ከጎሹ ገብሩ
የወልቃይት ባህልና የማንነት ጥያቄ በሚል ባለ ስምንት ገፅ መጣጥፍ ጥር 6 2016 በኢትዮሚድያ ድህረ ገጽ የወጣው ጽህፍ ደግሜ ደጋግሜ አንብቤዋለሁ። ወንድሜ ኃይሉና እኔ ተወልደን ያደግነው ተ.ሐ.ህ.ት በምትባል ከትግራይ አብራክ የተፈጠረች አረመኔ የፋሽሽቶች ጥርቅም ከአያት ቅድመ አያቶቻችን ይዘነው የኖርነውን ባድማችን ቀምታ ወገኖቻችን በመግደልና በማባረር ዘር አልባ ባስቀረችዉ በወልቃይት ጠገዴ አካባቢ ስንሆን ሁለታችንም የሚያስተሳስረን የዝምድና ሰንሰልት አለን ። ለተወሰነ አመትም በቅርበት አብረን በጎንደር ከተማ ስንኖር በመከባበርና በመደጋገፍ ጥሩ ጊዜ አሳልፈናል አቶ ኃይሉ ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ተሞክሮን ለማዳበር (ሰርቪስ ትሬኒንግ) በአስተማሪነት ተመድበው እኔም የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሆኜ ነው። በዛን ወቅት ወንድም ኃይሉ በእዉቀት የበሰሉና በተማሪዎች ንቅናቄም ዋና ተዋናኝ እንደነበሩ ብዙ ምልክቶች አይ ነበር። እኔም በወቅቱ ፖለቲካዊ አስተሳሰቤ ብስለት ያልነበረው፤በአገር ወዳድነትና በስሜት የምጋልብ ነበርኩ። አኔና አቶ ኃይሉ የሺወንድም ከ 1969 ዓ.ም ጀምሮ ለብዙ ዓመታት ተለያይትን ከቆየን በኋላ በ2006 ዓ.ም ኖርወይ እያሉ በተሌፎን ኮንፈረንስ ተገናኝተን በወቅታዊው የአካባቢያችን ችግር ለተወሰን ግዜ ጠለቅ ያለ ዉይይት ስናደርግ ወልቃይትን አስመልክቶ የነበራቸው አመለካከት ተሐህት ቦታችን ለቃ መውጣት አለበት ደንበራችን ተከዜ ነው የሚል አቋም ነበር ሲያስተጋቡት የነበረው። አሁን ያጋጠማቸው እንቅፋት ትክክለኛ መንስኤው ባላውቅም ምክንያት ይሆናል ብዬ የገመትኩት በስልጣን እየባለጉ ባሉት ስጋ ዘመዶቻቸው ተፅእኖ ብየ እንዳልል ወንድም ኃይሉ በትምህርት የበሰሉት በወያኔ ከበሮ ተታለው የትውልድ ሃረጋቸው፤ ባድማቸውና ወገኖቻቸውን ያስጨፈጨፉ ከሃዲዎች ሲሉ የሚወዱት ሞላውን የወልቃይት ሕዝብ ለታሪክ ጠባሳነት አሳልፈው ይሰጣሉ ብዬ አልገምትም ሌላ የተደበቀ አጀንዳ ካልነበራቸው በቀር።
ወደ ተነሳሁበት አርዕስት ወደ አቶ ኃይሉ መጣጥፍ ልመለስና በፅሁፉቸው ላይ ያስነበቡን አሉታዊ አባባሎች ሃቁን በማያንፀባርቁ ክሶች ላይ አስተያየቴን ስሰነዝር በፅኃፊው ግለሰብ ላይ ምንም ዓይነት የጥላቻ ቁርሾ እንደለለኝ ቅድምያ ግልፅ ማድረግ እሻለሁ። በ.ተ.ሐ.ህ.ት አረር ጥይት የተቆላው የወልቃይት ህዝብ ለሁለታችንም እኩል የሚደርሰን ቢሆንም በሁለታችን መካከል የሃሳብ አለመግባባት ልዩነት ሊኖሩን ይችላል። አቶ ሐይሉ የመሰላቸው መጻፍ መብታቸው ሲሆን እኔም በፅሁፉ የተሰማኝን መተቸት መብቴ ነዉ። ወንድም ሐይሉም ተተቸሁ ብለው ከንፈርዎ እንደማይነክሱ እርግጠኛ ነኝ።
1ኛ/ በወልቃይት ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጽሟል በሚሉ አካላት የወልቃይትን ባህል ለማጥፋት በትግራይ ነፃ አውጭ የተቀናጀና የተቀነባበረ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ደርሶብናል ከትግራይ ጋር በባህል፤በስነልቦናና በመሳሰሉት መስፈርቶች አንገናኝም በማለት የወልቃይት አማራ ማንነትን አንግበው የተነሱ ይሉናል።
በመሠረቱ ይህን ጥያቄ ከሚያነሱት መካከል አንዱ እኔ ነኝ ነገር ግን የእርስዎ አቋም ግልጽ ያልሆነልኝ ነገር ቢኖር ወገነዎ በሆነው በወልቃይት ህዝብ ላይ የደረሰውን አሰቃቂ ግድያና ጭፍጨፋ እንደሚጋሩ ለስለስ ባለ አረፍተነገር ጠቁመዋል። ተ.ሐ.ህ.ትን ግን በዘር ማጥፋት ወንጀል አልከሰሷትም እንዲያውም ተ.ሐ.ህ.ት ምክንያት ይሆነኛል ብላ ለምታቀርበው የማካለል ቆርጠህ ቀጥል ምክንያቶች ድጋፍ በመስጠት ከበሮዋ እስኪቀደድ ድረስ እንድትደልቅ አድርገዋታል። የወልቃይት ህዝብ ትግርኛ በመናገሩ የተነሳ ነው የተካለለው የሚል ቃል እርስዎን በመሰለ የታሪክ ምሁር አንደበት መነገሩ በጣም የሚያሸማቅቅ፤ ተስፋ የሚያስቆርጥና የሚያሳዝንም ነው። የትውልድ ቦታዎን የመዘበረችና የወገኖችዎ ደም ላፈሰሰች ጠላት ደርጅት አጋር መስለው ለመታየት የመረጡበት ምክንያት ይሆናል ብየ የገመትኩት የነብሰ ገዳይዋ ድርጅት ጡት እያላመጡ ያደጉትን ከሁለት ሦስት ለማይበልጡት ዘመዶችዎ ብለው ከሆነ ከእርስዎ የማይጠበቅ ድርጊት ነው። አቶ ኃይሉ ትላንት አንግበው የተነሱለት ብሩህ አላማ መስመሩ ስቶ ብር ማለቱ ‘ፈጭቸ ፈጭቸ ቋቱን ብዳስሰው እልም ብሎ ቀረ እንደ ዘመኑ ሰው’ እንዳሉት አበው ሆነና እንደ ግመል—ወደ ኋልዮሽ መጓዝዎ በጣም ያሳዝናል። ወንድሜ ሆይ ተ.ሐ.ህ.ት ወደ ወልቃይት ተንደፍድፋ የመጣችበትን ጉዳይ ስር መሰረቱ እያወቁ በሸፍንፍን ለማለፍ መሞከርዎ ወልቃይት የጎረፈው የንፁሃን ደም መች የአውሬዎች ሆነና የኔም የርስዎም ወገኖች ደም እኮ ነው ያለ ምንም ምክንያት እንደ እንሰሳ ባልሰላ ቢላዋ በ.ተ.ሐ.ህ.ት ቅጥረኛ ምልሻዎች ተቆራርጠው ለዘልዓለም ያሸለቡት ምናልባት የእርስዎ ቅርብ ዘመዶች ሌላው ወልቃይቴ የደረሰበት የሞት ፅዋ አልደረሰም ይሆናል በወንድምዎ እና በአክስትዎ ልጅ ተከላካይነት። በአካባቢው ተወልደን ያደግን በተለያዩ የዓለም ዙርያ የምንኖረው ላንቃችን እስኪዘጋ ድረስ የምንጮኸው ለግል ጥቅማችን ብለን ሳይሆን ድምፃቸው ለታፈኑት ወገኖቻችን ድምፅ ለመሆን ነው እንጅ መች እንደ የቀበሮዋ ታሪክ የበሬ—ይወድቅልኝ ይሆናል ብላ ስትከተል እንደ ዋለችው እኛም ለሆዳችን ስንል በወገኖቻችን ደም ለታጠቡት ወያኔዎች ተንበረከክን። ይህን በማድረጋችን ታፍኖ የቆየው የወልቃይቴዎች ግፍና በደል ሁሉም እንዲያውቀው በማድረጋችን በርቱ እንደማለት ፈንታ በጥላቻ የታወሩ የሚል ስያሜ በእርስዎ ቃል ተሰንዝሯል ቢሆንም በጣም ኩራት ይሰማናል የደደቢት ሽፍታ ያልተጠላ ማን ይጠላ ብለው ነው። እንደነ አቶ ገብረመድህን አርአያ የመሳሰሉ አገር ወዳድ የትግራይ ተወላጆች የዘር ሃረግ ሳይገድባቸው ተ.ሐ.ህ.ት በወልቃይት ሕዝብ ላይ የፈፀመችው የዘር ማጥፋትን ድርጊት ለመላው ኢትዮጵያዊና ለዓለም ሕብረተሰብ ሲያጋልጡ እርስዎ ግን የወገንዎን ማንነት ለችርቻሮ ገበያ በማቅረብ ስራ መጠመድዎ በጣም አሳፋሪና የሚያሸማቅቅ ነው። ወንድሜ ሆይ ትግርኛ በመናገራችን ብቻ አይደለም ይህን ሁሉ በደል የፈፀመችብን ከአያት ቅድመ አያት ይዘነው የቆየነውን ለም መሬት ዘርፋ ወርቃማው ወገኔ እያለች በባዶ ሜዳ ላይ ለምትደልለው የትግራይ ህዝብ ለመጥቀም ብላ ሳይሆን ኢትዮጵያን ለማጥፋት ስትል እቅድ አውጥታ ለተነሳችበት ዕኩይ ተግባሯ ለማሳካት ስትል እንጅ የወልቃይት ህዝብን በወገንነት ዛሬም ሆነ ትላንትና ፈርጃው አታውቅም። ወገኔ ነው ብላ የምታምን ቢሆን ኑሮ በጥይት ባሩድ በነበልባል እሳት እያቃጠለችና እየጨፈጨፈች ከቀየው ባላባረረችው ነበር። ትግርኛ በመናገሩ ከለልኩት ያለችው ሕብረተሰብ እኮ አጥፍተዋለች መሬቱ ብቻ ነው ትግርኛ ተናጋሪ ሁኖ የቀረው። “ጌታውን ፈርቶ አሽከሩን” እንዲሉ ሆነ እንጅ ተጋድሎ ሐርነት ትግራይ በቋንቋ ማካለል ከፈለገች ከኤርትራ የበለጠ የሚቀርባት ወገን ያለ አይመስለኝም።
2ኛ/ ለምሳሌ ያህል ይሉና አሜሪካውያን እና እንግሊዛውያን የአንድ ቋንቋ ማለትም የእንግሊዘኛ ቋንቋ ተናጋሪ ናቸው ነገር ግን አንድ ብሔር አይደሉም ስለዚህ የተለያዩ ብሔረሰቦች የተለያዩ ቋንቋ መናገር ይኖርባቸዋል ማለት አይደለም ይሉና…..
ተ.ሐ.ህ.ት የወልቃይትን ሕዝብ ትግርኛ በመናገሩ በገመድ ጎትታ ተከዜን አሻግራ ትግሬ መሆን አለብህ እንዳለችው እንግሊዝም አሜሪካዉያንን ቋንቋየን ሰለምትናገሩ የያዛችሁት መሬት በቁጥጥሬ ሥር አዉዬ የፈለኩትን አደርጋለሁ ማለት ትችላለች እንደማለት ነው። የወልቃይት ሕዝብ ከአማራው ወገኑ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ በመከባበር ለዘመናት ያዳበረውን የትዉልድ ዝርያ በማንም ጠመንጃ ነካሽ ሽፍታ ሊቀለበስ እንደማይችል በልበ ሙሉነት ላረጋግጥልዎ እወዳለሁ። የወልቃይትና የትግራይ ሕዝብ ክልል ሳያግደው በጉርብትና አና በኢትዮጵያዊነት ተከባብሮና ተደጋግፎ እንደቆየው አሁንም አብሮ ይኖራል ። ከኢትዮጲስ የግዛት ዘመን ጀምሮ መጠርያው የሆነውን ብሔረሰብ በሃይል ተቀምቶ የደደቢቶች አዲሱን የመሳፍንታዊ ትውልድ አቤት ወዴት እሺ ጌቶች ብለህ ተቀበል ብሎ ወደ ጠፋው የባርነት ሥርዓት ለመመለስ ሽርጉድ ማለቱ ለሁላችንም የሚበጅ አይሆንም አሁኑን መቆም ይኖርበታል። ሸዉራራ ታሪክ ትቶ ማለፍ ለዘልዓለም ያስወቅሳል። ፋሽሽት ኢጣልያ ሃገራችን በወረረችበት ወቅት እንደ አሁኖቹ ባንዳወች በጥቅም ተደልለው ከጠላት ጋር ያበሩት ሁሉ እስከ አሁን ድረስ በባንዳነት ሲወቀሱ ይኖራሉ። ዛሬ ቢመሽ ነገ ይነጋልና አርቆ ማሰቡ አማራጭ የማይገኝለት ዘዴ ነው። ስለዚህ ግዜው ሳይመሽ ለእውነት እንጂ ለጥቅም መሯሯጥ ዉርደትን ያስከትላል።
3ኛ/ የወልቃይት ህዝብ ከትግራይ ብሔረሰብ ጋር የሚመሳሰለው በቀጥታ ሳይሆን በተዘዋዋሪ መንገድ ነው።
ይህ አባባል አስደንጋጭም አሳዛኝም አሳፋሪም ነው። ጎበዝ አባት እንደለለን ሜዳ ላይ እንደዋለልን መቅረታችን ነው? እንደ ወንድም ኃይሉ አገላለፅ በተዘዋዋሪ የሚል ህብረተስብ ሰምቼ አላውቅም የተዘዋዋሪ ጦርነት(ፕሯክሲ ዋር) አሜሪካ ለቅጥረኛውና ተላላኪው መለሰ ዜናዊ ገንዘብ እየሰጠች በአልሸባብ ላይ እየተደረገ እንደ ቆየውና አሁንም እንድቀጠለው ጦርነት ወልቃይቴን አመሳስሎ በምሳሌ ማቅረብ የተሳሳተ አገላላፅ ነው። ተ.ሐ.ህ.ትም በወልቃይቴወች ተቀባይነት እንደለላት ተረድታ የከበሳ ትግረኛ ስለምትናገሩ ወደኛ አካለልናችሁ ለማለት እንዲያመቻት ይሆን አዲሱ ማንነት የተሽለምነው? ለተወደዳችሁ አገር ወዳድ ወልቃይቴዎች በ አቶ ኃይሉ የሽወንድም የተሰጠን አዲሱ ማንነት እንደ አለፈው የባርያው ስራዓት ለአሁኖቹ የደደቢት ሽፍቶች ወፍጮ ፈጭዎችና አረም አራሚዎች ሆነን ከምንቀር ሁላችን በጋራ በመነሳት ወላጆቻችን ያጎናጸፉን ጀግንነት በማደስ የተጀመረውን ትግል አፋፍመን ከደደቢት ሽፍቶች መንጋጋ ነፃ መዉጣት አለብን። አቶ ኃይሉ በግል በቤተሰቦቻቸው ውስጥ የኤርትራም የትግራይም ዝምድናና ትስስር ሊኖራቸው ይችላል ነገር ግን ወልቃይቴ የሆነው ሁሉ ግን በልበ ሙሉነት የፈለቀበትን ታሪክ የሚያውቅ በማንነቱ ሊሸጥ ሊለወጥ የማይችል ኩሩ ሕዝብ እንጅ ዘሩን ክዶ ለጥቅም የሚንበረከክ አይደለም።
4ኛ/ ቁጥራቸው ቀላል ያልሆነ ወልቃይቴወች አማራም ትግሬም እንዳልሆኑ ይናገራሉ ስለዚህ የወልቃይት ጥያቄ ዘላቂ መፍትሄ ከነዚህ ሶስት መስመሮች በአንዱ ላይ የሚመረኮዝ ይሆናል(በትግሬ፤በአማራ ወይም ራስ ገዝ)
ለወልቃይት ህዝብ ፍፁም ዲሞክራሲ ሰፍኖ ምርጫህ ምንድን ነው ቢሉት መልሱ አንድና አንድ ብቻ ነው። ይሄውም ተንደላቅቄና ተከብሬ የኖርኩበት የአማራነት ዘር ግንድ ቅንጣት ያህል በደል ያልበደለኝ፤ በሃብቴና በርስቴ እንደፈለኩ አዝዤ፤ጠረፌን ራሴ በነደፍኩት ወታደራዊ ስልትና በንብረቴ የገዛሁትን መከላከያ በመጠቀም ደንብሬና ጠረፌን ሳላስደፍር ጠብቄ እንድኖር መብቴንና ማንነቴ አስከብሮ ከተወለድኩበትና ካደኩበት አካባቢ በሰላም እንድኖር መብት ለሰጠኝ ብሔረ አማራነትን ብሎ 99% ድምፅ በመስጠት ማንነቱን ያለ ማወላወል ይፋ እንደሚያደርግ በእርግጠኛነት መናገር እችላለሁ። ቀሪው 1% የቤተሰብ ስብስብ ደግሞ የወይዘሮ አዜብ ስርወ መንግስት አሟሟቂዎችና የተ.ሐ.ህ.ት ጉርሻ ጠባቂዎች ድምፅ ሆኖ የወልቃይት ህዝብ በአቸናፊነት እንደሚወጣ መተንበይ ሳይሆን ሀቀኝነት ያለው አባባል ነው። ነገር ግን ኢትዮጵያ ሃገራችን በደደቢት ሽፍታዎች እጅ ሥር በወደቀችበት ዘመን 100% አሸነፍን ባሉበት ወቅት ምርጫ የሚባል ማደናገሪያ የሚታሰብ አይሆንም። የወልቃይት ጥያቄ እኮ የመገንጠል ጥያቄ አይደለም የማንነት፤ የግለሰብ መብት፤ የህልውናና የእኩልነት እንጅ የግለሰብ ፈላጭ ቆራጭ ገዥነት ጥም ለማርካት አይደለም። ይህ ኩሩ ህዝብ የሚያምነው ማንኛውም ኢትዮጵዊ ክልልና ዘር ሳያግደው በሙያውና በእውቀቱ ብቁ የሆነ ድርጅት ወይም ግለሰብ ይምራኝ ነው እያለው ያለው። ይህች ራስ ገዝ የሚሏት ፅንሰ ሃሳብ እንደ አሁን ይፋ አልሆነችም እንጂ ከ10 ዓመት በፊት በውጭ ያለነውን የወልቃይት ተወላጆች ለማታለል የ.ተ.ሐ.ህ.ት ታማኝ ካድሪዎች የሆኑ ሁለት ትውልደ ወልቃይቴዎች 1ኛ አቶ ፈረደ የሽወንድም( የአቶ ሃይሉ የሽወንድም ታናሽ ወንድም ) 2ኛ አቶ ፀጋይ አስማማው በተ.ሐ.ህ.ት ሳንባ የሚተነፍስና በሃሰት የሚፈርድ በጌቶቻቸው ተልከው እንደመጡ ሕዝቡን በእጅ አዙር ሰብስበው የነሱ ደጋፊ የሆነ አንድ ግለሰብ ስብስባው ከመጀምሩ በፊት እንዲህ ብለህ ጠይቅ ተብሎ መመርያ ተሰጥቶት ባህር አቋርጠው የመጡበትን አጀንዳ በጥያቄ አቅርቦታል። የወልቃይት ህዝብ የራስ ገዝነት መብት አለው ወይ ብሎ መጠየቁ በስብሰባው ላይ የነበሩ አገር ወዳድ የወልቃይት ተወላጆች “እኛም አውቀናል ጉድጓድ ጭረናል”ብለው አፊዘውባቸዋል። ያን ግዜ የተወጠነው ደባ ነው አሁን በተግባር ላይ ለማዋል ያልነበረ ታሪክና ያልተፈጸም በደል በአማራዎች ተፈፅመ እየተባለ ያለው። በአሁኑ ጊዜ የወልቃይት ህዝብ ለ40 ዓመት እንዳልናገር አፌን ሸብባችሁ በፍርሃት ቆፈንና በድህነት አሮንቃ የኖርኩት ይበቃኛል ብሎ በጥቁር መጋረጃ የተሸፈኑትን አይኖቹንና እንደ በሬ የተሸበበው አፉን ለማውለቅ በሚፈረጋገጥበት ወቅት የአዜብ መስፍን ስርወ መንግስት የፋሽሽቱን ባለቤቷ መፈክር በማደስ በደማችን የወረርናት ወልቃይት አማራ መልሶ አይቆጣጠራትም ከፈለጋችሁ በ.ተ.ሐ.ህ.ት መጉዚትነት ራስ ገዝ መጠየቅ ትችላላችሁ በማለት የወልቃይት ህዝብ እንደተቀበረ እንዲኖር ይህ ዓይነት ማነቆ ያዘጋጁለት። “ደሮንሲደልሏት በመጫኛ ጣሏት” የሚለው የአነጋገር ዘይቤ ለዚህ አርዕስት የሚስማማ ነው።
5ኛ/ በአማረኛ ተናጋሪዎቹ ገዥዎችና በትግርኛ ተናጋርዎቹ ወልቃይቴዎች መካከል በዙ የቋንቋና የባህል ልዩነቶች ስለነበሩ የባህሎች መደባለቅና አንዱን ሌላውን የመተካት እድል የተመቻቼ አልነበረም።
እኔ በ60ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ ያለሁ ነኝ ከህፃንነቴ ጀምሬ የሰማሁትና ያየሁት ወልቃይት ጠገዴ ሲያስተዳድሩ የነበሩት ወልቃይት ተወልደው ያደጉ በተፈጥሮ እዉቀት የበሰሉና ፈሪሃ እግዚአብሔር ያላቸው ገለሰቦች እንጂ ከሌላ አካባቢ የቋንቋና የባህል ልዩነት የነበራቸው አይደሉም የመተካካት ችግርም አልነበረም።ሥለዚህ አቶ ኃይሉ እርስዎም የሚዘነጉት አይመስለኝም ገዥው ወልቃይቴና ተገዥው ወልቃይቴ አማርኛ የሚናገሩና የአማራ ባህል ይዘው ለብዙ ዘመናት የኖሩ ስለሆነ ትግርኛ ተናጋሪዎቹ ወልቃይቴ የሚል ቃል ሕዝቡን ለመከፋፈል ረቂቅ የሆነ የተ.ሐ.ህ.ት ዘዴ ነው፡፡ ለምሳሌ፦ ጀግናውና አርበኛው ቢትወደድ አዳነ መኮነን፤ ደጃዝማች ደስታ ማሩ፤ቀኛ/ ገብሩ ገብረመስቀል፤ ቀኛ/ትርፌ ጣሰው ደጃዝማች መኮነን፤ደጃዝማች በዛብሕ አደመ፤ ግራዝማች ተገኘ ቢተው፤ፊታውራሪ አዲሱ መኮነን፤ ፊታውራሪ የሺወንድም ናደው(የእርስዎ ወላጅ አባት)፤ቀኛ/ ይርጋ ነጋሽ፤ፊታዉራሪ መለሰ ኃይሉ፤ ቀኛ/ ኃለማርያም ደሴ፤ቀኛ/አባይ ወልደማርያም፤ ፍታውራሪ ነጋ፤ ልጅ ተድላ ወልደማርያም፤ልጅ አስማማው ይርጋ፤ልጅ አቡሃይ አብተው፤ አቶ እንደሻ አያለው፤ አቶ ባየው ቸኮል ወዘት. ነበሩ በተለያየ የስራ ዘርፍ ተመድበው አካባቢውን ሲያስተዳድሩ የነበሩት። እንግዲህ እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት አካባቢውን ሲያስተዳድሩ የነበሩ ባህላቸውና ቋንቋቸው እንደማንኛውም ምልአተ ወልቃይቴ አማራዊነት ታሪካቸውን አክብረው ይዘው ቆይተው ለተተኪው ትውልድ አስረክበውን ያለፉት። አንድም የትግራይ ተወላጅ ተከዜን ተሻግሮ ወልቃይትን ያስተዳደረበት ግዜ የለም። ደንበራችን ተከዜ እንጅ ተ.ሐ.ህ.ት ጠፍጥፎ በሰራው ካርታ አንከለልም።
ሌላው አሳፋሪ ነገር ተ.ሐ.ህ.ት የወልቃይትን ወጣትና ሽማግሌ በብዛት ግድያ(ማስ መርደር) እንደተፈፅመበት ሳይጠቅሱ ከአምሳ ሁለት ዓመት በፊት በአቶ መኮነን በርሄ የተፈጸመው ግድያ አግዝፈውና አባዝተው በአማራነት የከሰሷቸው ክቡር ቢትወደድ አዳነ መኮነንን ያለ ምክንያት አይደለም በጠገዴ ሕዝብና በወልቃይት ህዝብ ልዩነት ተፈጥሮ ለመብቱ በአንድነት እንዳይነሳ መሰናክል ለመፍጠር ይመስላል ግን እኮ የእርስዎ መላ ምት አይመስለኝም ምን አልባት ከመጋረጃው በኋላ የተውጠነጠነ ሃሳብ እንዳይሆን እጠረጥራለሁ። የወልቃይትን ንብረት ዘማች በማሰማራት ይዘረፉት ነበር ላሉት ክስም የወልቃይት ሕዝብ ብቻውን በልቶ አያውቅም እንኳንስ ለተከበሩ ቢትወደድ አዳነ መኮነን ወር ለማይሞላ እንግድንት ቀርቶ ለ40 ዓመታት ያህል ንብረቱና ልጆቹን ለበላበት የደደቢት ሽፍቶችም ቆሽቱ እያረረ ከየትም ቦታ ቀምሰውት የማያውቁ ምግብ በመመገብ የጠወለገው ፊታቸው ፈካ አንዲል ያደረገ ለጋስ ህዝብ ነው። ቢትወደድ አዳነ ወደ ቃፍትያ የመጡበት ምክንያት ያካባቢዉን ህዝብ ለማራቆት ብልው ሳይሆን በዝያን ግዜ አካባቢውን ያስተዳድሩ የነበሩት ግለስብና የአቶ መኮነን በርሄ ዘመዶች ጭምር የአካባቢያችንን ሰላም ያወከ ግለሰብ አለና መጥተው መፍትሄ እንዲሰጡን ብለው በጠየቁት ጥያቄ መስረት ነበር ወደ ቦታው የሄዱት። ከቦታው ተገኝተው ቅድምያ ያደረጉት ነገር ቢኖር አቶ መኮነን በርሄ፤ዘመድ አዝማድና የአካባቢው ህዝብ በተገኘበት ጉባኤ ጠርተው ካነጋገሩ በኋላ በጥፋት የተከሰሱትን ግለሰብ ነገሩ ተጣርቶ ውሳኔ እስከሚሰጠው ድረስ ዋስ እንዲጠሩ ተጠየቁ ከስብሰባው ውስጥ የነበረው ባዕድም ይሁን የቅርብ ዘመድ ለአቶ መኮነን በርሄ እዋሳለሁ የሚል ሰው ሲታጣ በል ዋስ እስከሚገኝ ድረስ በማረፍያ ቤት እንዲቆዩ ሲባሉ ከኪሳቸው ሽጉጥ አውጥተው በተኮሱት ጥይት ቢትወደድ አዳነ መኮነን ተመትተው ሲወድቁ ከዘበኞቻቸው አንዱ ተኩሶ አቶ መኮነን በርሄን ገደላቸው ከሁሉ የሚገርመው ለተፈፅመባቸው የግድያ ሙከራ ሳያዝኑ የአቶ መኮነን በርሄ መሞት ሲሰሙ ለምን ገደላችሁት ለክፉ ቀን የሚሆን ጀግና ብለው ከልብ አዘኑ እንጂ ደግ ሰራችሁ አላሉም። አቶ መኮነን በርሄም ወደ ስብሰባው ከመግባታቸው በፊት አብረዋቸው ከነበሩት የተወሰኑትን ከውጭ ሆነው ሁኔታው እንዲጠባበቁና ተኩስ ከተጀመረ ሽፋን እንዲሰጧቸው የተበሉት ግለስቦች ተኩስ እንደሰሙ ፈርጥጠው ነበር የሄዱት እንግዲህ እንዲህ አይነቱ የበሰለ አመራር ከአሁኖቹ ነብሰ በላ ህወሃቶች ጋር ለማመሳሰል መጣሩ ፍርዱ ላንባብያን ልተወው። ሌላው የአቶ ኃይሉ አሳፋሪ ክስ ዘማች ሆነው የሄዱት አስገድደው ሴቶችን ይደፍሩ ነበር ላሉት ከአሁን በፊት ተሰምቶና ተነግሮ የማይታወቅ የወልቃይቴዎችን ጀግንነት የሚያጎድፍ የጠላት ወሬ ነው።
6ኛ/ ወልቃይት በትግራይ ክልል ውስጥ መቀጠሉ የተሻለ አማራጭ መሆኑን የሚያሳምኑ ብዙ የመከራከሪያ ነጥቦች አሉ ይሉናል።
የተ.ሐ.ህ.ት ሥም ማጥፋት ዘመቻ በእርስዎ ቃል መድገሙ ምን ዓይነት ትምህርት ይሰጣል ብለው እንዳሰቡ ግራ የሚያጋባ አባባል ነው። አልያም የእርስዎ ስም ተጠቅሞ የፃፈ ይኖር ይሆን የሚል ጥረጣሬ አድሮብኛል? ‘ትግሬ ነህ ሰው’ የሚለው የማጥላላት ቃል ለ50 ዓመታት ያሰለቸ እውነትነት የለለው ቃል በእርስዎ አፍ መደገሙ ማንን ለማስደሰት ይሆን ከቶ? በስልጣን ያለችው ወንበዴዋ ድርጅት በወልቃይት ህዝብ የተነሳው እረሮ የአጀንዳውን ይዘት ለማስቀየር ሆን ብላ የተጠቀመችበት ግዜ ያልፈበት ዘዴ ነው። ይህ ቃል ተናገርች የሚባለው ሁመራ ውስጥ በሴተኛ አዳሪ ስትኖር የነበረች የትግራይ ተወላጅ በአንድ ቀን ውስጥ የአስራ አንድ ሰዎች ሬሳ በቤቷ ደጃፍ አድርጎ ወደ ማርያም ቤትክርስትያን ሲያልፍ በሀዘን እየተከዘች እያለች 12ኛው ሲመጣ ይሄስ ‘ሰው ነው አማራ’(የትግራይ ሰው ነው ወይንስ አማራ)ማለቷ ነው እንጅ አንዱን ዘር አግዝፋ ሌላውን ለማንቋሸሽ የተጠቀመችበት ቃል አልነበረም። ተንኮለኞች ግን ሕዝብ ከሕዝብ ጋር ለማጋጨትና ለማጣላት ወልቃይቴዎች እንዲህ እያሉ ይንቁን ነበር እያሉ የማይረሳ አፍ ወለድ የጥላቻ ቁርሾ አሁንም እንደ ታላቅ ታሪካዊ አባባል ተቆጥሮ በመስኮት ብቅ ማለቱ አንገት የሚያስደፋ ግዜው ያለፈበት አፅያፊ ፌዝ ነው።
አንድ ህብረተሰብ አብሮ የመኖሩን እድል ከፍ የሚያደርገው ትግርኛ በመናገሩ ነው ብዬ አላምንም ምክንያቱም ቋንቋ ለመግባቢያ ከመሆኑ አልፎ ለሌላ ጥቅም የሚውልበት ምክንያት አይታይም “ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ” ሆነ እንጅ አብዛኛው የኢትዮጵያ ህዝብ አማርኛ መናገር ይችላል ለምን አማራ ነህ አይባልም? ስለዚህ የወልቃይት ህዝብ ትግርኛ በመቅሰሙ የትግራ ዜግነት ሳያምንበት መቀበል አለብህ ብሎ ማስገደድ የነብሰ በላው የእህትዎ ባለቤት የመለሰ ዜናዊ የጥፋት ራዕይ ሲባል የሰፊው ሕዝብ ሥቃይና መከራ ዳግም ለማራዘም ቀዳዳ መሻቱ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ የዘቀጠ ታሪክ ነው የሚሆነውና ለአንድ አፍታ ቆም ብለው በማሰብ ለህዝብዎ የሚጠቅም ያልተወላገደ ታሪካዊ ትምህርት ለማስተማር እንዲጥሩ ወንድማዊ ምክሬን ልለግስልዎት አወዳለሁ። ህዝባችን አልተማረም ብለን በማር የተለወሰ የኮሶ መድሃኒት እንደ የጋርዮሽ ዘመን ና እንጋትህ ብንለው ጉዳቱና ጥቅሙ ሳይመረምር አሺ ብሎ መቀበሉ ቀርቷል። እኔም ሆንኩ እርስዎ በጫርነው ማስታወሻ የሚደለል ህዝብ ያለ አይመስለኝም። ከሁለት ሦስት ለማይበልጡ የአካባቢው ተወላጅ ካድሬዎች ጥቅም ለማስከበር ተብሎ ለዘመናት የቆየዉን የህብረተሰብ ትስስር በዉሃና ዘይት መስሎ ግራ ለማጋባት መጣሩ በታሪክ ያስወቅሳል። ወንድምዎ አቶ ፈረደ የሺወንድም እጁ በወልቃይት ንፁህ ሕዝብ ደም የከረፋ መሆኑ እያወቁ ህዝብን ይቅርታ እንደ መጠየቅ ፈንታ ዳግም አገርሽቶበት ከመቀሌ አዲስ አበባ፤ከጎንደር ሁመራ፤ማይ ካድራ፤ቃፍትያና ወልቃይት እየተዘዋወረ እጃችሁ ይቆረጣል፤ አይናችሁም ይጠፋል እያለ የወልቃይትን ወጣቶች ከተወለዱበት ቦታ ገፍትሮ እያስወጣ አንገታቸው ለአረብ ስለት እያመቻቸ መሆኑ ተነቅቶበታልና ከእንደዚህ ዓይነት ተግባር ተቆጥቦ ሕዝቡን ይቅርታ መጠየቁ ብልህነት እንጂ ወርደት አይደለም። አቶ ኃይሉ ወልቃይት ለትግራይ እንጅ ለአማራ ቅርበት የለውም ባሉ ሳምንት ባልሞላው ግዜ የአሜሪካ ራድዮ ድምጽ አቶ አታላይ እና ኮሌኔል ደመቀ እንዲሁም አንዱን የተ.ሐ.ህ.ት ተወካይ የሆነው ግለሰብ ወይዘሮ ትዝታ በላቸው ባቀረበችላቸው ጥያቄ የዓማራ ማንነታችን ያለሕዝብ ፍቃድ በጠበንጅ ኃይል ነው ወደ ትግራይ የተካለልነው እና ወደ አማራው ብሄራችን መመለስ አለብን የሚለው የወልቃይት ሕዝብ ወክሎ ያስቀመጠን ተወካዮቹ ነን በማለት ለቀረበላቸው ጥያቄ ማስረጃን በማስደገፍ በሚያረካ ቃል ሃቁን ፍርጥርጥ አድርገው ሲገልፁ በተሐህት በኩል የቀረበው ወኪል ግን ሊያዝና ሊጨበጥ በማይቻል በውሸት የተቀነባበረ መተባተብ ስሰማ ያዘንኩት ለሆድ አደሩ ግለሰብ እንዲህ በል ተብሎ ተፅፎ ለተሰጠው ሳይሆን ያ ሁሉ እውቀት ይዘው ወገናቸው የሆነውን የወልቃይት ሕዝብ ለውርደት የዳረጉት አቶ ኃይሉ የሽወንድምን ነው። አቶ ኃይሉ ለብዙ ዓመታት ተደብቀው ከቆዩበት ዋሻ በጋህድ እንደ ነጭ በሬ ዛሬ በግልጽ አደባባይ መታየት የፈለጉበት ምክንያት በእኔ ግምት ራስ ገዝ የምትባለው የተሐህት ማደናግርያ ቃል ጠልፋ አታለለቻቸው መሰለኝ ያሳዝናል እርስዎን የመሰለ አዋቂ ግለስብ ከአቶ አቦሃይ ጋር አደባባይ ላይ መዋል ያሳፍራል ሹመት ይባርክ እላለሁ።
7ኛ/ አማራውና ወልቃይቴውን በዉሃና ዘይት፤ ትግሬውና ወልቃይቴውን በዉሃና ወተት ይመሰላል ይሉናል!!
ወንድም ኃይሉ የመሰለዎትን አቋም ለመግለፅ ለምን አቀበትና ቁልቁለት መዝለቅና መውረድ አስፈለገዎት የወልቃይትን ህዝብ እንደፈለጉት በወተትና ውሃ ወይም በዘይትና ውሃ ቢመስሉት የህዝቡ መልስ አንድ አና አንድ ብቻ መሆኑ በተለያዩ አጋጣሚዎች ግልፅ በሆነ ቋንቋ ኢፋ ሲያደርግ እንዲህ ነበር ያለው ማንነቴን ማንም ሊነግረኝ አይችለም የጠራሁ የነጠርኩ ጎንደሬ አማራ እትዮጵያዊ ነኝ።
8ኛ/ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ስርአት በበጎ ጎኑ የሚታወቀው በኢትዮጵያ ውስጥና ሰላም ባልሰፈነባቸው ቀጠናዎች ሰላምና መረጋጋትን በማምጣቱ ነው። የብሄረሰቦችን መልስ በመገኘቱ፡›
አሁንስ የኢትዮጵያን ህዝብ ጆሮ እንደሚያደነቁረው የመለሰ ዜናዊ ሬድዮ ጣብያ ሆኑብኝ የሰላምን ትርጉም ከእርስዎ የበለጠ የሚያውቅ ይኖራል ብየ አልገምትም እስኪ የኢትዮጵያ ህዝብ ያለ ችግርና መከራ የዋለበት ቀን ይቁጠሩልኝ ሰላምና መረጋጋት ከኖረ ለምን ወጣቱ በዱር ገደሉ፤በባህርና በየብሱ እንደ ቅጠል ይረግፋል፤ለምን የተወለደበትን አገር አስጠላው፤ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ግዜ ዲሞክራሲን ያሰፈንኩ ድርጅት ነኝ ባለች በበነገታው መሳርያ ባልታጠቁ ወጣት ተማሪዎች ላይ ለምን የጥይት ኢላማ ተደረጉ፤ለመሆኑ ጋዜጠኞችና ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ያሉበትን ቦታ ያውቃሉ? በኢትዮ ኤርትራ አላስፈላጊ ጦርነት የህዝብን ብሶት ለመሸፋፈን ሲባል ከመቶ ሺህ ህዝብ በላይ የተቀጠፈበት ጦርነት፤የአሜሪካን ምፅዋት ለማግኘት ሲባል አማችዎ መለሰ ዜናዊ ያስፈጀው ወጣት ወዘተ. እስቲ ይንገሩኝ የትኛው ብሄረሰብ ነው መብቱ የተከበረለት? ከተከበረለትስ ለምን የኦሮሞ ተወላጅ ኢትዮጵያውያን ወንድሞቻችን ለመብታቸው ስለጮሁ አናት አናታቸው በጥይት የተመቱ። ከአሁን በፊት ካልሰሙ እኔው ልንገርዎት ሰላም በአገራችን ሰፍኖ አያውቅም ምናልባት በመለሰ ዜናው ግቢ፤በአግአዚ ቅልብ ወታደሮች፤ፍርፋሪ ለቃሚ ካደሬዎች ሰላም ሰፍኖ ሊሆን ይችላል እንጂ ሌላው ኢትዮጵያዊ ከመቃብር በታች ነው እየኖረው ያለው። በአካባቢያችን ዙርያ ከሚኖሩት ጋር ሰላም ሰፍኗል ያሉት ለምን አይሰፍንም የእኔና የእርስዎ አያትና ወላጆች በደማቸው ያቆዩትን ለም መሬት ለገጸበረከት ለሱዳን ሲሰጥ፤ በአረቦችና ቻይናዎች ተደፍራ የማታውቀውን አገር ካስደፈርክ ለምን በሰላም መኖር አይቻልም። ለወንድሜ አቶ ኃይሉ የማሳስበው በሰለጠነው ህብረተሰብ ለብዙ ግዜ አብረው ኑረዋል በአስተሳሰብ ልዩነት ቢጋጩ ቢፋጩም አገራቸውን የሚጎዳ ነገር ሲመጣ ልዩነታቸው ወደ ጎን በመተው በአንድነት ነው የሚቆሙት እንጅ ጥላቻን መሰረት ያደረገ ቁርሾ አይገቡምና ሁላችንም የአገራችን ጉዳይ ማስቀደም ከሁሉም የበበለጠ ስራ መሆን ይኖርበታል የሰው ልጅ ተሰባሪ እቃ ነው አገርና ታሪክ ግን ህያው ናቸው።
የኢትዮጵያ ህዝብ ከአሁን በፊት በዘር የመከፋፈል ችግር ገጥሞት አያውቅም ነገር ግን ሊካድ የማይችል የአስተዳደር ብልሹነት ነበረ። በዘር አድሎ ግን አንዱን ጎድቶ ሌላውን የጠቀመበት ግዜ አልነበረም በርግጥ ውስን የሆኑት በስልጣን መዋቅር ላይ የነበሩት ህዝቡን ይበዘብዙት ነበር ግን እንደ አሁኖቹ ባለጌ የደደቢት ሽፍቶችን ያህል በደል በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶና ተሰምቶ አያዉቅም። ይህችን አውሬ የሆነች የሁላችን ጠላት ድርጅት ከምድረ ገፃችን ካላሰውገድን በሰላም የመኖር ተስፋችን የመነመነ ነው የፖለቲካ ልዩነቶች ወደ ጎን ትተን ህልውናችን ለማረጋገጥ በጋራ መነሳት ሲገባን አንዱ በአንዱ ጣት እየተቀሳሰርን የወገናችን ችግርና ስቃይ እያራዘምነው ያለን እኛው እራሳችን እንጂ ማንም ሊወቀስ አይችልም ወያኔን በየመድረኩ ከመርገም ይልቅ ሰብሰብ ብለን በአንድነት ተማምነን ስንቆም ብቻ ነው ጠላትን ማርበድበድ የምንችለው ሥለዚህ ግዜው አሁን ነው።
ዘረኝነት ይጥፋ!
ኢትዮጵያችን ለዘልዓልም ትኑር።
ጥር 22/2008 ዓ.ም
No comments:
Post a Comment