Thursday, 4 February 2016

እውን ወልቃይት ትግሬ ነው? (ይገረም አለሙ)

ይገረም አለሙ
ወቅቱ 1994 ክረምት ነው፡፡  በየአመቱ ት/ት ቤቶች ሲዘጉ መምህራንን አንደም በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ለማጥመቅ ሁለትም ስራ ፈተው ከዋሉ የሚሰሩት ስለማይታወቅ ጠርንፎ ለማቆየት የሚዘጋጀው ስብሰባ ጎጃም ደብረ ማርቆስ በሶስት አዳራሾች እየተካሄደ ነው፡፡ ቤተ መንግሥት አዳራሽ ሲኒማ ቤትና መንገድ ትራንስፖርት አዳራሽ፡፡
በሲኒማ ቤቱ  ስብሰባ በአወያይነት ከተመደቡት አንዱ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ በእንድ መምህር  ስለሚካሄደው የትምህር አሰጣጥ የሚያውቀውን ሳይሆን የተነገረውን በተረዳው መጠን ለተስባሳቢው ገለጸ፡፡ ይሄው የትምህርት አሰጣጥ አማራ ክልልን ጨምሮ በመላ ሀገሪቱ ውጤታማ ሆኗል ያለው  አወያይ በትግራይ ክልል ብቻ ተግባራዊ አለመሆኑ ጠቅሶ ምክንያት ተብሎ የተነገረውንም  ሲናገር በዚህ ደረጃ የተመደቡት በአብዛኛው ሴቶች ነበሩ፣ ከእነዚህ አብዛኛዎቹ ደግሞ በተመሳሳይ ውቅት በማርገዛቸው ፕሮግራሙን ማስቀጠል አልተቻለም  አለ ፡፡ በዚህ ግዜ አዳራሹ በሳቅ ተሞላ፡፡ መድረኩ ለውይይት ክፍት መሆኑ ሳይገለጽም  ለአስተያየትና ለጥያቄ በርካታ እጆች በአየር ላይ ታዩ፡፤
እውያዩ ገለጻውን አብቅቶ (የተነገረውን ተናግሮ) ቀጣዩ ሰአት የውይይት መሆኑን ገልጾ ቅድሚያ ለሴቶች በሚል የመጀመሪያውን የመናር እድል ለሴት ሰጠ፡፡ እድሉ የተሰጣት መምህርትም ከአንድ እስከ አራተኛ ክፍል በአንድ መምህር ማስተማር በአማራ ክልል ውጤታማ ሆኗል ተብሎ ከመድረክ የተገለጸው  እኛ በተግባር ከምናውቀው ጋር የሚገናኝ አይደለም በማለት ከአወያዩ ገለጻ በተቃራኒ የሆነ አስተያየት ከሰጠች በኋላ አንድ ጥያቄ አለኝ እሱም ምንድን ነው በትግራይ ክልል በዚህ ደረጃ የተመደቡት  አብዛኛዎቹ ሴት መምህራን በመሆናቸውና ከእነርሱም ብዙዎቹ በተመሳሳይ ወቅት በማርገዛቸው ፕሮግራሙ ተግባራዊ አለመሆኑና ወደ ቀድሞው አሰራር መመለሱ ተገልጻል፡፡ እዚህ አማራ ክልል እኛ ሴቶቹ ማርገዝ አልችል ብለን ነው; ወይንስ ወንዱ ማስረገዝ አቅቶት; ጥያቄየ ያሄ ነው ብላ ስትቀመጥአዳራሹ በጭብጨባ በሳቅ በውካታ ተናጋ፡፡ አወያዩ የሚይዝ የሚጨብጠው ጠፍቶት ተደነጋግሮ እየተርበተበተ ቀልዱን አቁሙና ወደ ቁም ነገር አንግባ ማለት ጀመረ፡፤
መምህርቷ አጋጣሚውን በመጠቀም አጠቃላይ ፖለቲካዊ መልእክት ለማስተላለፍ አስባ ያደረገችው ይሆን ወይንም በመድረክ የተነገረው ስሜቷን ነክቶት ለዚሁ ምላሽ ለመስጠት  ብላ የተናገረችው  የምታውቀው እሷ  ብቻ ብትሆንም የተናገረችው ቃል ግን  ጥልቅ መልእክት ያለው ነበር፡፡  የአማራ ወንዶች ማስረገዝ አቃታቸው ወይ; ከባድ ጥያቄ ነው፡፡
ከአስር ዓመታት በላይ ወደ ኋላ ሄጄ ይህን እንዳስታውስ ያደረገኝ አቶ አቦሆይ የተባሉ የህውሀት ሰው ሰሞኑን ከአሜሪካ ድምጽ ራዲዮ ጋር  ባደረጉት ቃለ ምልልስ  ያለምንም ማንገራገር  በድፍረት ወልቃይት ትግሬ ነው ሲሉ መስማቴ ነው፡፡ ሰውየው በዚህ አላበቁም ወልቃይት ትግሬነቱን ለማስከበር የትጥቅ ትግል ማካሄዱን  አሁን በትግራይ ክልል ስር በመሆኑ ደስተኛ መሆኑን ኮሚቴ የሚባሉት ሰዎች ህዝቡን የማይወክሉ እንደሆኑ ወዘተ ተናገሩ፡፡ ንግግራቸው ፈር የለቀቀና ከእውነት የራቀ  መሆኑ ሳያንስ ድፍረታቸው ያስገረማት ጋዜጠኛ (ትዘታ)  ጥያቄዋን ጠንከር ስታደርግባቸው አሁን ትንሽ ስራ አለብኝ ሌላ ግዜ ደውለው እንነጋር በማለት  ጥያቄዋን ከዛ በላይ አንዳትገፋ  አደረጓት፡፡
ግለለሰቡ የአንድ ወረዳ ሹም ቢሆኑም የተናገሩት የተነገራቸውንና ርሳቸው በቦታው ተሸመው እያስፈጸሙት ያለውን የድርጅታቸውን እምነት በመሆኑ በአነስተኛ ሥልጣን ለይ ያለ ሰው የተናገረው ተብሎ ተቃሎ የሚታይ አይደለም፡፡
ታሪክን ሽረው እውነትን ክደው ወልቃይት ትግሬ ነው ሲሉ ንግግራቸው ሳይሆን ንቀታቸው ያበግናል፣ ማንአለብኝነታቸው  ስሜትን ይፈታተናል፤  ድፍረታቸው እልህ ያሲዛል፡፡ የአማራ ወንድ ማስረገዝ ኣቃተው እንዴ  የሚለውን ከላይ የጠቀስናትን መምህርት ጥያቄም ያስታውሳል፡፡ ወልቃይት በብልሀትም በጉልበትም  መሬቱን ተነጥቆ፣   ማንነቱ ተለውጦ ያለአባቱ ትግሬ ተብሎ ሀያ አራት አመት በትግራይ ክልል ስር  መገዛቱ ሳያንስ  ወያኔዎች ደፍረው ወልቃይት ከጥንትም ትግሬ ነው ለማለት የበቁት የወልቃይትን አማራነት የሚያረጋገጥ ወንድ ጠፍቶ ነው ; የሚያሰኝም  ነው፡፡ (በቅርብ ግዜ ተጠናክሮ የቀጠለውን የኮሚቴዎች እንቅስቃሴ ሳይጨምር ነው ታዲያ)
ከላይ ከአፋፉ ላይ ካልከሉት ጠላት አይን የለውም ይገባል ከቤት በማለት ድንበር የሚገፋን ሆነ ግዛት የሚያስፋፋን
ገና ሲጀማምር  ማስቆም እንደሚገባ  በቀረርቶ የሚገልጸው አማራ በምን መንገድ ተታሎ ወይንስ በምን ያህል ጫና ተረቶ ት ነው እንዲህ በገዛ መሬቱ እሱ አንደ ጭሰኛ  ቀማኛው  አንደአባቢድራ ለመኖር የበቃው የሚያሰኝም ነው፡፡ መምህሯ አንዳለችው ማስረገዝ አቅቶት ይሆን!
እንደምንሰማው ከሆነ በወሰዱት ለም መሬት ያረኩት ይበልጡኑ የጎመዡት ወያኔዎች ከወሰዱት የሚበልጥ መሬት እንደሚቀራቸውና ያንንም ለመጠቅለል  እንደሚያልሙ ነው፡፡  ይህም አያያዙን አይተው ጭብጦውን ቀሙት አይነት መሆኑ ነው፡፡
የጥምቀትን በዐል በተለይም የጃንሆይ ሜዳ ክብረ በአልን በልዮ አጨፋፈራቸው በማድመቅ የሚታወቁት የቀድሞው ሰሜን ወሎ የአሁኑ ደቡባዊ ትግራይ ዞን ነዋሪዎች (ራያዎች) በሆታቸው የሚሉት ግጥም በአብዛኛው ፖለቲካዊ ነው፡፡ታዲያ ገና የወያኔ መንግስት ባልረጋ ባልተረጋገባት ግዜ አንስቶ እስከ ቀርብ ግዜ ድረስ ራያ እንጨት ስበር ቆቦ ውኃ ቅዳ ፣ላስታ አንጨት ስበር ጎንደር ውኃ ቅዳ እያሉ ወያኔ ወደመሀል አገር የተንደረደረባቸውን አካባቢዎች ይጠቃቅሱና ወዴት ትሸሻለህ ጎትተህ ጎትተህ ባመጣኸው እዳ  በማለት የአካባቢውን ፖለቲካዊ ሁኔታ ይገልጡት ነበር፡፡
ወያኔ ከደርግ አይብስም ብሎ በተለይም በመላኩ ተፋራ አረመኔያዊ ድርጊት ተማሮ ለወያኔ ድጋፉን የሰጠው ጎንደር መሬቱን ተነጠቀ፤  የጫርኩት እሳት እኔኑ ፈጀኝ ብሎ በድርጊቱ ተቆጭቶ ይህን  ለልጆቼ አላስተልፍም በማለት አማረነቴ ይታወቅ ድንበሬ ይከበር ሲል  ወልቃይት ከጥንትም ትግሬ ነው ተባለ፤ አረ እንዴት ሆኖ በማለት ትግሉን ሲያጠናክር  አማራና ቅማንት የሚል የማዳከሚያ ልዩነት ተፈጠረበት ይህም አልበቃ ብሎ የሱዳንን መሬት ወሮ የሚያርስ ሽፍታ ተብሎ ተወግዞ ጥቃት ታወጀበት፡፡ በወያኔ ስለተቀማው መሬት ሲከራከር ምን ታመጣለህ ተብሎ ቀሪው ለም መሬቱም ለሱዳን ሊሰጥበት ነው፡፡ ይህን ሲያደርጉ ሱሪውን ተጠራጥረውት ወንድነቱን ንቀውት ይሆን፡፡ …እነርሱ ምን ያርጉ ከእኛ ሰው ሲታጣ ነው ያለው ያ ድምጻዊ፡፡
ራያዎች በሆታቸው እንዳሉት  አሁን ያለው ትውልድ ይበጃል ብሎ ጎትቶ ያመጣው  በመሆኑ አንድ ውል ሳያሲዝ ከነገሩ መሸሽ ስለሌለበት ስለማይችል፤ ሁለትም የአካባቢው ሁኔታ በዚህ መልኩ ለመጪው ትውልድ መተላለፍ የሌለበት በመሆኑ የወልቃይትን አማራነት  የድንበሩንም ተከዜነት ማረጋገጥ የዚህ ትውልድ ግዴታ ነው፡፡ ወያኔዎች በብልሀትም በጉልበትም ተከዜን ተሻግረው መሬት መውረር ግዛት ማስፋፋታቸውን በተለያየ መንገድ የተቃወሙ የአካባቢው ተወላጆች የደረሱበት እንደማይታወቅ ሰሞኑን እየሰማን ነው፡፡ ከቅርብ ግዜ ወዲህም ነገሩን የምር ይዘው በህግ ለማስፈጸም የሚጣጣሩትን የኮሚቴ አባላት ከማወከብ አልፎ አዲስ አበባ እንዳይገቡ  እስከማገት ተደርሷል፡፡ይህ ሁሉ ንቀት ነው ማናለብኝነት፡፡
ቢሆንም ግን ይህና መሰል የወያኔ አድራጎት  ምሬቱን አክፍቶትና ብሶቱን አብሶት ነገሮች እነርሱ ወደሚፈልጉት ለኢትዮጵያውያን ግን ወደማይበጅ  አቅጣጫ እንዳያመሩ ቁስለቱን ሁሉ ችሎ፣ ንቀቱን ታግሶ፣ ጥቃቱን ተቋቁሞ ከእነርሱ በላይ ማሰብን ይጠይቃል፡፡ የገበያ ግርግር ለሌባ ያመቻል አንዲሉ እነርሱ ተጠቃሚ የሚሆኑት ህዝብ ተፋቅሮ ተከባብሮ ሲኖር ሳይሆን ርስ በርሱ ሲጋጭ መተማመን አጥቶ የጎሪጥ ሲተያይ ወዘተ በመሆኑ ነገሮች ወደዛ እንዳያመሩ ብርቱ ጥንቃቄ ያሻል፡፡ከምንም በላይ ትግርኛ ተናጋሪውን ወገን ከሌላው ኢትዮጵያዊ አቆራርጠው የህውሀት ምርኮኛ ለማድረግ የሚዘሩት መርዝ ፍሬ እንዳያፈራ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ አማራ አንጂ ትግሬ አይደለሁም ድንበሬም ተከዜ ነው ማለት ራሱ የወያኔው ሕገ መንግሥት የሚደግፈው ጥያቄ በመሆኑ ነገሮች ወያኔዎች ወደሚጎትቱት አቅጣጫ ሳይሆን ህዝብ ወደሚፈልገው አቅጣጫ እንዲያመሩና ዘላቂ ሰላም ሊያስገኙ በሚያስችል መልኩ መፍትሄ አንዲያገኙ ቆራጥና የሰከነ ትግል ማካሄድ የግድ ይላል፡፡ አለበለዚያ ዳሩ ካልተከበረ መሀሉ ዳር ይሆናል እንደሚባለው የወልይት ጎንደሬነት ታሪክ ሆኖ ይቀራል፡፡ አለያም ግዜ እየጠበቀ የሚፈነዳ ፈንጅ ይሆናል፡፡
የወልቃይትን አማራነትና የድንበሩንም ተከዜነት ለማረጋገጥ የሚካሄደው ትግል ከወያኔ ጋር ብቻ አይደለም፡፡ ኦህዴድ በአዲስ አበባው ማስተር ፕላን እንደተፈተነው ሁሉ ብአዴንም በዚህ ወሳኝና ወቅታዊ ጉዳይ መፈተን አለበት፡፡ ወልቃይት አማራ ነው ትግሬ ፤  ከጎንደርና ከወሎ ወደ ትግራይ የሄደው መሬት ቋንቋን መሰረት ባደረገው የፌዴራሊዝም አከላለል ነው ወይንስ ከጥንትም የትግራይ መሬት በመሆኑ ነው፡ ለሱዳን የሚሰጠው መሬት የኢትዮጵያ ነው  ወይንስ አቶ ኃይለማሪያም እንዳሉት የጎንደር ሽፍቶች በኃይል የያዙት የሱዳን መሬት ነው፡፡  ከብአዴኖች መልስ የሚሻ ጥያቄ ፡፡

No comments:

Post a Comment