Monday 22 February 2016

ከ 1983 እስከ 2007 ዓ.ም በዐማራው ነገድ ላይ የደረሰ የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ወንጀል ጥናት ውጤት ማጠቃለያ ዘገባ! (ሞረሽ ወገኔ)

ኢትዮጵያ አገራችን እያከተመ ባለው ምዕተ-ዓመት ሁለት የተለያዩ የማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ለውጦችን አስተናግዳለች። የመጀመሪያው በ 1966 የፈነዳው አብዮትና ሶሻሊስታዊ እንቅስቃሴ ሲሆን፣ ሁለተኛው በክስተቱም ሆነ በውጤቱ እጅግ የተለየው ደግሞ ከ1983 ጀምሮ የተንሰራፋው የዘመነ መሳፍንት ተምሳሌት ወያኔ መራሹ ፓለቲካ ነው። ይህ በጎጥና በመንደረተኛነት ላይ የተመሠረተ አምባገነናዊ አገዛዝ እነሆ! ከ 25 አመታት ቆይታም በኋላ ኢትዮጵያን እያመሳት መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ኅልውናዋን፣ ሉዓላዊነቷንና አንድነቷን አናግቷል። እያናጋም ነው።
በያዝነው  ዓለም አቃፋዊነት ዘመን (ዘመነ ግሎባላዜሽን)፣ ዓለም እየጠበበችና አንድ መንደር እየሆነች መጥታለች። የአገራት ጂኦግራፊያዊና የኢኮኖሚ ክልል ሳይገድባቸው ባለሀብቶች ባሻቸው አሕጉር፣ አገርና ማናቸውም ሥፍራ መዋዕለ-ነዋያቸውን በማፍሰስ እራሳቸውን ጠቅመው ተቀባዩን አገርና ኅብረተሰብ እንዲጠቅሙ የሚበረታቱበት ውቅት ነው። ባለሙያዎች ዜግነትና ድንበር ሳያግዳቸው በሚፈለጉበት አገር ሁሉ ሙያቸውን እንዲያጋሩ በሩ በተከፈተበት ዘመን፣ ኢትዮጵያ ውስጥ የጎሳ ፓለቲካ ባሰመረው ክልል የተነሳ፣ የጋራ ደም የተከፈለባት ኢትዮጵያ የጋራ አገር ልትሆን አልቻለችም። ኢትዮጵያ ውስጥ፣ አገሪቱ የሁሉም ነገዶቿና ጎሣዎቿ አገር ሆና ሳለ፣ «የእኛና» «የእናንተ» እየተባለ በተከለለ የጎሳ አጥር፣ ሕዝቡ ተዘዋውሮ መሥራት እንዳይችል  ገደብ ተጥሎበት ይገኛል። ነገዶችና ጎሣዎቻችን ጌጦቻችን መሆናቸው ቀርቶ፣ ለመከፋፈላችንና ለአንድነታችን መፍረክረክ ምክንያት እንዲሆኑ፣ በዘረኞች ቀመር ዞሪያ እየተሽከረከሩ ይገኛሉ። የውጭ ጻህፍት ሳይቀሩ «የነገዶች ሙዚየም» ብለው ያሞካሿት ኢትዮጵያ፣ በከፋፍለህ ግዛው የፓለቲካ ጦስ የእርስ በርስ ጦርነት መሻኮቻ መድረክ ሆናለች።
በቀዝቃዛው ጦርነት ማክተሚያ ወቅት፣ ኮሙኒዝምን ለመበቀል በዛቱት ምዕራባውያን ትከሻ፣ ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር በለስ የቀናቸው የትግሬ-ወያኔዎች፣ ኢትዮጵያን ለመበታተን ሌት ተቀን እየሠሩ ለመሆናቸው ገሃድ ከሆነ ውሎ አድሯል። የኢትዮጵያን መሠረታዊና ጥንታዊ ዕሴቶች፣ የሕዝቧን ኅብረትና አብሮነት ለመናድ ሳይታክቱ ጠንክረው እየሠሩ ነው። ገና ከጽንሳቸው ጀምሮ፣ የጥፋት ዒላማቸው ያደረጉት ደግሞ የዐማራውን ማኅበረሰብ ነው። ዐማራውን ያለ ስሙ ስም ሰጥተው ፣ያለጥፋቱ ጥላሸት ቀብተው ፣ ብሔራዊ  መለያ ደማቅ ቀለሙን አደብዝዘው ፣ አኩሪ ታሪካዊ ሚናውን አኮስሰው፣ ኮንነውና አጥላልተው  ባምሳላቸው ለቀረጿቸው ጎጠኞች የጥቃት ዒላማ አድርገውታል። እነዚህ በኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ ያለፈቃዱ የተፈናጠጡ የወያኔ ዘረኛና ጠባብ ናዚዎች በውስጣቸው በተፈጠረ የበታችነትና የቅናት ስሜት የተነሳ፣ በሰነቁት ጥላቻ ይህንን ታላቅ፣ ታታሪና ለኢትዮጵያ የክፉ ቀን ዘብ የቆመንና ኢትዮጵያን እንዳገር ለማፅናት የታገለ ሕዝብ የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽመውበታል። እየፈጸሙበትም ነው።
ጥቃቅን ችግሮችን በማጋነንና ልዩነት በመፍጠር አብሮ በኖረ ሕዝብ መካከል በቀላሉ የማይጠፋ እሳት ለኩሰዋል። ለጠባብ ዓላማቸው ስኬት ሲሉ፣ የጎሣ ፓለቲካን ከሚገባው በላይ አራግበውና አጡዘው፣ ከሁሉም በላይ የኢትዮጵያ ችግሮች ሁሉ መንስዔ የዐማራው ነገድ እንደሆነ ጧት ማታ በመልፈፍ፣ ልበወለድ ታሪኮችን በመፈብረክና ዕኩይ ፕሮፖጋንዳ በመንዛት መጠነ ሰፊ የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ዘመቻ ከፍተውበታል።
ዐማራው በ18ኛው ክፍለ-ዘመን መባቻ ላይ፣ ኢትዮጵያን ሊቀራመቱ ከመጡ ቅኝ ገዢዎች መንጋጋ ሕይወቱን ገብሮ እንዳላዳናት፣ በ 21ኛ ክፍለ-ዘመን በዚችው አገር እንደባዕድና እንደወራሪ ተጨፈጨፈባት ። በተሰዋላት ኢትዮጵያ ውስጥ በግፍ ሕይዎቱን በግፈኞች ተነጠቀ። የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ወንጀል ተፈጸመበት። ዘርን መርጦና ለይቶ የወል ወንጀል ሲፈጸም፣ ይህ በዐማራው ላይ የደረሰው በአገራችን ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው መሆኑ ነው።
አብዛኛው ዐማራ፣ በኑሮው ከማንኛውም የኢትዮጵያ ነገዶች ባነሰና በከፋ የድህነት አርንቋ ውስጥ መኖሩ በግልጽ እየታየ ፤ ገዛ፣ በዘበዘ ፣አደህየን ወዘተ በማለትና የሌለበትን ኃጢያት በመደርደር፣  ለዕኩይ ዓላማቸው የፕሮፓጋንዳ ፍጆታ ተጠቅመውበታል። ዐማራ የጎጠኝነትና የጠባብነት ስሜት ከቶ ኖሮት አያውቅም። ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወገኑ ጋር ተጋብቶና ተስማምቶ የሚኖር ብቻ ሳይሆን፣ በሄደበት ቦታ ሁሉ፣ በታታሪነቱና ባለው የዳበረ ማኅበራዊ መስተጋብሩ ከማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጋር እጅና ጓንት ሆኖ የሚኖር ማኅበረሰብ መሆኑ ማንም የሚያውቀው ነው። የጎጠኞች ፀረ-ዐማራ ርካሽ ቅስቀሳና መሠረተ ቢስ ክሳቸው፣ ተከላካይ ባለማግኘቱና ለዓመታትም በመደጋገሙ፣ ሌሎች ጠባቦችን ለመቀፍቀፍና ለማነሳሳት በቅቷል። በመሆኑም ዐማራው በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ዜግነቱን፣ ጥቅሙን፣ መብቱንና ክብሩን ብቻ ሳይሆን፣ ሰብአዊነቱንና ሕይዎቱንም ጭምር ተነጥቆ፣ቀሪው የሰቀቀን ሕይዎት በመግፋት ላይ ይገኛል።
ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት፣ የዐማራው ድምፅ ለመሆንና የገጠመውን መጠነ ሠፊ ችግር ለዓለም ማኅበረሰብ ለማመላከትና ለማሳወቅ  ከተመሠረተ እነሆ ሦስት ዓመት ሊያስቆጥር ነው። በዚህ በአጭር ጊዜ ውስጥ የዐማራው ድምጽ ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ዐማራው ምን እንደተፈጸመበት፣ ምን ሊፈጸምበት እንደታቀደና ያንዣበበትን  ከፍተኛ የኅልውና አደጋ የቱን ያህል የከፋ እንደሆነ፣ እንዲገነዘብና እንዲያውቅ  የበኩሉን ጥረት አድርጓል። አንቅቷል። ሞረሽ ሊያከናውናቸው ካቀዳቸው ግቦዎቹ ውስጥ አንዱ፣ ዐማራው ላይ የሚፈጸመውን የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተከታተለ ማጋለጥና አስፈላጊው እርምጃ እንዲወሰድ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማድረግ ነው። በዚም መሠረት ሞረሽ አንዱና ቀዳሚው ተግባሩ ያደረገው፣ ወያኔ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረበት ከዚያ ክፉ ቀን ጀምሮ፣ እስከ ዛሬ በዐማራው ነገድ ላይ የተከፈተውን መጠነ ሠፊ የማፈናቀልና የዘርማጥፋት ወንጀል ለማወቅና አስፈላጊውን እርምጃ ለመውሰድ እንዲቻል በመረጃ ላይ የተመሠረተ ጥናት ማካሄድ ነው። ይህንንም እንደሚያደርግ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ማስተዋወቁ የሚታወስ ነው። ስለሆነም በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍሎች በተለይም በዐማራው ላይ የዘር ማጽዳትና የዘር ማጥፋት ወንጀሎች የተፈጸሙባቸው አካባቢዎችን  ያካተተ በተጨበጠ፣ ግልጽና አስተማማኝ መረጃዎች ላይ የተመሠረተውን ይህንን ጥናት አስጠንቶ ለራሱ የዐማራ ነገድ ተወላጆች፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶችና ለታሪክ ተመራማሪዎች የኅሊና ፍርድ አቅርቧል።
ጥናቱ የዐማራውን መጠነ ሠፊና በዝምታ ዕልቂት ለዓለም ይፋ ለማድረግ ተዘጋጅቷል። ጆሮ ያለው እንዲሰማ፣ ዓይን ያለው አጥርቶ እንዲያይ፣ ዐማራው በዚህ በጎጠኞች ዘመን የተደገሰለትን በአሉባልታ ሳይሆን፣ በተጨበጥና በሚዳሰስ መረጃ ቀርቦለታል። የዚህ ጥናት ውጤት ተነቦና ከንፈር ተመጦ እንደ አንድ የትራጄዲ ልበወለድ ለተወሰኑ ጊዜ ቆዝመው የሚተው አይደለም። ይልቁንም ማናቸውም ኢትዮጵያዊ በተለይም ዐማራው ኅብረተሰብ ከዚህ የከፋ ምንም እንደማይጠብቀው አውቆና ከራሱ በስተቀር ማንም ተገን እንደለሌው ተረድቶ፣ ለራሱ መቆም እንዳለበት እንዲገነዝብ የሚያግዝ  ሁነኛ ዋቢ ታሪካዊ መረጃ ነው። ይህንን ግድያ ያቀነባበሩ፣ ያበረታቱና ቀጥታ ወንጀሉን የፈጸሙት ጎጠኞችና ጠባቦች የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የሚጠየቁበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም። የሞረሽ ወገኔ ፍላጎትም፣ የዚህ ጥናት የመጨረሻ ግብም ወንጀለኞችን ለሕግ ማቅረብ ነው።

የጥናቱ ዐብይ ዓላማ፦ ለአለፉት 25 ዓመታት በዐማራው ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋትና የዘር ማጽዳት ወንጀል የተጨበጠ መረጃ በማሰባሰብ፣ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ በሚኖሩ ወንጀለኞች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ ሲሆን፣ የወንጀሉን ደረጃና መጠን ለኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም፣ ሰለባ ለሆነው ለዐማራው ኅብረተሰብ፣ ወንድምና እህቶቹ መርጠው ባልተወለዱበት ዘራቸው ተነቅሰውና ተፈርጀው የገጠማቸውን ሰቆቃ፣ እልቂትና ሰብአዊ ውርደት በትክክል እንዲያውቅ ማድረግ ነው። የጥናቱ ዓላማ በዝርዝር፦
■        ከ 1983 ዓ.ም ጀምሮ ያለቁና የተፈናቀሉ ዐማሮችን መጠን ለማወቅ፣ እንዲሁም የወያኔ የጎሳ ፓለቲካ በዐማራው ሕዝብ ላይ ያደረሰውን ጥፋት በግልጽ ለማሳየት፣
■        የተፈናቃዮችንና የሟቾችን ማንነት ዝርዝር መረጃ ለማጠናቀር፣
■        በዐማራው ላይ የደረሰውን የጭፍጨፋ መጠን ለማሳየት፣
■        በዐማራው ላይ እየተፈጸመ ያለውን የዘር ማጽዳት ወንጀል ቀጣይነት ያለውና፣ ሆን ተብሎ በዕቅድ እየተፈጸመ መሆኑን ለማሳየት፣
■        ዐማራውና ሌሎች የኢትዮጵያ ነገድ አባላት በወገናቸው ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍና እልቂት እንዲገነዘቡ ለማድረግ፣
■        ወንጀለኞቹንና ድርጊታቸውን ለማጋለጥና ለሕግ ለማቅረብ፣


የጥናቱ ሥልት፦ ጥናቱ በማኅበራዊ ሳይንስ ጥራታዊ (Qualitiative) አጠናን ሥልት መሠረት የተካሄደ ነው። የጥናቱ ግብዓቶች በጥንቃቄ በተዘጋጁ የተመጠኑ ጥያቄዎች ላይ ተመሥርቶ በተዘጋጁ ቃለመጠይቆች በተሰጡ መልሶች፣ የጥቃቱ ሰለባ ከሆኑ ሰዎች፣ በቃል፣ በጽሑፍ፣ በቦታና በድርጊት የተሰበሰቡ መረጃዎች ናቸው ። ቃለመጠይቆቹ የተካሄዱት በገጽና ድርጊቱ በተፈጸሙባቸው አካባቢዎች ሆኖ፣ የወንጀሉ ሰለባዎች ከሆኑትና ከቤተሰቦቻቸው ጋር ነው። ጥናቱ በተጨማሪም የሰነድ፣ የፎተግራፍና የቦታ ማስረጃዎችን አካቷል። በቃለመጠይቁ የተሳተፉት ሰዎች ምስልና ድምጽም ተቀርጿል። ለዚህ ጥናት 216 ዐማሮች የእማኝ ቃላቸውን በመስጠት በጥናቱ ውስጥ ተሳታፊ ሆነዋል(የየአካባቢው የጥናቱ ተሳታፊዎች ቁጥር ዝርዝር ዝቅ ብሎ በሚገኘው ግራፍ ላይ ተመልክቷል።)
የጥናቱን ተሳታፊዎች ለመምረጥ ስኖው ቦል (Snow Ball) የናሙና አመራረጥ ዘዴ ተግባራዊ ሆኗል። በሁሉም ቦታዎች የተካሄዱት መጠይቆችና ውይይቶች በድብቅ የተከናወኑ ናቸው።





ጥናቱ የተካሄደባቸው አካባቢዎችም፦ ሐረር፣ አርሲ፣ ቤንች ማጂ፣ ጅማ፣ ወለጋ፣ ከማሽ፣ መተከል፣
አፋር(ዐባይ ነጌስ ጎጥ) እንዲሁም ባሕርዳርና ጎንደር ከተሞች ናቸው።

No comments:

Post a Comment