Monday, 22 February 2016

በኦሮምያ ክልል የተጀመረው ሕዝባዊ ንቅናቄና የሃገራችን መጻሒ ሁኔታ! | ከኃይለገብርኤ አያሌው

 | 

በኦሮምያ ክልል የተጀመረው ሕዝባዊ ንቅናቄና የሃገራችን መጻሒ ሁኔታ! | ከኃይለገብርኤ አያሌው

Share1  662  0 
 Share3
ሃገራችን በረጅም ዘመን ታሪኳ አያሌ ግጭትና ጦርነቶችን እስተናግዳለች ። በተደጋጋሚ ሕልውናዋን ሊያጠፉት የተቃረቡትን የውጭና የውስጥ አደጋዎች ተቋቁማ ዛሬ የደረስንበት ዘመን ላይ ደርሳለች። በነዚህ ዘመናት ውስጥ የገጠሟትን ችግሮች ፤ ዘር ሃይማኖት የቋንቋ ልዩነት ሳይገድባቸው ቆራጥና አስተዋይ ልጆቿ በሕብረት በከፈሉት ወደር የለሽ ተጋድሎ ሕልውናዋን እስጠብቃ ኖራለች። ሃገራችን ከዓለም ቀድምት ከሆኑት የስልጣኔና ፈር ቀዳጅ ጥቂት ሃገራት ተርታ የሚቆጠር አኩሪ ታሪክ ያላት ፡ በምድር የከበረች በሰማይም የተመሰገነች ፤ የቅዱሳን መሸሸጊያ የነጻነት ተምሳሌት ሆና ታፍራና ተከብራ   መኖሯ እርግጥ ነው።
Oromia
ኢትዮጵያ ዙሪያዋን በከበቧት እረፍት የለሽ የቅርብና የሩቅ ጂዖ ፖለቲካዊ ስትራቴጂካዊና ታሪካዊ ጠላቶቿ ሴራ በተራዘመ የግጭት አዙሪት ውስጥ ወድቃ እንድትኖር የቀበሩት ግዜ ጠብቆ የሚፈነዳ ፈንጂ በተደጋጋሚ ጉዳት ሲያደርስብን ቆይቷል። እነዚሁ ከራሳችን ሊወርዱ የማይሹት ባላንጣዎቻችን የተንኮል ሴራ ፍላጎታቸውን  ሊያስፈጽሙ የሚችሉ ሃገር በቀል  እንደ ሕውሃት ያለ ቅጥረኛ ባንዳዎች ያልተቋረጠ ድጋፍ ሲሰጡ ቆይተዋል። በዚህም  ትላንት በቀጥታ ያልቻሉትን በገዛ ወንድሞቻችን ጀርባ ተረማምደው የሃገራችንን ሕልውና በማፍረስ ሃገሪቱን በእጅ አዙር ለመቆጣጠር ብዙ ግዜ ሞክረው ያልተሳካላቸው ፖሊሲ ይህው በ 21 ክ/ዘ ተሳክቶላቸው በባህል በሃይማኖት በጋብቻና  በዕለት ተዕለት ሕይወት ተቆራኝቶ ተስማምቶ ለዘመናት የኖረውን ሕዝባችንን በዘውግ  ፖለቲካ ተከፋፍሎ፤  ያለፈ ታሪክ ማጥ ውስጥ ጥለውን እርስ በዕርስ እንድንጠፋፋ ሲያመቻቹን ከርመዋል። ሕወሃትና ሸሪኮቹ  ሃገራችንን እየቀሙን በስደት የባዕዳን አሽከር በሃገራችንም ሁለትኛ ዜጋ ሆነን ተነጣጥለን እንድንቆም ማድረግ በመቻላቸው ብሶትና መከራችን የጋራ መሆኑ ቀርቶ ክልልን የማይሻገር በጎጥ የታጠረ የተናጥል እንዲሆን ተድርጎ ቆይቷል።
በተለይም አውሮፓውያን አፍሪካን እንደ ቅርጫ ስጋ ተከፋፍለው ባካሄዱት ሕገወጥ የጭካኔ ወረራ ድፍን አፍሪካን ተቀራምተው ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲበቁ ፤ እንቢኝ አሻፋረኝ ብለው ለቅጥሯ ዘብ ሆነው ወራሪዎችን አይቀጡ ቅጣት እየቀጡ የሃገራችንን ሕልውና ለማስጠበቅ አባቶቻችን ቢችሉም ፥ ይህ ሽንፈት ያልተዋጠላቸው  ምዕራባዊ ተስፋፊ ሃይሎች ከገዛ ልጆቿ ማህል በመለመሏቸው ባንዳና ሹንባሾች ፤ በብሔሮች መካከል ጸንቶ የኖረውን ውህዳዊ የአብሮነት ኑሮ ለመበረዝ ጨቋኝና ተጨቋኝ ፤ ቅኝ ገዥና ተገዢ የሆነ ሃገር በቀልና ብሔርን መሰረት ያደረገ አስተዳደር  እንዳለና እንደነበር  አድርገው የረጩት ፕሮፓጋንዳና ያቀዱት የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ ዘመን ተሻግሮም ቢሆን ሊሰምርላቸው ችሏል።
በዚህ ባለንበት የ21ኟው ክፍለ ዘመን ዓለም በቴክኖሎጂ መንጥቆ የመገናኛ ዘዴዎችን ባቀለለበት የህዝቦች የባህል ፤ የኢኮኖሚና የጸጥታ ጉዳዮችን  በቀላሉ ከአንዱ ወደ ሌላው ክፍለ ዓለም በሰከንድ መረጃ በሚያደርስበት ግሎባላይዜሽን በሚዘመርበት የሃሳብ የበላይነት ገኖ በወጣበት በዚህ ባለንበት ዘመን ራሱን የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ብሎ የሚጠራው ፤ ከቅኝ  ገዥዎች  መቃብር ላይ የበቀለ የጥፋትና የዘረፋ ቡድን ዘመን የሻረውን ሗላ ቀርና  በታኝ የከፋፍለህ ግዛው ፍልስፍና በሃገራችን ላይ አንብሮ  በተንኮልና በአሻጥር ሲያተራምሰን  ቆይቷል።
ይህ ከዘመኑ አስተሳሰብ የተጣላ የዕውቀት ጠር ጨካኝና አረመኔ አገዛዝ ባለፉት 25 አመታት ሃይማኖትን በሃይማኖት ፤ ብሄርን ፤ ከብሄር የሚያጋጭ ክፉ ፖለቲካ ሲያራምድ ቆይቷል። እንደዚህ ፋሽስታዊ ቡድን ቅስቀሳና ፍላጎት ምንም ሕዝባችን ወደ አጠቃላይ ግጭት ባያመራም ፤ ነገር ግን ጸንቶ የኖረውን የሕዝባችንን አብሮነት በማወክ ለጋራ ሃገራዊ አላማዎች  የጋራ ሕብረት እንዳይኖረው ማድረግ የሚያስችል መሰሪ ዕቅዱ ለረጅም ግዜ ተግባራዊ ሆኖ ቆይቷል። ዛሬም ቀጥሏል ።  ለነገም ይህን እኩይ ሴራ ነቅቶ  ማክሸፍ የማይቻል ወገን ካለ መከራውም ይረዝማል ፥ ልዩነቱም ይሰፋል ፤ ባርነቱም ፤ ይቀጥላል!!
ለዘመናት በአንድነት የኖረው ሕዝባችንን አንድነቱን አላልቶ በቅራኔ አፋጦ ባለፈ የታሪክ ጠባሳ ላይ ስንታገል ሕወሓት ግን አፓርታይዳዊ ዘረኛና ዘራፊ አገዛዙን በላያችን ጭኖ ያሻውን ሲያደርግና ሲፈጽምብን ቆይቷል።  የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት  ይህው የከፋፍለህ ግዛው ፖሊሲ እስከግዜውም ቢሆንም ተሳክቶለት ፤ አማራው ሲጠቃ ፤ ኦሮሞው ቆሞ እንዲያይ ፤ ኦሮሞው ሲጎዳ አማራው በጸጥታ ሲያልፈው ፤ እንዲሁም ክርስቲያኑ ችግር ሲገጥመው ሙስሊሙ ዝም ሲል ፤ ሙስሊሙን ጉዳት ሲገጥመው የክርስቲያኑ ጸጥታ እስከ ተወሰነ ግዜ ገዥዎችን ሲጠቅም ቆይቷል። በነዚህ ዘመናት የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት እያፈራረቀ በተለያየ አጀንዳና ግንባር የሚፈልገውን እየደፈጠጠ አገዛዙን በሕዝብና በሃገር ላይ አጽንቶ ልክ እያስገባን ይገኛል።• ።
የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የረጨው የጥላቻና የመለያየት መርዝ ነቅቶ በግዜ በማርከስ ሕዝብን ማቀራረብ የነበረባቸው የአማራውና የኦሮሞ  ምሁራን መካከል ተካሮ የቆየው ልዩነት ለዘረኛው አገዛዝ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠሩም በላይ ሁለት ግንባር በአንዴ ከማጥቃት ተቆጥቦ ስልታዊና ታክቲካዊ ሽግሽግ በማድረግ የግዜና የሁኔታዎችን አመቺነት እያሰላ ፤ በተከታታይ እንደታየው የተነሳበትን ሕዝባዊ ተቃውሞና የአመጽ እንቅስቃሴ ለማዳፈን አንዱን በሌላው ላይ እየቀሰቀሰ ከጎኑ ለማሰለፍ ሲችልና ሲያደርግ ቆይቷል ፤ አሁንም ያንኑ ስልቱን በመቀመር በከፋና ምንአልባትም ሃገሪቷን ሊበታትን የሚችል የዘር ግጭት ለመቅስቀስ እየተንቅሳቅስ ለመሆኑ ከሚወጡት መረጃዎች መረዳት ይቻላል።
በተለይም ባልፉት አራት አስዕርተ አመታት ውስጥ በአንዳንድ የኦሮሞ ምሁራን ተላላነት በጥቂት ሆድ አድሮችና በእንዳንድ ጽንፈኞች ቅንብር እና በትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት አዝማችነት በተሳሳተ ፕሮፓጋንዳና በተንሸዋረረ የማንነት ውዥንብር  የኦሮሞን ሕዝብ ከኢትዮጵያዊነት ማዕከል ለመነጠል ያልተቋረጠ ሴራ ሲራመድ ቆይቷል። የዚህም ሴራ ዋና አላማ  እንዱ  የኦሮሞ ማሕበረሰብ ዙሪያውን ካሉት ሌሎች ብሄሮችና ከእንድነት ሃይሎች ጋር ያልተቋረጥ ቅራኔ ውስጥ  ከቶ ፋታ በመንሳት በተፈጥሮ ሃብት የበለጸገውን የኦሮምያ ምድር በምስለኔዎቹ ተረማምዶ ለዘመናት ትቆጣጥሮ ያለ ከልካይ ሲመዘብር ለመኖር ካለው ሕልም የተንሳ ነው።
በዚህም የሴራ ቅመራ ባለፉት አመታት እንደሆነውና እንደታየው ፥ በተለይ የአማራ ተወላጆችን ከኦሮሞ ማህበረሰብ ፍላጎትና ፈቃድ ውጪ የጥላቻ ቅስቀሳ በማድረግ በካድሬዎቹ አዝማችነት ተወልደው ካደጉበት ፤ ለፍተው ያፈሩትን ሃብትና ንብረት እየቀሙ ከክልሉ በገፍ እንዲባረሩ ሁን ተብሎ  በትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት በተቀነባበረ ሴራ በብዙ ሺህ በሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ላይ የጅምላ ግድያና ፥ የዘር ማጥፋት ወንጀል በኦሮሞ ነገድ ስም ሲፈጸም   ቆይቷል። ዛሬም ይህው ሴራ  ቀጥሏል ፥ ነገም በጋራ ካልቆምን ካሁን ቀደሙም የከፋ የእርስ በዕርስ መተላለቅ ሊከሰት እንደሚችል ለመረዳት ነብይ መሆን አይጠይቅ።
ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ነው ፤ ኢትዮጵያም የኦሮሞ ናት! ይህን ሊፍቅና ሊያስቀር የሚችል ምንም ውሃ የሚቋጥር ምክንያት የለም። የኦሮሞ ልጆች ለኢትዮጵያ የግዛት አንድነትና ለወሰኗ ክብርና ለሉዓላዊነቷ ወደር የሌለው መስውዕትነት ሲከፍሉ ኖረዋል። ይህንን የክብርና የኩራት ታሪክ ንደው የኦሮሞ ብሄር ተወላጆችን ከሃገራዊውና ከአህጉራዊው ተምሳሌታዊ ሕዝብነት አርቀው የባርነትንና የተገዥነትን የሃሰት ማቅ ሊያለብሱት በጠባብ ብሔረተኝነትና በጨለምተኛ የስሜት ፖለቲካቸው እሳት ውስጥ ትውልዱን ሊጥሉት የሚራወጡ ጽንፈኞች የሚያራምዱት ኦሮሚያ ለኦሮሞ የሚል ከፋፋይና አፍራሽ እንቅስቃሴ ለማንም የማይጠቅም ዘመኑን ያልዋጀ መፈክር ነው።
እርግጥ ነው ፥ መላው ሕዝባችን በየግዜው በተፈራረቁት መንግስታት ሲበዘበዝና ሲጨቆን የመኖሩን ሃቅ ሊዘነጋ የማይችልና ጠባሳውም ያልጠፋ ነው። ነገርግን ትላንትም ሆነ ዛሬ ጥቂት መሳፍንት ባላባትና ኤሊቶች ፥ ከአንዱ ወይ ከሌላው ብሄር በቁጥር ልቀውና የስልጣን ወንበር ይዘው ቆይተው ሊሆን ይችላል። አንድ ብሄረሰብ አጠቃላይ ተጠቃሚና የበላይ ሌላው ጎሳና ነገድ ተገዥ የሆነበት የመንግስት መዋቅር ፥  አልነበረም  ፥ የለምም ።
ምናልባት ዛሬ የትግሬዎች የበላይነት አለ የሚል  ክርክር ሊነሳ ይችላል። እርግጥ ነው በሃገራችን ታሪክ ታይቶም ሆነ ተሰምቶ በማይታወቅ ደረጃ የሃገሪቱን የስልጣን ፥ የኢኮኖሚ ፥ ወታደራዊና ፥ ማህበራዊ ሴክተሮች ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ በትግራይ ተወላጆች ተይዞ ለመገኘቱ አይን የሚያየው ሃቅ ነው።  ይህም ሆኖ ግን በስመ ትግሬነት ሁሉንም የብሄሩን ተወላጆች ከስልጣኑም ከዘረፋውም እንጥፍጣፊው ያልደረሳቸውን ጨምሮ በአንድ  ቅርጫት ከቶ የመፈረጁ አተያይ ተገቢም አስፈላጊም አይሆንም። ዛሬ ሕዝባችንን አለያይቶ የዘረፋ አገዛዙን ያነበረው የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ፥ ለዚህ አሁን ለደረሰበት ልዕልና ያበቃውን የትግራይ አርሶ አደር ክዶ ብዙ ሺዎች የከፈሉትን የሕይወትና የአካል መስዋዕተነት  ረስቶ  ቁንጮ መሪዎቹና አጫፋሪዎቻቸው በሃብት ላይ ሃብት ሲያካብቱ ፥ የራሳችውን መደብ ለይተው በቅንጡ ቪላ ሲምነሸነሹ ያስተዋልው የትግራይ ሕዝብ አፓርታይድ መንደር ሲል ብሶቱን መግለጹ ይታወሳል።
ዛሬ ለደረስንበ ሃገራዊ ውድቀት አያሌ ምክንያቶች መጥቀስ ይቻላል ነገር ግን እንደ አንድ የዚህ የጥበብና የግሎባልይዜሽን አለም ውስጥ እንዳለ እንድ ሕብረተሰብ ዛሬም በዛው እንዲያውም በባሰ ደረጃ ተዳክመን ለመገኘታችን ተጠያቂው ማን ነው። ሃገራችንን በብረት ክንዱ ደቁሶ የከፋፍልህ ግዛው ያረጀና ያፈጀ ሃገር በታኝና ትውልድ እውዳሚ የጥላቻና የጎሳ አስተሳስብ እየገዛ ያለው የህውሃት ቡድን በዋናነት ሊጠቀስ የሚችል ቢሆንም ፤ ይህ እኩይ ሴራ  በአንድም ሆን በሌላ ምክንያት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ተቀብለን ፤ ዘውገኛ   አመለካከትን ያራባንው ፤  በጠባብና ግትር አመለካክት ተካርን ለዘመናት ተዋልዶና ትጋብቶ በፍቅርና በአብሮነት የኖረውን ሕዝባችንን ጠላቶቻችን  ዘር መሰረት ያደረገ ግንብ ሲያጥሩልን ድንጋይ ያቀብልነው ፤ አጥፊነቱን እያወቅን በዝምታ ያለፍንው ፤ ጊዚያዊ ጥቅምና ጎጠኘነት አይሎብን ጸጥታን የመረጥንው ፤ ሁላችንም የተጠያቂንቱን ድርሻ ማንሳት ይኖርብናል ።
ታሪክ ሠሪው ሠፊው ሕዝብ ነው አዋቂዎች እንዲሉ ፤ የትላንት ገናናነታችን የዛሬው ውድቀታችን ተመስጋኙም ሆነ ተወቃሹ በዘምኑ ያለ ትውልድ  ነው። ቀደምት አባቶቻችን ዘርና ሃይማኖት ቋንቋና ነገድ ሳይሉ ደማቸውን አፍስሰው አጥንታቸውን ከስክሰው ቢያንስ በዓለም አደባባይ አንገታችንን ቀና አድርገን እንድንሄድ ታላቅ የስነልቦና ውርስ ትተውልን አልፈዋል።
ዛሬም ያለነው ትውልዶች ከቀደሙት አባቶቻችን መልካሙንና በጎውን ባህልና ፥ እሴት ጠብቀን አሮጌውን ጥለን እንደ ግዜያችን ዘመን የዋጀው ህይወት እንዲኖረን ፤ ለመብትና ነጻነታችን ዋጋ ሰጥተን ራሳችንን አስከብረን ሌሎችንም አክብረን ለመኖር የሚያስችል አስተዳደራዊ ስርዕት በሃገራችን እንዲኖር ፤ አሮጌ አስተሳሰቦችንና የጭቆና መዋቅሮችን እጅ ለእጅ ተያየዘን አፍርሰን የሕዝቦችን መብት የሚያከብር መንግስታዊ ስርዓት ልንመሰርት የሚያስችለንን ትግል በጋራ ልናደርግ ይገባል ።
በአሁኑ ወቅት ሃግራችንን የገጠማት የህልውና አደጋ ከምን ግዜውም የከፋ ሆኖ ይታያል ። የሕወሃት መራሹ ዘረኛና አፓርታይዳዊ አገዛዝ ባለፉት ሁለት አስዕርተ ዓመታት ሲከተለው በቆየው የጥቂት ወገኖችን ፍላጎት ማዕከል ያደረገ የአገዛዝ መዋቅርና የኢኮኖሚ ፖሊሲ የፈጠረው የጭቆናና የችጋር ወጀብ ሃገራችንንና ሕዝባችንን ውድቀት አፋፍ አድርሶዓታል። ይህ ሃገራዊ አደጋ እንዳይከሰት አስቀድመው ድምጻቸውን ያሰሙ የፖለቲካ መሪዎች  የኢኮኖሚ ባለሙያዎችና አክቲቪስቶች የተለያየ ስንካላ ምክንያትና የፈጠራ ወንጀል እየከሰሰ ከሃገራዊ ጉዳይ እንዲገለሉ ሲያደርግ ቆይቷል።
ሕወሃት ላለፉት 25 አመታት ቁልፍ የስልጣን ቦታዎችን ያለተቀናቃኝ ይዞ በመቆየቱ በሕዝባችን ላይ የፈለገውን ሲያደርግ ሊገድበው የሚችል ሳይኖር ቆይቷል። የዚህ የግፍና የጭካኔ ሰለባ የሆነው መላው ህዝባችንን በየግዜው ከማሃሉ ብሶቱን ብሶቴ ብለው በአደባባይ የታገሉትን ፖለቲከኞችን ጋዜጠኞችና የመብት ተከራካሪዎች ሲገልና ሲያስር የቀሩትንም ያለፍላጎታቸው ሃገር ለቀው እንዲሰደዱ አድርጓል።
ሕዝባችን ሕወሃት ባነበረበት አስከፊ የድህነት ሕይወት የሚካሄድበትን ጭቆና በጋራ መከላከያ እንዳይቻል በእለታዊ ኑሮው እንዲጠመድ ሁን ተብሎ ከመደረጉም በላይ አንዳንዴም ገንፍሎ ሲወጣ የተወሰደበት ምህረት የለሽ ጭፍጨፋ አንገቱን ደፍቶ እንዲኖር አስገድዶት ቆይቷል።  የአገዛዙን ግፈኛ እርምጃ በትግዕስት ችሎና በፍርሃት ተሽብቦ መቀመጡ ይበልጥ ልባቸው እንዲደነድን የሆኑት የህወሃት መሪዎች የከተማውን ሕዝብ በግፍና በገፍ አፈናቅለው ራሳቸው ለፈጠሯቸው የጠፍ ጨረቃ ከበርቴዎች አከፋፍለዋል። በከተማ የጀመሩትን  የመሬት ዝርፊያና ቅርምት  አልበቃ ብሎዐቸው የገጠሩን አርሶ አደር ያለ ተመጣጣኝ ካሳ ከመሬቱ እያፈናቀሉ ለድህነትና ለጎዳና አዳሪነት አድርገውታል።
በኦሮሚያ ከአመት በፊት ይህንን ግፍና በደል ያስተዋሉ የምስኪን ገበሬዎች ዋይታና እንባ ያስቆጫቸው ተማሪዎች በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለመቃወም አደባባይ በወጡ ተማሪዎች ላይ እብሪተኛው የሕወሃት አገዛዝ የለመደውን ጭፍጨፋ በማካሄድ ተቃውሞውን ለማርገብ የቻለ መስሎት ቆይቷል
ብሶት ጭቆናና ፥ የመብት ረገጣ እስካለ ድረስ ትግል መኖሩ እይቀርም ። በኦሮምያ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን መሰረት በማድረግ ዳግም ሌሎች በደሎች ገፊ ምክንያት ታክሎበት የፈነዳው አመጽ ከመጀመሪያው በይዘትም በመጠንም ሆነ  በአይነት የተለየ ከመሆንም በላይ ሕወሃትን በጣም የተገዳደረ ፥ ተምሳሌትነቱ ለመላው የሃገራችን ሕዝቦች የሆነ ፥ የጸረ አፈና ትግልን መረብ በጣጥሶ ፤ ሕዝባዊ እንቢተኝነትን ያሳየ ፥ ጠንካራ የለውጥ ሃይል የታየበት ፥ የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት  መግደል እስከ ቻለ ድረስ ለመሞት የቆረጠ የማይፈራ ትውልድ በየአደባባዩ ለፍትህ የተሰዋበት ፥ ወጣት ህጻን አዋቂው በጋራ በሰው በላው የወያኔ አጋዓዚ ወታደሮች  አፈሙዛቸው ስር በድፍረት በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞዎች ሲያሰማ በየማህበራዊ ሚድያዎች ተመልክተናል ።
በኦሮምያ በተለያዩ ቦታዎች ላለፉት ተከታታ ወራት ሲካሄድ የቆየውና አሁንም እንደቀጠለ ያለው ሕዝባዊ ትግል ከዚህ ሁሉ መስዋዕትነት በሗላ እንዳይቀለበስ የፖለቲካ ሃይሎች ና ሲቪክ ተቋማት በመሰብሰብ ፥ ከዘውገኝነት ከፍ ያለ ሃገራዊነት የተላበስ ፤ በፋሽስታዊው የሕወሃት አገዛዝ የተማረረውን መላውን ሕዝባችንን ያሳተፈ የተቀናጀና ፥ በስልት የታጀበ ሕዝባዊ ትግሉ እንዲፋፋምና ለውጤት እንዲበቃ አመራር ለመስጠት በሚያስችላቸው ደረጃ ልዩነታቸውን ወደ ጎን በማድረግ በዚህ ቀውጢ ወቅት ለሕዝብ ያላቸውን አጋርነትን ማሳየት ይጠበቅባቸዋል።
ይህ በኦሮምያ ክልል ያሉ ትንታግ ወጣቶች የተጀመረው መሬት አንቀጥቅጥ የሰላማዊ ትግል ሕዝባዊ ንቅናቄ የሃገራችንን መጻሒ እድል ሊወስን የሚችል እንቅስቃሴ በመሆኑ ፤ ወደ ሌሎችም ክልሎች ተዳርሶ በእንድ የጋራ አጀንዳና መፈክር ስር ታጅቦ ለስር ነቀል ለውጥ ትግሉን ለማብቃት ሁሉም ወገን በየአካባቢው መንቀሳቀስ ይኖርበታል። ህዝባችን የወያኔ አገዛዝ ሰልችቶታል ፥ ከጥቂት የዘረፋው ተቋዳሾች ውጪ ይህንን መንግስት እንዲለወጥ የማይፈልግ ወገን የለም ።ይህንን የሚሊዮኖች የጋራ ብሶት አንቀሳቅሶ ወደ ሕዝባዊ እንቢተኝነት ለመለወጥ የሁሉም ወገን የጋራ ጥረትን ይጠይቃል። ይህም ሲባል ለጥቂት የፖለቲካ ሃይሎች ብቻ የሚተው ሳይሆን ሁሉም ያገባኛል የሚል ዜጋ በያለብት በሚችለውና ባለው እቅም ተሳትፎ የማድርግን ሃላፊንትን በመወጣት የተጀመርው ሕዝባዊ እንቢተኝነት ከፍ ወዳለ ደረጃ ለማድረስ የሁኑንም ወገን ጥረት ይጠይቃ ።
እግዚያብሔር ኢትዮጵያን ይባርክል ! !

No comments:

Post a Comment