በኢትዮጵያ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ማለት፤ የአገሪቱ የህግ ማስፈጸሚያ የመጨረሻው ችሎት ነው። ከዚህም በተጨማሪ፤ የአገሪቱ ፕሬዘዳንትም ሆነ ጠቅላይ ሚንስትር እንዲሁም የፓርላማ አባላት ስራቸውን ከመጀመራቸው በፊት፤ ቃለ መሃላ የሚያስፈጽመው የዚህ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት መሆናቸው ይታወቃል። የህገ መንግስት ወይም የህግ ትርጉም የሚሰጠው የመጨረሻ አካል ነው – ጠቅላይ ፍርድ ቤት። ከዚህ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞች በላይ ደግሞ፤ ፕሬዘዳንታቸው አለ። እስከቅርብ ግዜ ድረስ ፕሬዘዳንቱ አቶ ተገኔ ጌታነህ ነበር። እናም በቅርቡ “ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዘዳንት አቶ ተገኔ ጌታነህ፤ ስልጣኑን በገዛ ፍቃዱ ለቀቀ” ሲባል፤ እንደማንኛውም ዜና ሰምተን ዝም የምንለው ሊሆን አይገባም።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዘዳንት ወይም ቃልአቀባዮች መግለጫ ባለመስጠታቸው የተፈጠረ ክፍተት አለ። ይህን ክፍተት በመጠቀም እኛም የራሳችንን መላ ምት እንሰጣለን። ከዚያ በፊት ግን ስለዳኛ ተገኔ የየራሱን ትንሽ ትንሽ ማለቱ አይቀርም። እኔ ከትንሽም ባነሰ መልኩ… በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ ችሎት – የቀኝ ዳኛ በነበረበት ወቅት ነው፤ ከጥቂት በታች በጥቂቱም ቢሆን ሰብዕናውን ለማወቅ የቻልኩት።
ዳዊት ከበደ ወየሳ (አትላንታ)
በፐሬስ ክስ ጉዳይ ስከሰስ… ለመጀመሪያ ግዜ የቀረብኩት፤ ዳኛ ተገኔ ጌታነህ ቀኝ ረዳት በነበረበት 1ኛ ችሎት ነበር። ከሁሉም የከፍተኛ ፍርድ ቤት፤ 1ኛ ችሎት ትንሽ ቀለል ያለ ነበር። ለንፅፅር እንዲረዳን ከጎኑ ወዳለው 2ኛ ችሎት ልውሰዳቹህ።
2ኛ ችሎት ውስጥ የግራ እና ቀኝ ዳኞች ቢኖሩም፤ ጎልቶ የሚታወቀው – ሃጎስ ወልዱ የሚባለው ከሰይጣን ቁራጭ የተሰራ የሚመስለው ቀይ ሰውዬ ነው። በተለይ ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ እስረኞች ካጋጠመው፤ በቁጣ እና በስድብ ያንቀረቅባቸዋል። እነፕሮ/ር አስራት ወልደየስ፣ እነዶ/ር ታዬ ወልደሰማያት፣ ታምራት ላይኔ እና በሌሎች ታዋቂ ሰዎች ላይ ምንም ቅም ሳይለው ስድብ አቅምሶ፤ ፍርዱን በፖለቲካ ጭቃ ለውሶ ፈርዶባቸዋል።
በደርግ ዘመን የአዲስ አበባ ከተማ ዳኛ የነበረው ግለሰብ፤ ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሲገባ… በአንድ ግዜ ተስፈንጥሮ የፌዴራሉ ፍ/ቤት መሃል ዳኛ እስከመሆን የደረሰው፤ በችሎታ ሳይሆን በፖለቲካ ሹመት በመሆኑ አብረው የሚሰሩት ጭምር ይፈሩታል። ችሎቱ በታጠቁ ፖሊሶች የሚጠበቅ ቢሆንም፤ ዳኛ ሃጎስ ወልዱ ግን የራሱን ሽጉጥ ታጥቆ ነበር – ችሎት የሚሰየመው። በዚያ ላይ ስድብ እና ጩኸቱ አይጣል ነው። ከድሮ ጋዜጠኞች መካከል አበራ ወጊ፣ አክሊሉ ታደሰ፣ ተፈራ አስማረ፣ ዘገየ ሃይሌ፣ እስክንድር ነጋ እና ሲሳይ አጌና ላይ ያለምንም ግርግር እስር እንደፈረደባቸው አስታውሳለሁ።
በ2ኛ ችሎት ከታዩት ክሶቹ መካከል አበራ ወጊ በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ጦርነት ሊጀመር መሆኑን በመዘገቡ፣ አክሊሉ በሰሜን ሸዋ ስለነበረው ወታደራዊ እንቅቃሴ በመጻፉ፣ እክንድር የኤርትራውን ፕሬዘዳንት በካርቱን እባብ አስመስሎ በመሳሉ “የፕሬዘዳንቱን ክብር ነክተሃል” ተብሎ… ብቻ በትንሽ እና በትንሹ ሰበብ ሁሉ ዳኛ ሃጎስ ወልዱ የስርአቱ ‘አፋሽ አጎንባሽ’ ሆኖ ንጹሃንን በእስር ቀጥቷል። እናም የ2ኛ ችሎቱን ሃጎስ ወልዱ የሚያውቅ ሰው… እሱ ፊት አለመቅረቡ በራሱ ደስ ያሰኘዋል።
በመጨረሻም በዚህች ቀልድ መሰል የፍርድ ቤት ገጠመኝ ሁለተኛ ችሎትን እንሰናበት። አንድ ተከሳሽ በችሎት ቆሞ ዳኛው ሃሳቡን እንዲረዱለት በተደጋጋሚ “ክቡር ፍርድ ቤት! ክቡር ፍርድ ቤት!” እያለ አቤቱታውን ያሰማል፡፡
በዚህ የተናደደው ዳኛ ሃጎስ ወልዱ፤ “አስሬ ክቡር ፍርድ ቤት! ክቡር ፍርድ ቤት አትበል።” ይለዋል።
ተከሳሽ አጋጣሚውን በመጠቀም፤ “ክቡርነትዎ… ክቡር ዳኛ!” ብሎ ይጀምራል። በዚህ ግዜ ዳኛ ሃጎስ ወልዱ ተናዶ፤ “አንተ ሰውዬ ተወኝ!” ሲለው ተከሳሹ ደንግጦ፤ “ወይ እግዚአብሄር?!” ይላል። በመጨረሻ ዳኛ ሃጎስ በንዴት፤ “ይሄ ፍርድ ቤት እንጂ ቤተክርስቲያን አይደለም። እግዚአብሄር እዚህ የለም!” ብሎት አረፈ – እየተባለ፤ በቀልድ እየተዋዛ ብዙ ግዜ ይነገር ነበር።
የኔም የመጀመሪያ ክስ ሃጎስ ወልዱ ጋር ባለመሆኑ፤ ‘እንኳን ደስ ያለህ’ ያሉኝ ጋዜጠኞች አልታጡም። በነገራችን ላይ የሃጎስ ወልዱን ቤት ሰዎች አቃጥለውበታል። (የተናደዱበት ሰዎች እንዳደረጉት ይወራል)። ይህ ግን ለተሻለ ደረጃ አሳጨውና ወደ ጠቅላይ ፍርድ ተዛወረ። ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ብዙ አልቆየም፤ እዚያ ካሉት ሰዎች ጋር አብሮ መስራት አልቻለም። በመሆኑም ሁሉንም ዳኞች ከማባረር እሱን በጡረታ አሰናበቱት። ከአገር ከወጣሁ በኋላ ይህ ሰው መሞቱን ሰምቼ፤ ‘በቃ ያ ሁሉ ነገር፤ ለዚሁ ነው?’ ብዬ ያልኩበት አጋጣሚም ነበር። “ሙት ወቃሽ” እንዳንባል፤ ሃጎስን 2ኛ ችሎት ትተን ወደ አንደኛ ችሎት እንመለሳለን። ከዚያ በፊት ግን ዳኛ ሃጎስ ወልዱ ችሎት ያጋጠመ አንድ ቀልድ
1ኛ ችሎት ውስጥ በቀኝ በኩል የሚታደመው፤ ዳኛ ተገኔ ጌታነህ ምን አይነት የፖለቲካ አቋም እንዳለው ባላውቅም፤ ችሎት ላይ ግን ረጋ ያለ ሰው ይመስላል። ቢያንስ ሲቆጣ ወይም ሲሳደብ አይቼው አላውቅም። እርግጥ ነው። በስንት ንጹሃን ሰዎች ላይ ያለአግባብ እንደፈረደ ወይም ስንት ንጹሃንን ነጻ እንዳወጣ ላናውቅ እንችላለን። ሆኖም በጋዜጠኞች ላይ ጠንከር ያለ ፍርድ ሲጠየቅባቸው፤ “ይሄማ ፕሬሱን ማሸማቀቅ ነው” ብሎ በችሎት ውስጥ የተናገረ ሰው ነው። የዛሬ 15 አመት ሌሎች ችሎቶች (በዚያን ዘመን ገንዘብ) ሃያ እና ሰላሳ ሺህ ብር ሲያስከፍሉን፤ 1ኛ ችሎት ግን የ500 ወይም አንድ ሺህ ብር ዋስትና ከፍለን እንድንወጣ ያደርግ ነበር። እናም በሃሳብ አንደኛ ችሎት ውስጥ ስንታደም፤ የክስ መዝገቡ ላይ ማስታወሻ መጻፍ የሚያዘወትረው፣ ቀኝ ዳኛ ተገኔ ጌታነህ በሃሳባችን ውልብ ማለቱ አይቀርም።
እኔ ለመጀመሪያ ግዜ 1ኛ ችሎት ስቀርብ፤ እልህና ጉርምስናው ተቀላቅሎ ፍርድ ቤቱን በመድፈር ሊያስቀጣኝ የሚችል ድርጊት ፈጽሜ፤ በተግሳጽ የታለፍኩት እነተገኔ ጌታነህ ፊት ስለቀረብኩ ይመስለኛል። በወቅቱ የተከሳሽ ሳጥን ውስጥ ሆኜ ሳለ፤ “የተከሰስኩበት የፕሬስ ጉዳይ ወንጀል ስላልሆነ፤ የክስ ወረቀቱን አልቀበልም” በማለት ከተላላኪው ጋር ስከራከር፤ የተከሳሽ ሳጥን ጋር ወርወር ሲያደርግልኝ፤ የክስ ወረቀቷ ተንሸራትታ መሬት ትወድቃለች።
የክሱ ወረቀት የወደቀው በክርክር መሃል ስለነበር፤ ወረቀቱን እኔ የወረወርኩት ነበር የሚመስለው። ይዞኝ ከቀረበው ፌዴራል ፖሊስ ጀምሮ እስከ መሃል ዳኛው ድረስ፤ በድንገት ሁሉም ነገር ጸጥ አሉ። (ከዚህ በኋላ የሆነውን መዘርዘር የወጋችንን ደረጃ ዝቅ ስለሚያደገው እንለፈው) ይህን ግድፈት የፈጸምኩት ዳኛ ሃጎስ ወልዱ በሚገኝበት 2ኛ ችሎት ውስጥ ቢሆን ኖሮ፤ እንኳንስ በተግሳጽ ልታለፍ ቀርቶ “ሳንጃ ባፈሙዝ” ገብቶ አሳሬን ልቆጥር እችል ነበር።
ከአገሬ ከወጣሁ በኋላ፤ የቀኙ ዳኛ ተገኔ ጌታነህም የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን እንደተቀላቀለ ሰማን። ብዙም ሳይቆይ የጠቅላዩ ፕሬዘዳንት ሆነ። በስልጣን ዘመኑ ሟቹን ጠ/ሚንስትር መለስ ዜናዊ እና የአሁኑን ጠ/ሚንስትር ስልጣን ሲረከቡ፤ ቃለ መሃላ አስፈጽሟቸዋል። በዚህ ላይ እያለን ነው እንግዲህ… ፕሬዘዳንት ተገኔ ጌታነህ -የአገሪቱን ከፍተኛ ስልጣን በገዛ ፈቃዳቸው ለቀቀ… የሚለውን ዜና የሰማነ።
የሰው ልጅ ከፊቱ ልዩ ልዩ ፈተናዎች ሲያጋጥሙት፤ ለራሱ መላ መምታቱ የሚከፋ አይደለም። አሁንም ዳኛ ተገኔ ጌታነህ ስልጣኑን ሲለቅ፤ “ለምን?” ብለን የመጠየቅ ሰብአዊ የማወቅ ጉጉት ያድርብናል።
በመግቢያችን ላይ እንደገለጽነው… የአገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣን የፕሬዘዳንትነት መንበራቸውን ሲለቁ የተሰጠ መግለጫ ስለሌለ አጋጣሚውን በመጠቀም፤ የራሳችንን መላምት ልናቀርብ እንችላለን።
የመላምታችን መነሻ የሚሆነው አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ነባራዊ ሁኔታ ነው። ህዝቡ ከላይ ጀምሮ እስከታች ድረስ እንደሸረሪት ድር በተተበተበ የሸፍጥ እና የጉልበተኞች አገዛዝ ስር ወድቋል። እንዲህ አይነቱ አገዛዝ፤ ህግ እና ደንብ ለሱ እስከጠቀሙት ድረስ ብቻ ነው የሚገለገልባቸው። ከዚያም አልፎ የዜጎችን ነጻነት ለማፈን፤ በህግ ሽፋን አደናቃፊ ጉድጓዶች ይቆፍራል። ህግ አውጪውም ሆነ አስፈጻሚው አንድ የፖለቲካ አካል በመሆኑ፤ ያሻውን ይፈጽማል ያስፈጽማል። እንዲህ አይነቱ አካሄድ ሁሉንም ዜጋ እኩል ሊያስደስተው ስለማይችል፤ በተለይ ለህሊናቸው ተገዢ የሆኑ ሰዎች ስርአቱን በመክዳት ሰላማዊ ኑሯቸውን ይመርጣሉ።
አሁን በኢትዮጵያ ያለው መንግስት አፋኝ ስርአት በመሆኑ፤ የህዝብ አጋር የሆኑ… ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ እና ሃይማኖት መሪዎች ቁጥር ጠላቶቹ ናቸው። እነዚህ ሁሉ “አሸባሪ” ተብለው እድሜ ልካቸውን በእስር ቤት ቢማቅቁ፣ ቤተሰባቸው ቢበተን፤ የሚበሉትና የሚይርጡት ቢያጡ የስርአቱ አዳማቂዎች ደንታቸው አይደለም። ህሊና ያላቸው ሰዎች ግን ይህንን ተሸክመው ለመሄድ አቅም ያንሳቸዋል። እናም አንድ በአንድ ይህን ስርአት ይከዱታል።
እንደነጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና ሌሎችም ድረስ፤ የታሰሩት በ’ርግጥም በአሸባሪነት መሆኑን ለማሳመን፤ ከኢህአዴግ ጽ/ቤት ጀምሮ እስከ እስከፓርላማ አባላት – ከዚያም ታቹን ለግልገል ካድሬዎች ጭምር የውሸት ታሪክ ይነገራቸዋል። እነሱም ውሸት መሆኑን እያወቁ ‘በክርስቶስ ነኝ’ ከሚለው ጠቅላይ ሚንስትር ጀምሮ ሌሎች ሚንስትሮች የተሳተፉበት የቅጥፈት ዘመቻ ሲያከናውኑ ይሰነብታሉ። ይህን ለሚያስፈጽሙላቸው የደህንነት፣ የፖሊስ እና የአቃቤ ህግ ሰዎች ገንዘብ በቁና ይሰፍሩላቸዋል። ህዝቡን ሰጥ ለጥ ለማድረግ እንዲቻል እንደፌዴራል ፖሊስ አይነት፤ ህሊና ቢስ ሰዎችን ያሰማራሉ።
ፌዴራሎችም በጭካኔ ለመደብደብ እና ለመግደል በመጀመሪያው ረድፍ ላይ ሆነው፤ በደም ጥማት ይክለፈለፋሉ። ጭካኔያቸውን ለማሳየት እንደቀልድ ተደርጎ የሚወራ ነገር አለ። የአድማ በታኝ ሃላፊው ፌዴራሎቹን ይሰበስብና በቅርቡ የሚነሱትን አመጾች በእሳት አደጋ ውሃ ጭምር ለመበተን ዝግጅቱ አልቋል። ስለዚህ ጥይት ከማባከን ይልቅ በውሃ እንበትናቸዋለን። እያለ ካብራራ በኋላ፤ የፌዴራል ፖሊሶቹ ጥያቄ ካላቸው እንዲጠይቁ ይፈቅድላቸዋል። በዚህ ግዜ አንዱ ፌዴራል ፖሊስ ብድግ ብሎ እንዲህ አለ።
“ሃሳቡ ጥሩ ነው። ውሃው ግን የፈላ ቢሆን የተሻለ ውጤት እናገኛለን።” ሲል ሌሎች የፌዴራል ፖሊስ አባላት ሃሳቡን በጭብጨባ ደግፈው ሲያበቁ፤ “የፈላ ውሃ ከሌለ አሲድ ብንጨምርበትስ?” እያሉ ሃሳቡን አዳበሩት እየተባለ ይቀለዳል። እንግዲህ ስርአቱ በዚህ አይነት ጨካኝ ሰዎች የተገነባ ነው። የስርአቱ ደጋፊዎች የተባሉትን የሚያደርጉ፣ የተሰጣቸውን የሚያነቡ ለመሆናቸው ምንም ጥርጥር የለውም። የፌዴራል ፖሊሶች ብቻ ሳይሆኑ፤ የፌዴራሉ አቃቤ ህጎችና ዳኞች ጭምር አይናቸውን በጨው ታጥበው፤ ንጹሃን ሰዎች ላይ ፍርድ ሲሰጡ ይስተዋላል።
ለምሳሌ የአንድነት ፓርቲ አመራር የነበረው ሃብታሙ አያሌው፤ በሃሰት የአሸባሪነት ክስ ተመስርቶበት፣ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት “አሸባሪ” ተብሎ፤ እስር ተፈርዶበት ከቆየ በኋላ፤ ለጠቅላይ ፍርድ ቤቱ “ይግባኝ” ብሎ ነጻ ወጥቷል። ሌሎችም የነሃብታሙን ፈለግ ተከትለው “ይግባኝ” በማለት ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ነጻ ሊያወጣቸው ይችል ይሆናል። ይህ አካሄድ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱን እና ጠቅላይ ሚንስትሩን እንደሚያቃቅር ግልጽ ነው። ጫናው እየበዛባቸው ሲሄድ የባለስልጣናቱ ምርጫ፤ አንድም ማጎብደድ ወይም ስርአቱን መክዳት ሊህን ይችላል። የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዘዳንት “በገዛ ፈቃድ የመልቀቅ ውሳኔ” የመነጨው፤ አንድም አጎብዳጅነትን መሸከም የማይችል ትከሻ ባለመኖሩ መሆኑ ግልጽ ነው።
እዚህ ላይ ሌላም ምሳሌ ጠቅሰን እንለፍ። በቅርቡ የአድማ በታኝ ሃላፊ የሆነውን የየማነ መንጁስን ነገር እንመልከት። የማነ መንጁስ የህወሃት አገልጋይ በመሆን፤ ብዙዎች እንዲታሰሩ እንዲደበደቡ ብሎም እንዲገደሉ ያደረገ ሰው ነው። ሰሞኑን በተደረገው ኢህአዲጋዊ ግምገማ ግን፤ ግለሰቡ ግዴታውን በብቃት እንዳልተወጣ ይነገረዋል። እንደማስረጃም አሁን በኦሮሚያ ያለውን አመጽ መቆጣጠር አለመቻሉ ሲነገረው፤ ሰውየው እራሱን መቆጣጠር ተስኖት… የራሱን ህይወት ለማጥፋት ሽጉጥ ጠጥቶ፤ በሞት እና በሞት መሃል ሆኖ ሆስፒታል መሄዱን ሰምተናል። ይሄ ሁሉ እንግዲህ ስርአቱ በሰዎች ላይ የሚፈጥረው ጫና ውጤት መሆኑ ነው።
ለማጠቃለል ያህል… እንደ ዳኛ ተገኔ ጌታነህ በእውነት እና በቅጥፈት መካከል ሆነው፤ ምርጫቸው መኖር ወይም አለመኖር፤ ቅንጦት ወይም እጦት ሆኖ ህይወታቸውን የሚገፉ ብዙ ናቸው። ለሙያቸው እና ለህግ ልዕልና ሲሉ ለሃቅ የሚሞቱ እንዳሉ ሁሉ፤ በአሳዛኝ መልኩ ለፖለቲካ ጥቅም ሲሉ ፍርድ የሚያዛቡ፤ የእለት እንጀራቸው ደም ደም የሚላቸው ብዙዎች ይኖራሉ። ፈላጭ ቆራጭ ስርአት እስካለ ድረስ የሁለቱ ወገኖች ሽኩቻ መቼም አያቆምም። እንደ’ውነቱ ከሆነ… አሁን በኢትዮጵያ ባለው እውነታ፤ የህግ ፍርድ ሰጪ አካል መሆን ማለት፤ በእሳት ላይ እንደተጣደ ገበር-ምጣድ ነው። ከላይም ከታችም እሳት ይነድበታል።
ወደፊት የአንዳርጋቸው ጽጌን የሞት ፍርድ የሚያጸና ብርቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ያስፈልጋል። ይህ ብቻ አይደለም። በኦሮሚያ ውስጥ የተለኮሰው፤ የዘረኝነት እሳት ከመጥፋቱ በፊት ጥፋተኛ የተባሉትን ግለሰቦች ወደ ፍርድ ቤት በማምጣት በህግ ሽፋን የሞት ቅጣት ሊሰጣቸው ይችላል። አወዛጋቢ የሆነው የኦሮሚያ እና የአዲስ አበባ ጉዳይ፤ የህገ መንግስት ትንታኔ ሲያስፈልገው፤ ከፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ቀጥሎ… መፍትሄ ሰጪው ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ነው።
ህሊና ላለው ሰው… ይሄን ሁሉ የሚንቀለቀል እሳት ተሸክሞ መሄድ ይከብደዋል። ሌላም እንጨምርበት። አሁን በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚታዩ ትላልቅ ጉዳዮች ወደፊት በይግባኝ ወደ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሲመጡ፤ ከመጨረሻው የፍርድ ወንበር ላይ ተቀምጦ የመጨረሻውን ፍርድ መስጠት ይከብዳል። ለምሳሌ ጋዜጠኞች፣ የፖለቲካ መሪዎች እና የሙስሊሞች መፍትሄ አፈላላጊ ሰዎች አሸባሪ ተብለው ተከሰዋል። ይህ ክስ እውነት እንዳልሆነ፤ የታችኛውም ሆነ የላይኛው ፍርድ ቤት ሁሉም ያውቀዋል። ለዚህ አይነቱ የፖለቲካ ክስ፤ ፍትሃዊ ውሳኔ መስጠት ሁሌም አስቸጋሪ ይሆናል። ያለምንም ማወላወል አይንን ጨፍኖ “አዎ ጥፋተኛ ነህ” ብሎ ተሳድቦ፤ “ወስደህ እሰረው!” ለማለት እንደ-ዳኛ ሃጎስ አይነት፤ እዝነ- ህሊና ያልፈጠረበት አይነት ሰው መሆን የግድ ነው።
በሚገርም ሁኔታ ለህሊናቸው ተገዢ የሆኑ ሰዎች፤ ስርአቱን በዚህ መልኩ ሲሰናበቱ፤ ህሊናቸውን ለፍርፋሪ የሸጡ ሰዎች ደግሞ ለአዲስ ሹመት የጠቅላይ ሚንስትሩን ቢሮ ደጅ ሊጠኑ ይችላሉ። እነሱም ለጠቅላይ ሚንስትርነት ከመሰየማቸው በፊት ለኢህአዴግ የሰጡት አገልግሎች ግምት ውስጥ ገብቶ ይመረመራል። በዚህ አይነት በሙያ ሳይሆን የፖለቲካ አቋምህ እየታየ ዳኛ ትሆናለህ። የዚህ አይነት የፖለቲካ ሹመኞች በበዙ ቁጥር፤ ቁልቁል እየወረደ ያለው ፍትህ፤ ልጓሙ እንደተበጠሰ መንኮራኩር እታች ወርዶ እንክትክቱ ይወጣል። አሁን የዳኛ ተገኔ ጌታነህን ከስራ መልቀቅ ለግል ህሊናው ተሳማሚ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ አዲስ የሚሾመው ግለሰብ ፍትህን ሳይሆን፤ ስርአቱን ለማገልገል ከቆመ፤ ለኢትዮጵያ ዘላቂ የፍትህ ተቋም መገንባት አይቻልም። “ለሁሉም ግዜ አለው” እንደሚባለው፤ መጪውን ግዜ አብረን የምናየው ይሆናል። እስከዛው ግን የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ፕሬዘዳንት ውሳኔ ከማድነቅ ውጭ ለመውቀስም ሆነ ለማሞገስ ግዜው ገና ይመስላል።
No comments:
Post a Comment