብከት
በያሉበት
Ø ለማኅበረ ቅዱሳን ለሁሉም ማእከላት
በያሉበት
Ø ለኦዲትና ኢንስፔክሽን አገልግሎት
Ø ለዋና ጸሐፊ ቢሮ
ማኅበረ ቅዱሳን
ቀሲስ ዶ/ር ሰሙ ምትኩ
የማኅበረ ቅዱሳን ሰብሳቢ
ፊርማና ማህተም አለው¾

No comments:

Post a Comment